የ1966ቱን አብዮት ያቀጣጠሉ የጥበብ ሥራዎች የትኞቹ ናቸው?

የየካቲት 66ቱ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮት ዘውዳዊውን አገዛዝ ከገረሰሰ ዘንድሮ 50ኛ ዓመቱን ደፍኗል።

የንጉሡ ከሥልጣን መወገድ ‘ቁጣ ነው’ ብለው ያለቀሱና ‘ኢትዮጵያም አበቃላት’ ብለው በሐዘን የተዋጡ በአንድ ወገን ሲቆሙ ‘ኢትዮጵያ ቀን ወጣላት’ ብለው በደስታ የቦረቁና ‘በኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ’ መመሥረት ተስፋ የጣሉ በሌላ ወገን ቆመዋል።

አብዮቱን መለስ ብለው ሲያስታውሱ፣ አብዮቱን ተከትሎ ሥልጣን የጨበጠውና ‘ደም እንደ ጅረት ያፈሰሰው’ ብለው የሚገልጹትን ወታደራዊው የደርግ አገዛዝ በስብራት የሚገልጹ ወገኖች፣ ‘ለዚህ ነበር የታገልነው?’ ብለው በቁጭት ይብከነከናሉ።

አብዮቱን በማቀጣጠል፣ ሕዝብን በማንቃትና በማደፋፈር፣ የለውጥ ድምጽ በመሆን፣ ከአብዮቱ በፊትና በኋላም አመራሮችን በመተቸት፣ ኢ-ፍትሐዊነትን ነቅሶ በማውጣት፣ ቀውሶች ሲፈጠሩ ሕዝብን በማጽናናትም ጥበብ ድርሻ ነበራት። አብዮቱም የኢትዮጵያን ጥበብ በቅርጽ እና በይዘት ለውጧል።

በዚህ ዘገባ ሥነ ጽሑፍ፣ ሙዚቃ፣ ሥነ ጥበብ እና ቴአትር በ1966ቱ አብዮት ላይ የነበራቸውን ሚና እንዳስሳለን።

ሥነ ጽሑፍ እና አብዮቱ

“በመቃብር ዓለም አለ ወይ በውነት

በስም አጠራሩ ሚባል ነፃነት

ነፃነት ምትሉት ከውጭ አጥቂ ጠላት መጠበቁን ነው

ወይንስ በርግጡ ሌላ ፍቺ አለው

የውስጥ ነፃነትስ በመሀል በናንተ

ዘየው ሳይታወቅ ከንቱ የሻገተ

ከዝምታ ብዛት ለብዙ ዘመን

ምርምር ሳይገባው ሳይተነተን

ዋጋውን አጥቷል ወይ በናንተ ዝንጋታ

በእናንተ ዝምታ

ወይንስ ንቁ ነው እጅግ የበረታ. . .”

(ዮሐንስ አድማሱ፣ ‘እስኪ ተጠየቁ’)

ዮሐንስ አድማሱ በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ ታላቅ አስተዋጽኦ ያበረከተ ገጣሚ እና ሃያሲ ነበር። አብዮቱን ካቀጣጠሉ ፀሐፊዎች መካከል ይጠቀሳል።

‘እስኪ ተጠየቁ’ የተሰኘው ረዥም ግጥሙ የንጉሡን ሥርዓት አምርሮ በመተቸት ይታወሳል።

ያኔ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ንጉሡ በተገኙበትም ጭምር ሥርዓቱን በማውገዝና ለውጥን በማቀንቀን ታሪክ ጽፈዋል።

ፀሐፌ ተውኔትና ገጣሚ አያልነት ሙላት ግጥም አቅርቦ ዋንጫ ከመሸለም አንስቶ፣ ቆየት ብሎ ደግሞ በግጥሙ እስከመታሰር ድረስ የዘመኑን ከፍና ዝቅ ኖሮታል።

በዩኒቨርስቲው በበዕደማርያም ትምህርት ቤት 12ኛ ክፍል ተማሪ እያለ ‘ግጥም ጽፌ ልወዳደር’ ብሎ ጠየቀ።

ያኔ እንኳንስ የበዕደማርያም ተማሪ ይቅርና የዩኒቨርስቲው የመጀመሪያ ዓመት ተማሪም ‘እንደ ሰው’ አይቆጠርም ነበር ሲል ያስታውሳል። ለምን? ቢባል ‘በክሪስመስ’ ሊባረር ይችላል ተብሎ ስለሚጠበቅ።

አያልነህን፣ ‘አንተ ደሞ ግጥም ትችላለህ?’ ብለው ቢያጣጥሉትም እንደምንም አሳምኖ ‘የትኛው ነው ልጅሽ?’ የሚል ግጥም ጽፎ አስገባ።

በዚህ ግጥሙ ተወዳድሮ ዋንጫ ተሸለመ። ከዚህ በኋላ በጻፋቸው ግጥሞች እና ተውኔቶች ግን የጠበቀው ሽልማት ሳይሆን መታሰርና መደብደብ ነበር። በሦስት የኢትዮጵያ ሥርዓቶች ሥነ ጽሑፍ ዋጋ አስከፍሎታል።

