ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለረዥም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው የዩክሬን መልሶ ማጥቃት መጀመሩን ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ተናገሩ
ዩክሬን በሩሲያ ጦር ላይ እፈጽመዋለሁ ብላ ስትዘጋጅበት የቆየችው እና ብዙ የተጠበቀው የመልሶ ማጥቃት ኦፕሬሽን መጀመሩን የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ አረጋገጡ።
ፕሬዝዳንቱ ማረጋገጫ ከመስጠጣቸው በፊት ዩክሬን የመልሶ ማጥቃት ኦፕሬሽኗን ስለመጀመሯ መረጃዎች ሲወጡ ነበር።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንም ከቀናት በፊት “የዩክሬናውያኑ መልሶ ማጥቃት ተጀምሯል” ብለው ነበር።
ይሁን እንጂ የመልሶ ማጥቃቱ ኦፕሬሽን ስለመጀመሩ እስካሁን ከዩክሬን ፕሬዝዳንት ማረጋገጫ አልተሰጠም ነበር።
“የመልሶ ማጥቃት እና የመከላከል እርምጃዎች እየተከናወኑ ነው” ያሉት ዜሌንስኪ፤ የኦፕሬሽኑ ደረጃንም ይሁን ይዘት በመተለከተ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
የዜሌንስኪ ማረጋገጫ የተሰማው በደቡብ እና ምስራቅ ዩክሬን በሁለቱ ኃይሎች መካከል የሚደረገው ጦርነት ተፋፍሞ በቀጠለበት ወቅት ነው።
የዩክሬን ወታደሮች ረዥም ርቀት ሚሳኤሎችን እያስወነጨፉ በባክሙት ምስራቅ አቅጣጫ እንዲሁም ከዛፖሬዢያ በቅርብ ርቀት በደቡብ አቅጣጫ ወደፊት እየገፉ ነው የሚሉ ሪፖርቶች ከዩክሬን ወገን እየወጡ ነው።
ይህ ይባል እንጂ በአውደ ውጊው እየተከናወነ ያለውን በትክክል ማወቅ አዳጋች ነው። ሁለቱም ወጎችን እርስ በእርሱ የሚጣራስ ሪፖርት ሲያወጡ ቆይተዋል። ዩክሬናውያኑ በመልሶ ማጥቃት ወደፊት እየገፋን ነው ሲሉ ሩሲያውያኑ ደግሞ የዩክሬንን ጥቃት እያከሸፍን ነው ይላሉ።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አርብ ዕለት በተሰራጨ ቪዲዮ ላይ ሲናገሩ፤ የዩክሬን መልሶ ማጥቃት መጀመሩን ገልጸው የሩሲያ ኃይል በዩክሬን ጦር ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሎ መልሶ ማጥቃቱን እያከሸፉ እንደሆነ ተናግረዋል።
ለዚህ የፑቲን ንግግር ምላሽ በሚመስል መልኩ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ንግግር ሲያደርጉ፤ ፑቲን ማን እንደሆኑ እንደማያውቁ ለማስመሰል ትከሻቸውን ሰበቅ፤ ቅንድባቸውን ደግሞ ከፍ አድርገው፤ ሩሲያውያኑ ከአሁን በኋላ ‘ብዙ እንደማይቀራቸው’ መገንዘባቸው ጥሩ ነገር ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
ዜሌንስኪ የአገራቸው ጦር መሪዎች ጥሩ መነቃቃት ላይ ናቸው ካሉ በኋላ “ይህን ለፑቲን ንገሩት” ብለዋል።
ዜሌንስኪ ይህን መልዕክት ያስተላለፉት ከካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ነው። በዚህ የሁለቱ መሪዎች ውይይት ላይ ካናዳ 500 ሚሊዮን ዶላር አዲስ የጦር ድጋፍ ለዩክሬን እንደምታደርግ ይፋ አድርገዋል።
ከመሪዎቹ ንግግር በኋላ የወጣው የጋራ መግለጫ ሁኔታዎች ሲፈቅዱ ዩክሬን በተቻለ ፍጥነት የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል እንድትሆን ካናዳ ትደግፋለች ይላል።
የዩክሬን መልሶ ማጥቃት ዘመቻ ተጀምሯል ከተባለ በኋላ ከፍተኛ ውጊያ እየተካሄደባቸው ካሉ አካባቢዎች መካከል አንዱ ደቡባዊ ዛፖሬዢያ ነው። የሩሲያ መሪዎች እንደሚሉት ከሆነ የዩክሬን ጦር አዞቫ የተባለ የውሃ አካልን በቁጥጥራቸው ሥር በማድረግ የሞስኮን ኃይል ሁለት ቦት ለመቁረጥ ጥረት ላይ ናቸው።
ባለፈው ሳምንት ቮቫ ካህኮቭካ የተባለው ግድብ እንዲወድም መደረጉ የፈጠረው የውሃ መጥለቅለቅ በዩክሬን መልሶ ማጥቃት ኦፕሬሽን ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚኖረው ተገምቷል።
የፈረሰው ግድብ ያስከተለው መጥለቅለቅ 596 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ቦታን የሸፈነ ሲሆን ከ3ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቃላቸው ተመላክቷል።