ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
“በወንድ ደራሲያን በሚገባ ተስለናል ብዬ ስለማላስብ ነው ስለሴቶች በትኩረት መጻፍ የፈለግኩት” ቤዛዊት ዘርይሁን
ቤዛዊት ዘርይሁን ለልብ ወለድ አንባቢያን አዲስ ስም አይደለም። በተለይ ደግሞ የሴቶች ጉዳይን ከአጀንዳዎች ፊት እንዲሆን ለማድረግ በሚሞክሩ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ላይ ስሟ ይነሳል።
የመጀመሪያ መጽሐፏ ‘የመሀል ልጅ’ ይሰኛል። ስለዚህ መጽሐፍ ስትናገር “የራሴ ታሪክ፣ ከህመሜ የተፈወስኩበት” በማለት ነው።
አሁን ደግሞ ‘ሃርካ ሂንኬኒኒ (Harka hin kennin) እጅ አትስጪ’ የተሰኘ የአጭር ልብ ወለዶች ስብስብ አሳትማለች። ይህ ስድስት አጫጭር ታሪኮችን የያዘው መጽሐፏ ወጣትነትን፣ ሴትነትን እና የሴትነት ፈተናን አንስቷል። ቢቢሲ ከቤዛዊት ጋር በመጽሐፏ ዙርያ ቆይታ አድርጓል።
* * *
ቢቢሲ- መጽሐፍሽ መግቢያ ላይ ካሰፈርሽው ሃሳብ ልጀምር። ለምንድን ነው የምትጽፊው?
ቤዛዊት- የምጽፈው በዚህ ዘመን ላይ እዚህች ቦታ ላይ ነበርኩኝ ለማለት ነው። አይተህ ከሆነ መጽሐፉ ላይ የሰውነት ጥያቄ ተደጋግሞ ይነሳል። ምንድን ነን? ትርጉማችን ይህን ያህል ነው? የሚለው ነገር ደጋግሞ ይታያል። እነዚህ ጥያቄዎች የእኔም ጥያቄዎች ናቸው። እየኖርኩኝ የምጠይቃቸው ጥያቄዎች ናቸው። አንዳንድ ጊዜ ቁጭ ብዬ ሳስበው ትርጉሜ [ሰው የመሆን] በጣም ያንስብኛል።
. . .ከአጠገባችን የሆነ ሰው ሲሞት የምንረሳበት ፍጥነት በጣም ያስገርመኛል። አብሮን ብዙ ያሳለፍን፣ አብረን ብዙ ታሪክ ሠረተን፣ ከዚያ የሆነ ሰዓት ላይ ከሕይወታችን ሙሉ በሙሉ አውጥተን እንረሳዋለን። ታዲያ በዙ ጊዜ በቃ ይህችን ታህል ነው ያስብለኛል።
እውነት ለመናገር ሰዎች ለሌላ ሰው ትርጉም ሰጥተው በሕይወታቸው ውስጥ ይዘውን የሚጓዙ አይመስለኝም። እና የምጽፈው ለራሴ ዋጋ ለመስጠት፣ በዚህ ዘመን እዚች ቦታ ላይ ነበርኩኝ የሚለውን የሆነ ቦታ ላይ ለማስፈር ነው።
ቢቢሲ- በመጽሐፍሽ ውስጥ ወጣትነት፣ ሴትነት፣ የሴትነት ፈተና አለ። ጽሁፎችሽን በዋናነት ማን እንዲያነብልሽ ትፈልጊያለሽ? እነማንን ታሳቢ አድርገሽ ነው የጻፍሽው?
ቤዛዊት- በተለይ የእኔ የራሴ ትውልድ የብዙ ነገር መፈተኛም፣ መሞከርያም ነን ብዬ ስለማስብ በዋናነት በእኔ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ወጣቶች ቢያነቡት ይበልጥ የምንግባባ ይመስለኛል። ታናናሾቻችን ደግሞ የተሻለ ይረዱኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። እውነት ለመናገር ከእኛ በዕድሜ ትንሽ ከፍ ያሉት የሚረዱኝ አይመስለኝም። ዘመን ከፈተናቸው ሰዎች ጋር ግን 'ሪሌት' የማደርግ ይመስለኛል።
ቢቢሲ- እዚህ መልስሽ ውስጥ የዘመንሽን ሰዎች አነሳሽ እንጂ በጾታ አልከፈልሻቸውም፤ ወንዶች ወይንስ ሴቶች ናቸው አንዲያነቡሽ የምትፈልጊው?
