ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከ156 ዓመታት በፊት የተዘረፉት የአፄ ቴዎድሮስ አልባሳት የት ነው ያሉት?
አንድ የታሪክ ተመራማሪ ከ156 ዓመታት በፊት የተሰረቁ የኢትዮጵያው ንጉሥ አልባሳት የት እንዳሉ ለማወቅ እየጣሩ ነው።
ተመራማሪው እነዚህ አልባሳት በእንግሊዝ ማንቸስተር እንደሚገኙ እምነት አላቸው።
ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ በእንግሊዝ ወረራ ወቅት እጅ አልሰጥም ብለው መቅደላ ላይ የራሳቸውን ሽጉጥ ጠጥተው ከሞቱ በኋላ ለብሰውት የነበረው የክብር ካባ እና የአንገት ልብስ ከአስክሬናቸው ላይ ተገፎ ተወስዷል።
አልባሳቱ ወደ እንግሊዝ ከተወሰዱ በኋላም በስታሊይብሪጅ፣ ስታምፎርድ ፓርክ ሙዚየም ውስጥ ተቀምጠው ነበር።
ሙዚየሙ በ1950ዎቹ ከፈረሰ በኋላ ግን እነዚህ ጥንታዊ ቅርሶች የት እንዳሉ አይታወቅም።
አንድሩ ሔቨንስ የተባሉት የታሪክ አዋቂ እነዚህ አልባሳት ከማንቸስተር ከተማ እንዳልወጡ እምነት አላቸው።
በመሆኑም የከተማዋ ነዋሪዎች የጥንታዊ ዕቃዎች ማስቀመጫዎቻቸውን እንዲፈትሹ እያሳሰቡ ነው።
ምሁሩ እንደሚሉት የተረፉትን የንጉሡን አልባሳት ማግኘት ወሳኝ ነው።
ኢትዮጵያም በጦርነቱ ወቅት የተወሰዱ ቅርሶቿ መልሳ ለማግኘት እየጠየቀች ሲሆን፣ በተመሳሳይ ግሪክም በእንግሊዝ የተወሰደባትን ‘ኢልጂን ማርብል’ ከድንጋይ የተሠሩ ጥንታዊ ቅርጻ ቅርጸች እንዲመለሱላት ትፈልጋለች።
እንግሊዝ በቀድሞዋ አቢሲኒያ በአሁኗ ኢትዮጵያ ላይ ወረራ የፈፀመችው በወቅቱ በንጉሡ የታሰሩ አውሮፓውያን እስረኞችን ለማስፈታት በሚል ነበር።
በዚህ ጦርነትም አፄ ቴዎድሮስ ራሳቸውን በማጥፋታቸው ድል የተቀዳጀው የእንግሊዝ ጦር የወርቅ ዘውዶችን፣ የብራና ጽሑፎችን ጨምሮ በርካታ ቅርሶችን ዘርፈው አገሪቷን ለቀው ወጥተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የንጉሡን የአንገት ልብስ እና ካባ እንዲሁም የቁንዳላቸውን ዘለላ ቆርጠው ወስደዋል።
አፄ ቴዎድሮስ ከእቴጌ ጥሩወርቅ የሚወልዱት እና በወቅቱ የ7 ዓመት ታዳጊ የነበረው ተወዳጅ ልጃቸው ልዑል አለማየሁም ወደ እንግሊዝ ተወስዶ በብቸኝነት ካሳላፈ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በ18 ዓመቱ ሕይወቱ አልፏል።
በ19ኛው ክፍለ ዘመን ከእንግሊዝ ነገሥታት ጎን የተቀበረው የልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስ አፅም ወደ አገሩ እንዲመለስ ጥያቄ ቢቀርብለትም የባኪንግሃም ቤተ መንግሥት ጥያቄውን እንደማይቀበለው በቅርቡ መግለጹ ይታወሳል።