“በተማሪዎች እንቅስቃሴ ምክንያት ተደብድቤ፣ በደርግ ታስሬ፣ በኢሕአዴግም ከመምህራን ጋር ተባርሬ. . .” ሲል ያስታውሳል።

በቅድመ አብዮቱ በዋነኛነት የሚያነሳው ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ ተማሪዎችን ንጉሡ ወደ ዩኒቨርስቲ ሲያስገቡ ነው።

ንጉሠ ነገሥቱ ጋናን ጨምሮ ከቅኝ ግዛት ነጻ ከወጡ አገራት ወደ 60 ተማሪዎች አምጥተው ዩኒቨርስቲ አስገቡ።

ተማሪዎቹ ኢትዮጵያ ሲመጡ ባዩት ‘መቀዛቀዝ’ ሳይገረሙ አልቀሩም። ምክንያቱም ያኔ ንጉሡ በተማሪዎች ይካቡና ይሞካሹ ነበር።

“ነጻነትን የሚያውቁ፣ የቅኝ ግዛትን ችግር የተገነዘቡ ነበሩ። ዩኒቨርስቲ ሲገቡ ምንም ነገር አላዩም። እንድያውም ንጉሡ እየተጋበዙ ግጥም ይነበብላቸው፣ ለተማሪዎች ሽልማት ይሰጥ ነበር። ተማሪዎቹ ‘እንዴ! ኢትዮጵያ ያለው የተማሪ እንቅስቃሴ እንዴት የሞተ ነው!’ አሉ” ሲል አያልነህ ያስታውሳል።

ወደ 1960ዎቹ ስንመጣ ግን ተማሪዎች ዋነኛ የንጉሡ ተቃዋሚና ተቺ ሆኑ። የገበሬውን ጥያቄ የሚያስተጋቡ የተማሪ ገጣሚዎች ተበራከቱ።

ኃይሉ ገብረዮሐንስ (ገሞራው) ሳይጠቀስ አይታለፍም። የገሞራው ‘በረከተ መርገም’ ግጥም የተማሪዎች እንቅስቃሴ አቀጣጣይ ሆነው ከሚጠቀሱ አንዱ ነው።

“ያልተደረገውን፣ ከፅንፍ እስከ አድማስ ጊዜን ጊዜ ገጭቶት

ይወልደው ይመስል፣ መዋቲውን መንፈስ ከቶ መመሥረትህ

በደል ለማጽደቂያ የውሸት ምክር ቤት

በተስማምቻለሁ ለማድለብ ከሆነ የሰዎችን ሙክት

ጮማ ለማይወጣው ከአኞ በስተቀር ልፋጭ ሊያበረክት

አስበህ ከሆነ እንዲያ እነደዲያ ማድረግህ የሰው ልጅ ለማወክ

መንጋ ማጎሪያውን ፓርላማ ነው ብለህ ለኛ ሰላሳለፍክ

ያንግሎ ሳክሶኑ ለፍዳዳው ዊልያም ዘርህ አይባረክ. . .”

(ገሞራው፣ ‘በረከተ መርገም’)

ዩኒቨርስቲ ተገኝተው ግጥም አድምጠው፣ ሸልመው ይሄዱ የነበሩት ንጉሥ ተቀይመው ወደ ዩኒቨርስቲ መሄድ አቆሙ።

አያልነህ እንደሚያስታውሰው፣ ለጃንሆይ የሚቀርቡ ግጥሞች ‘ይገምገሙ’ ተብሎ እነ ፕ/ር ዓለማየሁ ሞገስን የመሰሉ ባለሙያዎች ቢመደቡም የተቃውሞ ግጥሞችን ማስቆም አልተቻለም።

“እነ ነገደ ጎበዜ፣ እነ ተገኘ ተሻወርቅ. . . በቃ ምን ልበል፣ በርካታ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀመሩ። በግጥሞቻቸው የንጉሠ ነገሥቱን ሥርዓት ማውገዝና መሳደብ ጀመሩ።”

‘መሬት ላራሹ’ የሚሉ፣ የፊውዳሊዝምን ጭቆና አምርረው የሚተቹ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ተበራከቱ።

የዳኛቸው ወርቁ ‘እምቧ በሉ ሰዎች’ የሕዝብን ስቃይ ነቅሰው ካወጡ ሥራዎች መካከል ይጠቀሳል።

‘ምላሴን ተውልኝ’ እና ‘ኢትዮጵያዊ ማነው?’ ተጠቃሽ ሥራዎች ናቸው።

“መጨረሻ ላይ በእነዚህ ሥራዎች ነው ንጉሠ ነገሥቱ ተገልብጠው ደርግ ተንጠልጥሎ ሥልጣን ላይ የወጣው” ሲል አያልነህ ይገልጸዋል።

የሥነ ጽሑፍ ሥራዎቹ የተማሪዎች ንቅናቄ አካልና አብዮቱን አቀጣጣይ ስለሆኑ ነው ተማሪዎቹ ‘ማዕበል ጠሪ ወፍ’ በሚል የሚሞካሹት።

ግን ደግሞ የዚህ እንቅስቃሴ አካል ከሆኑት ተማሪዎች እንዲሁም ጸሐፍት መካከል የተወሰኑት “በአብዮቱ ተበልተዋል። ያነደዱት የአብዮት እሳት አቃጥሏቸዋል” ሲል ነው የሚገልጻቸው።