ቤዛዊት- አብዛኛው ሴቶች ያለፍኩባቸውን ነገሮች ያውቋቸዋል ብዬ አስባለሁ። አንዳንድ ጊዜ ከወንዶች ጋር ቁጭ ብዬ ለማስረዳት ስሞክር አውቀው ሳይሆን ተፈጥሯቸው የማይፈቅድላቸው በመሆኑ ብቻ የማያውቁት ነገር አለ፤ ለመረዳት የግድ ሴት መሆን አለባቸው። በጣም ጥቂት ወንዶች ምናልባት ሊረዱት ይችላሉ። እነዚህን ነገሮች እንዲረዱት ስለምፈልግ፣ በአካባቢያቸው የሚገኙ ሴቶችንም በትኩረት እንዲያዩ፣ እንዲረዱ ስለምፈልግ ወንዶችም ቢያነቡልኝ በጣም ደስተኛ ነኝ።
ቢቢሲ- ተደራሲዎችሽ ማን እንዲሆኑ ትፈልግያለሽ ካልኩባቸው አንዱ ምክንያት የመጽሐፍሽ መግቢያ ላይ የተጠቀምሽው ረዥም እንግሊዝኛ ነው። ይህ ደግሞ ገጸ ባህሪያቶቹም በንግግራቸው መካከል ሲጠቀሙበት ያስተዋልኩት አለ። ለምንድን ነው በአማርኛ ታሪኮች ውስጥ ረዣዥም እንግሊዝኛ መጠቀም የመረጥሽው?
ቤዛዊት- ጉራማይ እንዲሆን የፈለግኩት . . . እኩዬቼም፣ ጓደኞቼም፣ የሥራ ባልደረቦቼም፣ በአካባቢዬም ካሉ ጋር የምንግባባው እንደዚያ ስለሆነ ነው። ዘመኑን ለመመስል ሳይሆን ስናወራ እንደዚያ ነው የምንግባባው። ዘመኔን፣ እኔን የሚመስለኝን ነገር ለመግለጽ እንዳለ፣ እንድወረደ ብንቀመጥ ጥሩ ነው ብዬ ነው። ቋንቋ ደግሞ አገራችን ላይ አማርኛም፣ እንግሊዝኛም የምንገለገልበት ነው።
ስለዚህ የሚሰማንን ስሜት እንዳለ ሆኖ የሚገልጽልን ከሆነ ሥነ ጽሑፉን የሚያበላሻ አይመስለኝም። በእርግጥ 'አለማክበር' ነው ያሉ አሉ። ለእኔ ግን በትክክል ይወክለኛል፣ እኔንም መሰሎቼንም ይወክላል ብዬ ስላሰብኩ ነው እንዳለ ያስቀመጥኩት። . . . . በትክክል አሁን ያለነውን ወጣቶች፣ ዘመናችንን ይገልጻል ታሪካችንም እዚያ ውስጥ አለ ብዬ ስለማስብ ነው።
ቢቢሲ- በመጽሐፍሽ ውስጥ የሚገኙት ስድስት አጫጭር ታሪኮች ዋና ገጸ ባህሪያት በሙሉ ሴቶች ናቸው። ለምን?