በጉዳዩ ላይ መጽሐፍ የጻፉት የታሪክ ተመራማሪው ሔቨንስ እንደሚሉት በመቅደላው ጦርነት ወቅት የተወሰዱ ቅርሶች ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በአገሪቷ ውስጥ ይገኛሉ።
ከአምስት ዓመት ገደማ በፊትም የብሔራዊ ጦር ሙዚየም የንጉሡን የፀጉር ዘለላ ወደ ኢትዮጵያ መመለሱም ይታወሳል።
ከሐር የተሠራው የንጉሡ ትንሽ የአንገት ልብስም ስታሊይብሪጅ ውስጥ በሚገኘው ሰታምፎርድ ፓርክ ሙዚየም ውስጥ ተቀምጦ ነበር።
ሙዚየሙ በ1950ዎቹ ከፈረሰ በኋላ የንጉሡ የአንገት ልብስ ወይም የካባው ክፍል በሆነ ሰው ቤት ውስጥ እንደሚገኝ ሔቨንስ እምነት አላቸው።
የተረፉት ሌሎች ቅርሶችም ወደ ሌሎች የአካባቢው ሙዚየሞች ተሰራጭተዋል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮም የታሪክ ምሁሩ ለታሜሳይድ የአካባቢ ጥናት ተቋም፣ ለመዘክሮች እና ለማንቸስተር ሙዚየም ጥያቄ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
ሆኖም ስታሊይብሪጅ ቤተ- መጽሐፍት እና ታሜሳይድ ሙዚየም እነዚህ አልባሳት እነርሱ ጋ እንደሌሉ ገልጸዋል።
በዚህም ሔቨንስ ስለ ንጉሡ አልባሳት መገኛ መረጃ ለማግኘት ያደረጉት ጥረት እስካሁን ፍሬ አላፈራም።
“የንጉሡ የአንገት ልብስ ጠፍቷል፤ አሊያም ወድሟል” ይላሉ ሔቨንስ።
በሌላ በኩልም “አልባሳቱ በተለይ በጥሩ ማስቀመጫ ውስጥ ተይዘው ከነበረ፤ ሙዚየሙ ሲፈርስ የሆነ ሰው ወደ ቤቱ ወስዷቸው ሊሆን የሚችልበት ዕድልም እንዳለ አስባለሁ” ብለዋል ተመራማሪው።
እንደ ብሔራዊ የጦር ሙዚየም ከሆነ አፄ ቴዎድሮስ ከ1855 ጀምሮ አገሪቷን ያስተዳደሩት በጦርነት ውስጥ ሆነው ሲሆን፣ በአገር ውስጥም በርካታ ፈተና ገጥሟቸው ነበር።
በእነዚህ ፈተናዎች ውስጥ የነበሩት ንጉሡ እንደ አውሮፓውያኑ 1862 የእንግሊዝ መንግሥት ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው እና የሚረዷቸው ባለሙያዎችን እንዲልኩላቸው ቢጠይቁም፤ መልስ አላገኙም ነበር።
በዚህም ምክንያት በርካታ የአውሮፓ ዜጎችን ያሰሩ ሲሆን ከእነዚህ መካከል የእንግሊዝ ቆንስል ካፒቴን ቻርለስ ካሜሩን ይገኙበታል። ቆንስሉ ለሁለት ዓመታት ታስረው ቆይተዋል።
ይህም በእንግሊዝ ሕዝብ ዘንድ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን፣ለድርጊታቸው ምላሽ ለመስጠት የአገሪቷ መንግሥት ወረራ እንዲፈፅም እና ቅርሶች እንዲዘረፉ ምክንያት ሆኗል።
የታሪክ አዋቂዎች እንደሚናገሩት በጦርነቱ ወቅት ከመቅደላ የተሰረቁትን ቅርሶች ለማጓጓዝ 15 ዝሆኖች እና 200 በቅሎዎች አስፈልገው ነበር።
እንደ አውሮፓውያኑ 2008 ኢትዮጵያ በተለያዩ የእንግሊዝ ተቋማት የሚገኙ ቅርሶቿ እንዲመለሱላት ይፋዊ ጥያቄ ማቅረቧም አይዘነጋም።