በልብ ወለዱ አቤ ጉበኛ፣ ሀዲስ ዓለማየሁና ሌሎችም በርካታ ጸሐፍትን እናገኛለን።

“አስበውበት ወይም ጉዳዩን አጢነው ጻፉት ለማለት ባንደፍርም ፊውዳሊዝምን ያጋለጠ ሥራ ‘ፍቅር እስከ መቃብር’ ነው” ይላል አያልነህ።

የባላባቱን ሥርዓት በመገዳደርና አብዮተኛነትን በማቀጣል ረገድ ልንጠቅሰው እንችላለን።

የአቤ ጉበኛ ‘አልወለድም’ እና ‘ሰይፈ ነበልባል’ ለማኅበረሰባዊ ንቃት እንዲሁም ዘውዳዊውን ሥርዓት እምቢኝ ለማለት ከፍተኛ ሚና ነበራቸው።

እነዚህ ሥራዎች “ያውም የሳንሱር ቢላዋን አልፈው ነው ለሕዝቡ የደረሱት” ሲል ይገልጻል።

ሳንሱር ባይኖር ደግሞ ምን ይጽፍ ነበር? ካቀረበው ሥራ ላይ በሳንሱር ምን ተነሳበት? ምን ተፈቅዶለት ወጥቶ ነው ይህን ያለው? የተፈቀዱት ጽሑፎች እንኳን አገር ማናጋት ከቻሉ የጻፈው ሙሉውን ቢወጣ ምን ይፈጠር ነበር? በማለት አያልነህ ይጠይቃል።

እነዚህ ሥራዎች አቤን ለግዞት ቢያበቁትም፣ የሕዝቡን እሮሮ አብሮ ተካፍሏል። ከወጣበት ማኅበረሰብ ሕይወቱን አጣምሮ ሥርዓቱን በጽኑ ተቃውሟል።

ደራስያኑ ሊደርስባቸው የሚችለውን ለመጋፈጥ ቆርጠው ጽሑፎቹን ለሕዝብ አበርክተዋል። ሥራቸው ዋጋ ያስከፈላቸውም ጥቂት አይደሉም።

እነዚህን አብዮት አቀጣጣይ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ሁሉም ወዷቸው አጣጥሟቸዋል ማለት ግን አይደለም።

ችግሩ ያለው ዘውዳዊው ሥርዓት ጋር ሳይሆን ተቃዋሚ ተማሪዎች ጋር እንደሆነ በማመን ተማሪዎችን የነቀፉ ነበሩ።

ምናልባትም ለዘመናት የዘለቀው የንጉሥ ፍራቻ የተማሪዎችን ተቃውሞ መልሰው እንዲቃወሙ ሳያደርግ አልቀረም።

“በተለይ በከተማ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ሲደረግ ሁሉም ነዋሪ አልደገፈም። እንዲያውም ተማሪዎች በፖሊስ ሲደበደቡ ‘በለው! ይሄ ፉርኖ ያጠገበው! ኬክ ያጠገበው! በለው!’ እያለ ሕዝቡ ከሥርዓቱ ጎን ቆሞ ይሳደብ ነበር” ይላል አያልነህ።

ይሄ የፈጠረው ቁጭት የመንግሥቱ ለማን ‘ባሻ አሸብር ባሜሪካ’ ግጥም እንዲሁም ‘ያላቻ ጋብቻ’ ተውኔትን አጭሮ እንደ ትግል መቀስቀሻ መሣሪያ ውለዋል።

ምሁራን ወደ ገጠር እየሄዱ ሕዝቡን እንዲያነቁ ማድረግ የንቅናቄው አካል ነበር።አያልነህ አብዮቱን ያለ ሥነ ጽሑፍ ማሰብ አይቻልም ይላል። አብዮቱ የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍን በተለይም በይዘትም የለወጠ ነው።

“አብዮቱን ያለ ሥነ ጽሑፍ ወይም ያለ ጥበብ ማሰብ አይቻለም። ጀግንነትን በማሞገስ፣ አመራሩን በመደገፍም በመንቀፍም፣ ሕዝቡን በማንቃትም ጥበብ ሚና ነበራት።”

አብዮቱ በሥነ ጽሑፍ ትልቅ ለውጥ አመጣ ብሎ የሚያስበው ‘ንጉሥ አይከሰስ. . .’ ከሚለው አሳሪ ዕሳቤ መላቀቅ በማስቻሉ ነው።

“ገበሬን ‘እድፋም’ ‘ቆሻሻ’ ‘ጥፍራም’ ማለት ምንም ችግር አልነበረም። ጥንቃቄው ለቤተ መንግሥቱና አካባቢው ነበር። አብዮቱ ይህንን ገለበጠ። ንጉሥን መስደብ፣ ማርከስና ማውገዝ ይቻላል። ገበሬውን ግን ተጠንቀቁ። ወዛደሩን ግን ተጠንቀቁ ተባለ።”

