ቻይና የዶናልድ ትራምፕን ታሪፍ ለመቋቋም ምን ዓይነት እርምጃዎችን ልትወስድ ትችላለች?

የዓለማችን ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆኑት አሜሪካ እና ቻይና በንግድ ጦርነት ውስጥ ናቸው።

ዶናልድ ትራምፕ ቻይና ወደ አሜሪካ የምትልካቸው ምርቶች ላይ የ245 በመቶ ታሪፍ ጥለዋል።

ቻይና በምላሹ ከአሜሪካ የሚገቡ ምርቶች ላይ የ125 በመቶ ታሪፍ ጥላላች።

ሸማቾች፣ የንግድ ተቋማት እና ገበያዎች ዓለም አቀፍ ግሽበት ይከሰታል በሚል ስጋት ውስጥ ናቸው።

የፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ መንግሥት ለውይይት ክፍት መሆኑን በተደጋጋሚ ይናገራል።

ይኹን እንጂ አስፈላጊ ከሆነ አሜሪካንን "እስከ መጨረሻው ድረስ ለመጋፈጥ" ዝግጁ መሆኑንም አስጠንቅቀዋል።

ቻይና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ታሪፎችን ለመመከት ያሏት አማራጮች ምንድን ናቸው?

የሚያደርስባትን ጫና ተቋቁሞ መቀጠል

ቻይና የዓለማችን ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ አገር ናት። ስለዚህ ከትንንሽ አገራት በተሻለ የተጣለባትን ታሪፍ የመቋቋም አቅሙ አላት።

ከአንድ ቢሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ቻይና፣ ወደ አሜሪካ በምትልካቸው ምርቶች ላይ የተጣለው ታሪፍ የሚያስከትለውን የዋጋ ጭማሪ ለመመከት ሰፊ የአገር ውስጥ ገበያዋን ልትጠቀም ትችላለች።

በእርግጥ ቤይጂንግ አሁንም ዜጎቿ ገንዘባቸውን እንዲያወጡ እና እንዲሸምቱ ማድረግ ላይ ብዙ መሥራት ይጠበቅባታል።

ነገር ግን በቤት እቃዎች ላይ እንዲሁም ጡረተኞች ወደ ተለያዩ ስፍራዎች ሲንቀሳቀሱ የሚጠቀሙት የባቡር ቲኬት ላይ የሚኖሩ ድጎማዎች ላይ ለውጥ ይመጣሉ ተብሎ ይታመናል።

የትራምፕ ታሪፍ ለቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የአገር ውስጥ ሸማቾች አቅምን አሟጦ እንዲጠቀም የዕድል በር ከፍቶለታል።

ፓርቲው በቻይና የሕዝብ ተቃውሞ ይገጥመኛል ብሎ የሚሰጋ አይደለም። መሪዎችን በመራጮች የድምጽ ውሳኔ ወንበር ላይ የሚያስቀምጥ ምርጫም በቅርብ አይኖርም።

የምጣኔ ሀብቱ በዶናልድ ትረምፕ ታሪፍ የተነሳ የሚገባበት ቅርቃር አገራቸው በእድገት መሰላል ላይ ስትወጣ ብቻ ለተመለከቱ ወጣት ቻይናውያን ግርታን ሊፈጥር ይችላል።

ፓርቲው ግን በመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን በአገሪቱ ምርቶች ላይ የተጣለውን ታሪፍ ለመመከት የብሔራዊ ስሜትን እንደ ደጀን አድርጎ ለመጠቀም ሲሞክር ተስተውሏል።

ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ምናልባት ትንሽ ስጋት ሽው ሊላቸው ቢችልም፣ እስካሁን ያለው በራስ መተማመን እና የአልበገር ባይነት ስሜት ነው።

አንድ የአገሪቱ ባለሥልጣን ሕዝቡን "ሰማይ አይደፋብንም" ሲሉ ለማረጋጋት ሞክረዋል።

በመጪው ዘመን ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ

ቻይና ሁሌም የምትታወቀው የዓለም ምርቶች ፋብሪካ በመባል ነው። ነገር ግን እጅግ የላቀ ደረጃ ላይ ለመድረስ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ታፈስሳለች።

በአሁኑ ወቅት ደግሞ ከአሜሪካ ጋር የቴክኖሎጂ የበላይነት ለመያዝ ፉክክር ውስጥ ናት።

በአገር ውስጥ በሚበለጽጉ ቴክኖሎጂዎች ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋያቸውን የሚያፈሱሰት ቻይና እና አሜሪካ ከታዳሽ ምርቶች እስከ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ድረስ ይፎካከራሉ።

በቅርቡ ቤይጂንግ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ የሚደረገውን ፈጠራ ለመደገፍ በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ውስጥ ከአንድ ትሪሊየን ዶላር በላይ ለማውጣት ማቀዷን አስታውቃለች።

የአሜሪካ ኩባንያዎች የአቅርቦት ሰንሰለታቸውን ከቻይና ለማራቅ ሞክረዋል።

ነገር ግን ተመሳሳይ ደረጃ ያለው መሠረተ ልማት እና የሰለጠነ የሰው ኃይል በሌላ አገር ለማግኘት ተቸግረዋል።

አሜሪካ ከአሁን በኋላ የቻይና ትልቋ የወጭ ንግድ ገበያ አይደለችም።

ይህ ስፍራ አሁን በደቡብ ምሥራቅ እስያ ተተክቷል።

በእርግጥ ቻይና በ2023 ለ60 አገራት ትልቋ የንግድ አጋር ነበረች።

ይህ ማለት ግን የዓለም ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት አሜሪካ ለቻይና ወሳኝ የንግድ አጋር አይደለችም ማለት አይደለም።