ቤዛዊት- ሳድግ ብዙ የወንድ ደራሲያንን ሥራዎች እያነበብኩኝ ነው ያደግኩት። . . .ስለሴት ሲጻፍ ስለውበቷ ይጻፋል፤ ስለ አካላችን፣ ስለሳቅ በጣም የሚገርመኝ ነገር ብዙ ወንዶች ስለሴት ልጅ ሳቅ ይጽፋሉ። ወይንም ደግሞ ሕይወታቸው ውስጥ ገብተን ስለምንሰጣቸው ደስታ ይጽፋሉ፤ እንደ ማሙያነት። የሆነ የራሳችንን ሕይወት ይዘን የመጣን አይመስልም። በመጥፎ ነገር ቀርጸውናል እያልኩ አይደለም። በጣም በጥሩ መንገድ ጽፈውናል። ግን ደግሞ በትክክል እያንዳንዷን ያለፍንበትን መንገድ ያንን ለእነርሱ የምናሳያቸውን ሳቅ፣ ከዚያ ሳቅ ጀርባ ያለው እያንዳንዱ ጎርበጥባጣችን አልተጻፈም ብዬ ነው የማስበው። በደንብ አልተገለጽንም።
እና ምንም ሳናሰማምር፣ ሳናሸበርቅ መጻፍ አለብን። ያለፍንበትን እያንዳንዷን ነገር መሰፈር አለባት ብዬ ስለማስብ ለዚያም ነው ሴቶች ላይ በትኩረት ለመጻፍ የፈለግኩት። እና ደግሞ ሴቶች በደንብ የስሜት ሰዎች ነን ብዬ ነው የማስበው። እያንዳንዷን የሳቅም የደስታም ስሜት በጥልቀት በደንብ መረዳት የምንችል ፍጡር ነን ብዬ አስባለሁ።
ስለዚህ በመጽሐፌ ከተለያዩ ሴቶች አንጻር፤ ከተማም ካለችው፣ ገጠርም ከኖረችው፣ ታማሚም ከተባለችው፣ አንድ ተከብራ የምትኖር ባለትዳር እና አሁን ፈት የሆነች፣ ከተማረችው፣ ወጣት ከሆነችውም ከእነዚህ አንጻር የሴቶችን ህመም እና ስሜት ለመግለጽ ነው።
ቢቢሲ- ለአንቺ ሴትን ጥሩ አድርጎ የገለጸ ወንድ ደራሲ ማን ነው?
ቤዛዊት- ብዙ ጊዜ ስናገር ከአፌ የማይጠፋው አዳም ረታ ነው።. . . .አዳም ሴት ሆኖ የሚያውቅ ያህል በጣም ተረድቶኛል ብዬ ነው የማስበው።. . .አዳም የወንድን ወገን ብቻ ይዞ የሚጽፍ ደራሲ ነው ብዬ አላስብም። በዚያ ላይ ሴት ገጸ ባህሪያቶቹ የማውቃቸው ሰዎች ሁሉ ይመስሉኛል። እርሱ ከጻፋቸው ሴት ገጸ ባህሪያት እኔን የሚመስሉ ሴቶች አሉ። ከአዳም ውጪ በቅርቡ የተለያዩ ደራሲያን በጋራ ያሳተሙት ጉራማይሌ የሚል መጽሐፍ አለ። እዚያ ላይ ልዑል ዘወልደ የሚባል አንድ ልጅ ሁለት ሥራዎች አሉት. . . በጣም ወድጄ የማነብበው ጽሑፍ የእርሱን ነው። እርሱ ራሱ በደንብ ያውቀናል ብዬ አስባለሁ።
ቢቢሲ- መጽሐፍሽ ውስጥ ብዙ ጥቃት ብዙ መንገብገብ አይቻለሁ። ሴት ገጸ ባህሪያቶችሽ በአጠቃላይ አማራሪ ናቸው። ለሚደርስባቸው ነገር ሁሉ ተጠያቂ የሚያደርጉት ወንድ አያጡም። በተደጋጋሚ ተስፋ መቁረጥ እና ሞትን ሲመኙ እናያለን። እውነት በሴቶች ውስጥ የሚታይ ጥንካሬ የለም? ያ ጥቃት፣ በደል፣ መገፋት ብቻ ነው ለመጻፍ ገፊ ምክንያት የሆነሽ?