ኪነ ጥበብ የሕዝብ ናት፣ የምትወጣው ከሕዝብ ነው፣ የሕዝብም አንደበት ናት ቢባልም ለዘመናት ንጉሣውያኑን እንጂ ሕዝብን አታሞግስም ነበር።

አብዮቱ ግን የገበሬውን፣ የሠራተኛውን፣ የድሃውን መደብ ነው መካብ ያለባችሁ ብሎ መጣ።

“መሬት ላራሹ ብላችሁ ዘምሩ ተባለ። መሬት ከፊውዳሉ ይውጣና ለገበሬው ይከፋፈል ተባለ። ይሄ በደራሲውና ኅብረተሰቡ ትስስር የፈጠረ ነው” ሲል ነው አያልነህ የሚገልጸው።

እነ መንግሥቱ ለማ፣ ፀጋዬ ገብረመድኅን (ሎሬት)፣ ብርሃኑ ዘሪሁን፣ በዓሉ ግርማ፣ “ስለ ንጉሠ ነገሥቱ ይጨነቁ የነበሩ ሁሉ ስለ ገበሬው ማውራት ጀመሩ” ይላል።

የብርሃኑ ዘሪሁን ‘ማዕበል’ እንዲሁም ሌሎችም ጽሑፎቹ ማጠንጠኛቸው የገበሬው ሕይወት ሆነ።

ስለ ችግረኛው፣ ስለተራበው፣ መሬት ስላጣው ዘምሩ ሲባል “ሥነ ጽሑፉ፣ ሙዚቃው፣ ድራማው ነጻ ወጣ። በቃ ጥበብ ነጻ ወጣች” ይላል።

ሙዚቃ እና አብዮቱ

ድምጻዊ ተሾመ ምትኩ ‘በእጆቼ እየዳሰስኩ እንዳላጫውትሽ፣ ሰው ከማይደርስበት ጋራ ሥር ነው ቤትሽ. . .’ እያለ መድረክ ላይ ያቀነቅናል።

ተማሪዎች ሙዚቃውን እየሰሙ ቢዝናኑም መስማት የፈለጉት ሙዚቃ ግን ሌላ ነው። የፈለጉት ሙዚቃ እንዲቀርብላቸው በፉጨትም፣ በጭብጨባም ይገፋፋሉ።

ተማሪዎቹ ድምጻዊውን ከመድረክ አላስወርድ አሉት። እያመነታም ቢሆን የፈለጉትን ዘፈነላቸው።

“ፋኖ ተሰማራ፣ ፋኖ ተሰማራ

እንደ ሆ ቺ ሚኒ እንደ ቼ ገቫራ. . .”

በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መምህርት ዓለምነሽ አወል (ረዳት ፕሮፌሰር) “እንደ ንፋስ ሆ! ብሎ ወጣቱ የተነሳው በሙዚቃ ነው” የምትለው እንዲህ ያሉ የታሪክ አጋጣሚዎችን በመጥቀስ ነው።

“ተሾመ ምትኩ በቦታው ከነበረው የፖሊስ ሠራዊት ምን እንደሚጠብቀው ያውቃል። ተከብቧል። ፈርቷል። ግን ደግሞ የተማሪዎች ጥያቄ በረታ። በጭብጨባ ከመድረክ አላስወርድ ሲሉት ‘ፋኖ ተሰማራ’ እያለ ዘፈነ። ያኔ ሙዚቀኞች እንዲህ ያለ ነገር ሲያደርጉ የቤተ መንግሥቱ ዐይን ውስጥ ይገባሉ። አሳዳጃቸው ይበዛል። ተሾመም ከዛ በኋላ እንዳይሠራ ጫና በረታበት።”

የ1950ዎቹ መጨረሻና 1960ዎቹ የኢትዮጵያ ሙዚቃ እንደሌሎቹ የጥበብ ዘርፎች ሁሉ አብዮቱ ሳይነካው አላለፈም።

“ንጉሥ አይከሰስ. . . በሚባልበት ጊዜ ተማሪውን ለማነሳሳት ሙዚቃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል” በማለት ነው ዓለምነሽ የምትገልጸው።

ሙዚቃ በቀጥታም በቅኔም ሥርዓቱን የተጋፈጠበት ዘመን ነበር። ለትርጓሜ ክፍት ሆነው ውዝግብ ከፈጠሩ ሙዚቃዎች መካከል ዓለምነሽ የጥላሁን ገሰሰን ‘እስከመቼ’ ትጠቅሳለች።

‘እስከመቼ ባንቺ ባህሪ እነዳለሁ፤ አልቻልኩም አርሚ ብያለሁ. . .’ የሚለው ዘፈን፣ “ለሴት የተዘፈነ ይመስላል እንጂ የንጉሡን ሥርዓት ለመቃወም ነው” ተብሎ ደራሲው ሐንስ አፈወርቅ እንዲያርመው ታዘዘ።