ነገር ግን ዋሽንግተን ቻይናን ወደ ዳር መግፋት ቀላል አይሆንላትም።

ቻይና የትራምፕን ስስ ጎን አግኝታዋለች

ትራምፕ በሚያዝያ ወር መጀመሪያ ላይ በአገራት ላይ ታሪፍ መጣላቸውን ተከትሎ የአውሮፓ እና አሜሪካ አክሲዮን እና የቦንድ ገበያዎች እያሽቆለቆሉ ሄደዋል።

ዶናልድ ትራምፕ ምንም እንኳን ታሪፉ የተዛባውን የንግድ ሚዛን ለማስተካከል የሚረዳ "መድኃኒት" ነው ቢሉትም የሆነው ግን በተቃራኒው ነው።

ይህንን ተከትሎም ዶናልድ ትራምፕ ታሪፎቹ ለ90 ቀናት ተግባራዊ ከመሆን እንዲዘገዩ ወስነዋል።

ትራምፕ ከቻይና ጋር የገቡበትን የንግድ ውዝግብ ለማርገብ እንደሚፈልጉ ፍንጭ ሰጥተው በቻይና ምርቶች ላይ የሚጣለው ታሪፍ "በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል፤ ነገር ግን ዜሮ አይሆንም" ብለዋል።

ተንታኞች ቤይጂንግ አሁን ዶናልድ ትራምፕን የቦንድ ገበያው እንደሚረብሻቸው አውቃለች ይላሉ።

ቻይና 700 ቢሊዮን ዶላር የአሜሪካን መንግሥት ቦንድ ይዛለች።

አንዳንዶች ይህ ለቤይጂንግ ጥቅም ይሰጣል ብለው ይከራከራሉ። የቻይና መገናኛ ብዙኃን የአሜሪካ ቦንድ ግዥን እንደ "መሳሪያ" ልትጠቀምበት እንደምትችል ይናገራሉ።

ነገር ግን ቻይና ከእንደዚህ ዓይነት ተግባር ምንም ጉዳት ሳይደርስባት እንደማትወጣ ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ።

ይልቁንም የቤጂንግ ኢንቨስትመንቶች በቦንድ ገበያ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ያስከትላሉ እንዲሁም የቻይና መገበያያ ገንዘብም እንዳይረጋጋ ያደርጋል ሲሉ ምክራቸውን ሰጥተዋል።

ቻይና የአሜሪካ መንግሥት ቦንድ ላይ ጫና ማድረግ የምትችለው "እንደ ፋይናንስ መሳሪያ ሳይሆን እንደ መደራደሪያነት በመያዝ ነው" ሲሉም የተሻለውን አማራጭ ጠቁመዋል።

ብርቅዬ ማዕድናትን መያዝ

ቻይና ለተሻሻሉ የቴክኖሎጂ ምርቶች ማምረቻ የሚያገለግሉትን ብርቅዬ ማዕድናትን በማውጣት እና በማጣራት ቀዳሚ መሆኗ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር በገባችበት የንግድ ጦርነት የበላይነት ሊሰጣት ይችላል።

ቻይና የእነዚህ ብርቅዬ ማዕድናት ከፍተኛ መጠን ያለው ክምችት አላት።

ለምሳሌ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እና በነፋስ ተርባይኖች ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውለው ዲስፕሮሲየም እና በጄት ሞተሮች ውስጥ ሙቀትን ለመቋቋም የሚያገለግለው ያትሪየም ተጠቃሽ ናቸው።

ቤይጂንግ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ቺፖችን ለመሥራት አስፈላጊ የሆኑትን ጨምሮ ሰባት ብርቅዬ ማዕድናትን ወደ አሜሪካ መላክን በመገደብ ትራምፕ ለጣሉት ታሪፍ አጸፋውን መልሳለች።

በዓለም አቀፍ ኢነርጂ ኤጀንሲ ግምት መሠረት ቻይና 61 በመቶ የሚሆኑትን ብርቅዬ ማዕድናን በማውጣት እና 92 በመቶውን ደግሞ በማጣራት በዓለም ላይ ጉልህ ሚና አላት።

አውስትራሊያ፣ ጃፓን እና ቬትናም ብርቅዬ ማዕድናትን ማውጣት የጀመሩ ቢሆንም፣ ከቻይና የአቅርቦት ሰንሰለት ለመላቀቅ ዓመታትን ይወስድባቸዋል።

በአውሮፓውያኑ 2024 ቻይና ለተለያዩ የማምረቻ ሂደቶች ወሳኝ የሆነውን ብርቅዬ ማዕድን ወደ ውጭ መላክ አግዳለች።

በዚህ የቻይና እርምጃ የተደናገጡ አገራት ለመግዛት በሚያደርጉት መራኮት ውስጥ የማዕድናቱ ዋጋ አሻቅቧል።

በተመሳሳይ ቻይና ብርቅዬ ማዕድናት ላይ የወሰደችው የቅርብ ጊዜ እርምጃ ከኤሌክትሪክ ተሸከርካሪ አምራቾች እስከ መከላከያ ተቋማት ድረስ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል።

ይህ እርምጃም "በአሜሪካ የመከላከያ ኢንዱስትሪ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከፍተኛ ይሆናል" ያሉት የጂንጀር ኢንተርናሽናል ትሬድ ኤንድ ኢንቨስትመንት ዳይሬክተሩ ቶማስ ክሩመር ናቸው።