ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አገራት ከአሜሪካ ጋር በሚያደርጉት የንግድ ድርድር ዙሪያ ቻይና ማስጠንቀቂያ ሰጠች
ቻይና ዶናልድ ትራምፕ የጣሉትን ታሪፍ ተከትሎ አገራት ከአሜሪካ ጋር በሚያደርጉት የንግድ ድርድር ወቅት አሜሪካን የምትፈልገውን በማድረግ ለማስደሰት እንዳይሞክሩ አስጠነቀቀች።
የቻይና ንግድ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ማስጠንቀቂያውን የሰጡት ዋሺንግተን መንግሥታት ወደ አሜሪካ የሚልኳቸው ምርቶች ከቀረጥ ነጻ እንዲሆኑላቸው ከቤይጂንግ ጋር በሚያደርጉት የንግድ ልውውጥ ላይ ጫና ለመፍጠር ማቀዷ ከተሰማ በኋላ ነው።
የትራምፕ አስተዳደር ከንግድ አጋሮች ጋር ታሪፍን በተመለከት ንግግር መጀመሩ የተገለፀ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት የጃፓን ልዑካን ቡድን ዋሺንግተንን የጎበኙ ሲሆን፣ በዚህ ሳምንት ደግሞ ደቡብ ኮርያ ለመወያየት ቀጠሮ ይዛለች።
ትራምፕ በጥር ወር ሥልጣናቸውን ከተረከቡ በኋላ ከቻይና የሚገቡ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ታሪፍ የጣሉ ሲሆን ሌሎች በርካታ የዓለም አገራትም ታሪፍ ተጥሎባቸዋል።
የቻይና የንግድ ሚኒስትር ቃል አቀባይ "ለማስደሰት የሚደረግ ጥረት ሠላምን አያመጣም፤ እንዲሁም ማመቻመች ክብርን አያቀዳጅም" ብለዋል።
"ቻይና ሁሉም አካላት ከፍትሃዊነት ጎን መቆም አንዳለባቸው ታምናለች. . . እንዲሁም ዓለም አቀፍ የምጣኔ ሀብት እና የንግድ ሕጎች እንዲሁም የአገራት የንግድ ሥርዓትን መከላከል አለባቸው።"
ባለፈው ሳምንት ዎል ስትሪት ጆርናል አሜሪካ ታሪፍን በተመለከተ ከአገራት ጋር በምታደርገው ድርድር ከቻይና ጋር በሚኖራቸው ንግድ ላይ አዲስ ገደብ በመጣል ጫና ለማድረግ እንደምትፈልግ ዘግቦ ነበር።
ቢቢሲ የአሜሪካ ግምጃ ቤት እንዲሁም ንግድ ሚኒስትር ተወካዮችን ምላሽ ለማግኘት ሞክሮ የነበረ ቢሆንም አልተሳካም።
በንግድ ጉዳዮች ላይ የሚሠራው ሞኔክስ ግሩፕ ባልደረባ የሆኑት ጄስፐር ኮል "ቁጥሮችን የምንመለከት ከሆነ የጃፓን 20 በመቶ ትርፋማነት የሚመጣው ከአሜሪካ ነው፤ 15 በመቶው ደግሞ ከቻይና ነው" ብለዋል።
ስለዚህም "ጃፓን በእርግጠኝነት ከአሜሪካ እና ከቻይና ልትመርጥ አትችልም።"
ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣናቸውን ከተረከቡ በኋላ ታሪፍን በተመለከተ የተለያዩ ውዝግቦች ተቀስቅሰዋል።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በገቢ ምርቶች ላይ የሚጣል ግብር ሸማቾች በአሜሪካ የተመረቱ ምርቶችን እንዲገዙ ያበረታታል፤ የሚሰበሰበው ታክስ ይጨምራል እንዲሁም ወደ አሜሪካ ትልልቅ ኢንቨስትመንቶችን ይስባል ሲሉ ይከራከራሉ።
ተቺዎች ግን ግዙፍ አምራቾችን ወደ አሜሪካ ለመሳብ እንዲህ አንደሚታሰበው ቀላል አይደለም ይላሉ።
ምናልባት አስርት ዓመታትን ሊወስድ ስለሚችል በመካከል የአገሪቱ ኢኮኖሚ ፈተና ውስጥ ይገባል ሲሉ የአሜሪካ መንግሥት ውሳኔውን አንዲያጤን ምክራቸውን ይለግሳሉ።
ትራምፕ በአገራት ላይ ታሪፉን ይፋ ካደረጉ በኋላ ውሳኔያቸው ተፈጻሚ የሚሆንበትን ቀን አራዝመውታል።
ትራምፕ ከቻይና የሚገቡ ምርቶች ላይ 145 በመቶ ታሪፍ ጥለዋል።
ሌሎች የዓለም አገራትም እስከ ሐምሌ ወር ድረስ አነስተኛ ነው የተባለው 10 በመቶ ታሪፍ ተጥሎባቸዋል።
የትራምፕ አስተዳደር ባለፈው ሳምንት አዲስ የሚጣሉ ታሪፎች ሲጨመሩ ከቻይና የሚገቡ ምርቶች ላይ የሚጣለው ታሪፍ እስከ 245 በመቶ እንደሚደርስ ተናግሯል።
ዶናልድ ትራምፕ በአገራት ላይ ታሪፍ መጣላቸውን ካስታወቁ በኋላ ከ70 አገራት በላይ ለድርድር ጥያቄ ማቅረባቸው ተገልጿል።