“ከዛ ‘የፍቅር ዘፈን’ እንዲመስል ተብሎ ከብዙነሽ በቀለ ጋር እንዲዘፍኑት ተደረገ። ግን ምንም ለውጥ አላመጣም።”

የፍትሕ ጥያቄን ለማስተጋባትና ጭቁኖችን ለማነሳሳትም ሙዚቃዎች ተጽፈዋል። 1957 ዓ.ም. ላይ የጦር ሠራዊቱ የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄን ሲያነሳ ተስፋዬ አበበ ‘አትበሳጭ’ የሚል ዘፈን ደርሷል። የዘፈነው ዓለማየሁ እሸቴ ነበር።

“የእዬዬ ወሸኔ የዋኔ ጭፋሮ

በእከክ መሰንቆ ውርደት እንጉርጉሮ

በፎከት ዳንኪራ በስቃይ ከበሮ

እዛ ፈላ ሞላ ላምናም ለዘንድሮ”

ዓለምነሽ አብዮቱን የምትገልጸው “ብዙ ሙዚቀኞችን ያገኘንበት ወቅት፣ ለሙዚቃም ብዙ በር የተከፈተበት” በማለት ነው።

ሙዚቃዊ ድራማዎችም ሕዝብን የማንቃትና የማነሳሳትም ሚና ተጫውተዋል።

“አብዮቱን ያለ ሙዚቃ በፍጹም ማሰብ አልችልም” ስትል ነው መምህርቷ የምትገልጸው። በእሷ ዕይታ አብዮቱን ያነሳሳውም ያነቃቃውም ሙዚቃ ነው። ያለ ሙዚቃም አብዮት የለም።

አንዳንዴም የተቃውሞ ይዘት የሌላቸው ዘፈኖች ራሱ ‘ንጉሡን ለመቃወም ነው’ በሚል ዘፋኞቹ ይንገላቱ እንደነበር ትናገራለች። በአብዛኛው ግን የተቃውሞ ሙዚቃዎች ከጥግ እስከ ጥግ አስተጋብተዋል።

ሙዚቃው “ሕዝብ ተርቦ ንጉሡ ግን ውሻ ተንከባክበው ያሳድጋሉ” ብሎ ሲተች የተቀበለው ሁሉም አልነበረም። ምክንያቱም ንጉሥን መንካት እንደ ‘ወንጀል’ አልያም እንደ ‘ኀጥአት’ ስለሚቆጠር።

“በልጅነቴ ንጉሡ ከሥልጣን ወረዱ የተባለ ጊዜ ሰዎች ሲያለቅሱ አስታውሳለሁ። እሳቸው ከሌሉ አገር አገር አይሆንም ተብሎ ነበር የሚታሰበው። ሰማይ ምድሩ ግልብጥብጥ እንደሚልብን ነበር የሚታሰበው። ግን ንጉሡ ሳሉ አይደል ሰው እየተራበ የነበረው? ንጉሡ ልደታቸውን በድግስ ሲያከብሩ የወሎ ሕዝብ እየተራበ ነበር። ወጣቶች የመጨረሻ ትንፋሻችንን እንተንፍስ ብለው የተነሱትም ለዚህ ነው።”

ወጣቶች ለኢሕአፓ ድጋፍ ወጥተው ፖሊስ ሲያሳድዳቸው የደበቁ፣ ወጣቱን ‘ተው አትቅበጡ!’ ብለው የገሰጹም ነበሩ።

ዋናው የአብዮቱ ማጠንጠኛ የነበረው ‘መሬት ላራሹ’ በሙዚቃው ተስተጋብቷል።

“መሬት ላራሹ

መሬት ላራሹ

ለላብ አፍሳሹ

አገሩን ለባላገሩ

ድል ላይ ቆመናል ለወዛደሩ”

ይሄንን በሚመስሉ ዜማዎች ታጅቦ አብዮቱ ፈነዳ።

ሙዚቃው በቅድመ አብዮቱ፣ አብዮቱ ሲፈነዳና በድኅረ አብዮቱም፣ ንጉሡን የመቃወም፣ ለውጥን የመቀስቀስ፣ ተማሪዎችን የመደገፍ፣ የደርግን ርዕዮተ ዓለም የማስተጋባትና በስተመጨረሻም ደርግን አምርሮ የመንቀፍ ሽግግሮች ውስጥ አልፏል።

የሙዚቃ መምህርቷ ዓለምነሽ ያንን ዘመን ለሙዚቃ ባበረከተው አስተዋጽኦና በተቃራኒው በፈጠረው አፈና በሁለት ፈርጅ ታየዋለች።

በአንድ ረገድ ሙዚቃው ሕዝባዊውን አብዮት ገፍቶ የሥርዓት ለውጥ ሲመጣ በሌላ በኩል ወንበሩ ላይ ያለው ብቻ ተለውጦ ሌላ ዓይነት አፈና በሙዚቃው መቀጠሉን ታወሳለች።

ቴአትር እና አብዮቱ

ጭሰኛው ባለቤቱ አራስ ቤት ታማ ተኝታ ጨንቆታል። የሚያደርገው ቢያጣ ብዙ ከብት የሚያረባው ከበርቴ ጋር ሄዶ “ሚስቴ የሚላስ የሚቀመስ አጣች። እንደው ቅቤ ብታገኝ፣ እንደው የአንዷን ጥገት ወተት ቢሰጡኝ” ብሎ ይማጸናል።