ቤዛዊት- ሴት ልጅ በጣም ጠንካራ እንደሆነች ነው የማስበው። ጽሑፌም ላይ ለማስረዳት የሞከርኩት ነገር በእነዚህ ሁሉ ነገሮች ውስጥ ጥንካሬ እና ተስፋ እንዳለ ነው።
ቀደም ሲል አንዳልኩት ስለሴት ሲጻፍ ደስታችን፣ ለሰው የምናጋባው ሕይወት፣ ሳቃችን፣ የሰውን ሕይወት ሙሉ የምናደርገው ክፍል በደንብ ተጽፎ አልፏል ብዬ አስባለሁ። ስለዚህ እኔ ምንድን ነው የምጽፈው ያልታየነው ምኑ ጋር ነው የሚለውን ነው።
እና ደግሞ ሁሉም የሚከሱት ወንድ አላቸው ላልከው፣ እንደምታውቀው ሁለት ፆታ ነው ያለው። እኛ ያለ ወንዶች፣ ወንዶች ያለ ሴቶች መኖር አንችልም። በዚህ መካከል ተጠላልፎ መኖር፣ በደል ይኖራል። ይህ ጉዳይ ለምን ርዕሰ ጉዳይ አንደሚሆን ይገርመኛል። ግንኙነት ውስጥ ከገባን እና አንዳችን ሌላኛችንን ከጎዳን የምንከሰው ሌላኛውን ወገን ነው።
መጽሐፌን በደንብ አይተኸው ከሆነ ወንዱን ጠላት [ቪለን] የማድረግ ሃሳብ የለኝም። ምክንያቱም አንድ ቦታ ክፉ የሚሆን ሰው ሌላ ቦታ ላይ በጣም ጥሩ ነው። ወንድን ክፉ የማድረግም፣ የመክሰስም ጉዳይ አይደለም። በአጭሩ ታሪኩን ከሴቶች አንጻር ሲነገር ምናልባት ሕይወታችን ላይ ስላሉት ወንዶች አንስተን ትንሽ ቆዝመን ይሆናል። በቃ ይኽው ነው።
ቢቢሲ- መጽሐፍሽን ሳነብ ያጣሁት ነገር ፍርርቅ ነው። እነዚህ የአጭር ልብ ወለድ ስብስቦች ተመሳሳይነት ይታይባቸዋል። በሴራ ደረጃ፣ በሕይወታቸው፣ በብሶታቸው ሁሉ ተመሳሳይነት ይታይባቸዋል።
ቤዛዊት- በእሱ ደረጃ ካየነው ልክ ነህ። አብዛኛው ታሪክ የሚነሳው ከአንድ ዓይነት ቦታ ላይ ነው። ስለ 'ቫራይቲ' ካወራህ ፌስቡክ ላይ የጻፍኳቸው ብዙ ታሪኮች አሉ። . . .እነርሱን ስብስብ አድርጌ ባሳትማቸው የተለያየ ታሪክ ይወጣቸው ነበር። እነዚህን ስድስቱን ግን አንድ ላይ ያደረግኩበት ምክንያት አንድ ዓይነት ሀሳብ፣ አንድ ዓይነት ፍሰት ስላላቸው ነው። ከአንድ ቦታ የሚነሳ ታሪክ ስላላቸው ነው። በዚህ የተነሳ እኔም ቫራይቲ አለው ብዬ አላምንም።
በተጨማሪ ደግሞ ገና ስለ ህመማችን ተወርቶ አላላቀም ብዬ ስላሰብኩ ነው። የመጀመሪያ ሥራዬ ላይ (የመሀል ልጅም) ትንሽ ሐዘን አለው፤ በዚያ መጽሐፍ እኔ ከነበረኝ ሕመም እና ቁስል ተነስቼ የጻፍኩት እና የዳንኩበት ነው። አሁን ደግሞ ከእኔ ባሻገር፣ የሌሎች ሴቶችን ታሪክ ስሰማ ደግሞ ይህንን መጽሐፍ ለእነርሱ ማስታወሻ እንዲሆን፣ እንዲድኑበት፣ ጩኽታቸን ይጻፍ በሚል የተጻፈ ነው። እስቲ መጀመሪያ ከሕመማችን እንዳን እና ወደ ሌሎች ታሪኮች እንሄዳለን።
ቢቢሲ- ኦሮምኛ ትችያለሽ?