ከበርቴው ይህን ሲሰማ እንደተናቀ ቆጠረው። ተቆጣ።

“ጉድ ፈላ! ድሃ በቅቤ በላ!” ብሎ ይተርታል። ከጭሰኛው ጋር ይጣላል። ጭሰኛውን “እንዲያውም ርስቴን ለቀህ ውጣ!” ይለዋል።

ምስኪኑ ጭሰኛ በምጸት “ቢገባው ላስረዳው፣ ሦስት ክንድ ሌላ ርስት እንደሌለው” ይላል።

ከዚያ ዘመን ‘አብዮተኛ’ ቴአትሮች አንዱ በሆነው ‘ባሻ ዳምጤ’ ላይ ነው ይህ የሚታየው።

የፀጋዬ ገብረመድኅን ‘ሀሁ ፐፑ’፣ ‘እናት ዓለም ጠኑ’፤ የአቤ ጉበኛ ‘ባለ ካባና ባለ ዳባ’፤ የአያልነህ ሙላት ‘ደሀ አደግ’ አብዮትን ካቀጣጠሉ በርካታ ተውኔቶች መካከል ይጠቀሳሉ።

በተውኔት ድርሰትና ዝግጅት እንዲሁም በዘፈን ግጥምና ዜማ የሚታወቀው ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) የዘመኑን ጥበብ “መስዋዕትነት የተከፈለበት” ሲል የሚገልጸውም ለዚህ ነው።

በተለይም ከታኅሣሥ ግርግር ወዲህ ቴአትር አብዮተኛ እንደሆነ ያወሳል። ለአብዮቱ ክብሪት የጫሩና ለሕዝብ መብት የታገሉ መሆናቸውን ያክላል።

‘ባሻ ዳምጤ’ የተጻፈው የወሎ ረሃብን አስመልከቶ እንደነበርና፣ ቴአትሩ ሲሠራ ገና ረሃቡም በይፋ እንዳልታወጀ ያስታውሳል።

በጻፉት ወይም ባዘጋጁት ቴአትር መታሰር ለብዙዎቹ የጥበብ ሰዎች እንግዳ አልነበረም።

ተስፋዬ ገሰሰ (ረዳት ፕሮፌሰር) ከአንድም ሁለቴ በ ‘እቃው’ ቴአትር ታስሯል። ተስፋዬ አበበም እንደዚሁ።

ሳንሱር እየበረታ የሄደውም ‘ክብሪት ጫሪ’ ሥራዎች ሲበዙ እንደሆነ ይገልጻል።

በግንባር ቀደምነት በብሔራዊ ቴአትር እና በአገር ፍቅር አልፎ አልፎም በማዘጋጃ ቤት ይቀርቡ የነበሩ ተስፋዬ “የሕዝብ ልሳን” ሲል የሚገልጻቸው ቴአትሮች ተመልካቻቸውም ብዙ ነበር።

በንጉሡ ጊዜ በየቴአትር ቤቱና በወታደራዊ ሙዚቃ ክፍልም ‘አብዮታዊ’ ጽሑፍ ከተጻፈ ቅጣት ነበር የሚጠብቃቸው።

ተስፋዬ የጻፈውና ወጋየሁ ንጋቱ መሪ ተዋናይ የነበረበት ‘የወሬ ፈላስፋ’ ቢሮክራሲን ይተቻል። ከተዋንያኑ መካከል ሲራክ ታደሰ፣ ዓለምፀሐይ ወዳጆ እና ዓለሙ ገብረአብ ይገኙበታል።

“ከአዋቂው አልሆነ ወይም ከደንቆሮ፣ ሺ በሺ አባዛ ሳይወጣ ከዜሮ” በማለት ‘ያልተማረ አዋቂን’ በስላቅ ይተቻል።

‘የጥቁር ድምጽ’ ቴአትር ደግሞ “የውዝግብ መድረክ ፍረጂኝ አንቺ ዓለም፣ ሰው የእግዚአብሔር እንጂ የሰው ባርያ አይደለም” እያለ አፓርታይድን ይነቅፋል።

ተስፋዬ የጻፈው ‘ሕይወት ያለው በድን’ ቴአትር ወጣቱን እንዴት እንዳነቃነቀ ያስታውሳል። ቴአትሩ ገዢውን መደብ ለመተቸት ነበር የተጻፈው።

“ጭሰኛ፣ ባሪያ ተብሎ ሳይታወጅ ነው እኛ መድረክ ላይ ያወጅነው” ሲል ይገልጸዋል።

‘ሕይወት ያለው በድን’ ፊውዳሎችን ይኮንናል። እነዚህ ፊውዳሎች “ድሆችን የማላይበት መነጽር ምን ነበር ሳይንቲስቶች ቢሠሩልኝ” ሲሉ ይደመጣሉ። በዚህም ሕዝባዊ ቁጣና የለውጥ ጥያቄ ተቀስቅሷል።