ቤዛዊት- አይ መናገርም፣ መስማትም አልችልም።
ቢቢሲ- በመጽሐፍሽ ውስጥ የተሳሉት ሴት ገጸ ባህሪያት ግን ከአንድ ቦታ በላይ ኦሮምኛ ሲናገሩ አንብቤያለሁ።
ቤዛዊት - አዎ ሳስበው አንድ ቦታ ላይ ብቻ መቆም ጥሩ አልመሰለኝም። ሁላችንም በያለንበት ቦታ፣ ብሔርም፣ ቋንቋም ታሪክ አለን። እና አንድ የኦሮምኛ ተናጋሪ ስትሰማ፣ እኔ አቅሜ መጻፍም የምችለው በአማርኛ ቢሆንም፣ ውክልናዋን፣ ማንነቷን ሰጥቶ ለማለፍ የተደረገ ትንሽዬ ሙከራ ነው።
ቢቢሲ - ግን እኮ እነዚህ ኦሮምኛ ተናጋሪ ገጸ ባህሪያት ከወለጋ አካባቢ የመጡ እንደሆኑ የተጠቀሱ ይመስለኛል? ልክ ነኝ?
ቤዛዊት- ገጸ ባህሪያቱ የማውቃቸው ዓይነት ገጸ ባህሪያት አይደሉም። ታሪኮችን ስሰማ ሙሉ በሙሉ የእነርሱን ታሪክ ገልብጦ ከመጻፍ፣ ከማውቀው እውነታ ጋር አንዲያያዝ አድርጌ፣ የራሳቸውን ማንነት ለማሳየት የተጻፈ ሙከራ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ከርዕሱም እንደምንረዳው ሁሉንም ታሪክ ለማስተሳሰር ርዕሱ ኦሮምኛ ከሆነ፣ ከዚያ ደግሞ 'አገኘሁ የቀይ ሸጋ ላይ' ያለው አንድ ገጸ ባህሪ ደግሞ ከወለጋ የመጣ ስለሆነ፣ ያንን ታሪክ ስሰማ ለምን አላስተሳስረውም በሚል ነው። እና ደግሞ ታሪኮቹ የተያያዙ ነገሮች አሏቸው።
ቢቢሲ- ሃርካ ሂንኬኒኒ (Harka hin kennin) የሚለው ቃል በየታሪኮቹ ውስጥ እዚህም እዚያም እናገኘዋለን። በየታሪኮቹ ውስጥ እጅ አትስጪ ማለት የፈግሽው ለምንድን ነው?
ቢቢሲ- የአቡሽ ዘለቀ 'ፉላኒዬ' የሚለውን ዘፈን ስሰማ ነው ይህችኛዋ ቃል ጆሮዬ ላይ የገባችው። ከዚያም ጓደኛዬን ምን ማለት እንደሆነ ጠየኳት። ስሰማው ቃሉ አፍላይ ቆንጆ ነው። እና ጓደኛዬ 'እጅ አትስጪ' ማለት እንደሆነ ስትነግረኝ በሰዓቱ ይህንን መጽሐፍም እያዘጋጀሁ ስለነበር ሐዘን ስጽፍ፣ ሐዘን ላይ ብቻ እንዲቆዩ፣ ስለተስፋ መቁረጥ ሳወራ፣ ተስፋ መቁረጥ ላይ ብቻ እንዲሰነብቱ አልፈለኩም። ነገ ቀኑ ሲነጋ፣ ከማለዳው ጋር አብረን ተስፋ ይዘን እንነቃለን። እና ይህ ርዕስ ለዚህ ጥሩ መግለጫ ይሆናል ብዬ ስላሰብኩ ነው ሃርካ ሂንኬኒኒን የተጠቀምኩት ማለት ነው። ከዚህ በፊት እንዳልኩት መጽሐፉ ላይ ደግሞ ሁሉንም የሚያስተሳስረው ነገር አለ። . . .ሁሉም በያሉበት ብሶት ቢኖራቸውም ቃሉ ግን ማጽናኛ ሆኖ አገልግሏቸዋል።