በኃይሉ እሸቴ “ቆሻሻ ሞልቶ በጎዳና አላስኬድ ብሎኝ ሲቀረና፣ ይብስ በሽታ ሳይፈጥር ጠረገው አሉ ወታደር አንድም ሳይቀር” ሲል ያዜመው ገዢውን መደብ ለመሸንቆጥ ነው።

የታኅሣሥ ግርግር ሰሞን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ ተማሪዎች ተቃውሞ ሲወጡ፣ የክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ ከኋላቸው እየሄደ “አትነሳም ወይ! የአባትህ ጋሻ ትኋን ወረሰው” እያለ ሲያበረታታ ተስፋዬ ያስታውሳል።

ፈጥኖ ደራሹ በየተቃውሞው እየደረሰ በጭስ ይበትናቸዋል። እነሱም መልሰው ‘መሬት ላራሹ’ እያሉ መፈክር ይዘው ተመልሰው አደባባይ ይገኛሉ።

ተስፋዬ የሚገልጸው “በጥበብ የተቀሰቀሰው ወጣት እየጋለ ሲሄድ አብዮቱ እየዳበረ ሄደ። ለውጤትም በቃ” በማለት ነው።

አገር ፍቅር የታየው ‘ቀዩ ማጭድ’ ተስፋዬን ከጦር ሠራዊት ጋር ፊት ለፊት ያጋፈጠው ቴአትር ነበር።

“ያኔ ላብአደር ማለት አይቻልም ነበር። ቴአትሩ ግን በቀጥታ ስለ ላብአደር ያወራል። በተለይ የኢሕአፓ ወገንተኛ የሆነ እየገባ ያየው ነበር።”

የቴአትሩን መታየት ተከትሎ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ‘አቶ ተስፋዬና ቀዩ ማጭዳቸው’ ተብሎ ተጻፈ። “ቀዩ ማጭድ ማለት የኢሕአፓ ልሳን ማለት ነው” ከዚያ በኋላ ሰዎች የበለጠ ቴአትሩን ይመለከቱት ጀመረ።

ታዲያ አንድ እሑድ ቀን ቴአትሩ ሲታይ ጊቢውን ጦር ሠራዊት ወረረው። ግርማዬ መኮንን የወዛደር ልብስ ለብሶ፣ ጠመንጃ ይዞ ይተውናል። ቆየት ብሎ ደግሞ የሲቪል ልብስ ለብሶ፣ የቀበሌ ሊቀ መንበር ሆኖ ይሠራል።

ከአንዱ ገፀ ባህሪ ወደ ሌላው ለመቀየር ልብሱን ሊለውጥ ሲገባ ‘ኢሕአፓ በዛ በኩለ ስንጠብቅሸ በዚህ መጣሽ’ ብለው ወታደሮች በከስክስ ጫማ ደበደቡት።

ተስፋዬ ጣልቃ ገብቶ፣ “አዳራሹ ተረብሾ የመንግሥት ንብረት የሆነ ወንበር ከሚሰባበር ለምን ሰው ሲወጣ አይፈተሽም?” ብሏቸው ቴአትሩ ቀጠለ። ተዋናዩ በድንጋጤ ቃለ ተውኔቱ ጠፍቶበት እንደምንም ጨረሱ።

አብዮቱ ከፈነዳ በኋላ በአንድ በኩል ደርግ ፕሮፓጋንዳ የሚያስፋፋባቸው ተውኔቶች ሲሠሩ፣ በተቃራኒው የሥርዓቱን ጭቆናና የወጣቱን እልቂት የሚነቅፉ ቴአትሮችም ተበራክተዋል።

እነዚህ ሥራዎች የጥበብ ባለሙያዎችን ለሞት፣ ለድብደባ፣ ለእስርና ለስደት የዳረጉም ነበሩ። ቴአትርን የማገድና ከመድረክ የማውረድ እርምጃም ይወሰድ ነበር።

ሥነ ጥበብ እና አብዮቱ

በቅድመ አብዮቱና በድኅረ አብዮቱም የሥነ ጥበብ ሚና እንደሌሎች የጥበብ ዓይነቶች ‘ሰፊና ሕዝባዊ’ ከመሆን ይልቅ በሥነ ጥበቡ ክበብ ውስጥ ታጥሮ መቆቱ ያመዝናል።

በአለ ፈለገሰላም ሥነ ጥብበ ትምህርት ቤት መምህርና የገብረክርስቶስ ደስታ ሙዝየም ዳይሬክተር የሆነው ሠዓሊና ቀራፂ በቀለ መኮንን (ተባባሪ ፕሮፌሰር) እንደሚለው፣ ለዚህ ምክንያቱ የኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ለዘመናት ሃይማኖታዊ መሆኑ ነው።

እንደ ሙዚቃ እና ሥነ ጽሑፍ ማኅበራዊ ሚና በመጫወት የዕለት ከዕለት ሕይወትን ከማሳየት ወይም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ፖለቲካዊ መሣሪያ ከመሆን ይልቅ ሃይማኖታዊ ሆኖ ለበርካታ ዓመታት ቆይቷል።

በተለይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ነበር ሥነ ጥበብ ጎልቶ የሚታየው። ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው (Veneration Art) ከቤተ እምነት ወጣ ከተባለም የጦር ሜዳ ውሎን ለማሳየት ነበር የሚውለው።

አለ ፈለገሰላም ሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት በቅድመ አብዮቱ (በ1950 ዓ. ም.) ቢመሠረትም በኢትዮጵያ ከሃይማኖታዊ ይዘት ውጭ የሆነ ሥነ ጥበብ (Secular Art) ቆየት ብሎ ነው የተጀመረው።

በቀለ ሲያስረዳ፣ “ሥነ ጥበብ ለምን በዕለት ከዕለት ጉዳይ ውስጥ አልመጣም? ስንል ሃይማኖት ቤት ውስጥ ማደጉን እንደ ምክንያት ልናነሳው እንችላለን” ይላል።

በእርግጥ በግለሰቦች ደረጃ የተወሰኑ ሙከራዎች ነበሩ። በዓድዋ ጦርነት ወቅት የተሠሩ የጦር ሜዳ ተጋድሎን የሚያሳዩ ሥራዎችን መጥቀስ ይቻላል።

ከዚህ ውጭ የቤተ መንግሥት ውሎን ለመሳየት ውሏል። የንጉሣውያንን ግለ ምሥል (Portrait) መሥራት ሌላው ነው።

“ለቤተ ክርስቲያን የሚሠሩ ሥዕሎችን ስንመለከት የሠዓሊው ስም እንኳን እንዲያርፍባቸው አይጠበቅም። ምክንያቱም እንደ መመጻደቅ፣ እንደ ትዕቢት ስለሚወሰድ። ጥግ የያዘ ትህትና ይፈለጋል” ሲል ነው በቀለ የሚያስረዳው።

ሥነ ጥበብ ተቺ ወይም በዕለት ከዕለት ሕይወት የሚገባ እየሆነ የመጣበትን ሂደት “አዝጋሚ ነው” የሚለው በቀለ፣ ይህ አካሄድ እየተለወጠ የመጣውም በቅርብ እንደሆነ ያስረዳል።

አብዮቱ ሲፈነዳና በኢትዮጵያ ስለ ፖለቲካ መወያየት በይፋ ሲጀመር፣ የትኛውም መንግሥት እንደሚያደርገው የኢትዮጵያው ሥርዓትም ጥበብን የርዕዮተ ዓለም መግፊያ ወይም ማስረጫ አድርጎታል።

“ፊደል ባልቆጠረ ሕዝብ ውስጥ ጥበብ እንደ መሣሪያ አገልግሏል። ርዕዮተ ዓለም መግፊያ እንዲሆን ሲፈለግ መድረክ ተዘረጋ፣ ገንዘብ ተመደበ፣ እንቅስቃሴም ተጀመረ።”

በቅድመ አብዮቱና በድኅረ አብዮቱም ውስንም ቢሆን ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው የሥነ ጥበብ ሥራዎች ቢሠሩም በማኅበረሰቡ ውስጥ ሰርጾ ከመግባት እንዲሁም እንደሌሎች የጥበብ ዘርፎች ‘መንግሥትን ከማስደንገጥ’ አንጻር የነበራቸው ሚና እምብዛም አልነበረም።

ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሥነ ጥበብን አይቶና ተረድቶ፣ የመተርጎምና የመተንተን ባህል አነስተኛ መሆኑ እንደሆነ በቀለ ያስረዳል።

አብዮቱ ከመፈንዳቱ በፊትና በኋላም የተሠሩና አብዮታዊ ሊባሉ የሚችሉ የሥነ ጥበብ ሥራዎች እንደ ሌሎች አገራት ንቅናቄ የፈጠሩና የአብዮቱ ጉልህ አካል የነበሩ ለማለት እንደማያስደፍር ይናገራል።

ለምሳሌ ገብረክርስቶስ ደስታ የ66ቱን ድርቅ በተመለከተ የደረቁ (Mummify የተደረጉ) ሰዎችን የሚያሳዩና በቀለ “በጣም አሰቃቂ” ሲል የሚጠራቸው ሥራዎችን አሳይቷል።

እነዚህ ሥራዎች “እንደ ትልቅነታቸው ከአንድ ግጥም እኩል አገር የሚነቀንቁ አልነበሩም” ሲልም ያስረዳል።

እሸቱ ጥሩነህ ከሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ለመመረቂያ የሠራው ‘Victims of Famine’ ሌላው ጉልህ ሥራ ነው። በአጥንታቸው የቀሩ፣ መራመድ ያልቻሉ ሕጻናት፣ ሴቶችና አረጋውያንን፣ በረሃብ መንምነው የወደቁ ሰዎችን አስክሬን ያሳያል።

ሌላው የገብረክርስቶስ ‘ኖት ፍሮም አምባሳደር’ የተሰኘ ሥራ የድሃና የሃብታም ንጽጽርን፣ የከሲታና የወፍራም ንጽጽርን የሚያሳይ እንደሆነ በቀለ ይናገራል።