ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለምርጫ ቅስቀሳ ከጋዳፊ ገንዘብ የተቀበሉት የቀድሞው የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ከሦስት ሳምንት እስር በኋላ ተለቀቁ
የአምስት ዓመት እስራት ተፈርዶባቸው የነበረው የቀድሞው የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ሳርኮዚ ከሦስት ሳምንት እስራት በኋላ ተለቀቁ።
ሳርኮዚ ለምርጫ ቅስቀሳ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕገ ወጥ ገንዘብ ከቀድሞው የሊቢያ መሪ ኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊ በመቀበል ጥፋተኛ ተብለው የአምስት ዓመት እስራት ተፈርዶባቸው ነበር።
ሳርኮዚ ከፈረንሳይ እንዳይወጡ እገዳ ተጥሎባቸው ከእስር የተለቀቁ ሲሆን፤ ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግባቸውም ይሆናል። ይግባኝ የጠየቁት ሳርኮዚ በ2026 በድጋሚ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ።
የ70 ዓመቱ ሳርኮዚ እአአ በ2007 ለተካሄደ ምርጫ ከጋዳፊ ገንዘብ መቀበላቸው ተገልጿል።
ከእስር ከተለቀቁ በኋላ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው "ሙሉ አቅሜን ተጠቅሜ ንጹህ መሆኔ እንዲረጋገጥ አደርጋለሁ። እውነት ታሸንፋለች. . . ታሪኩ ገና አላከተመም" ብለዋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳት እንዲለቀቁ ፍርድ ቤት ከወሰነ በኋላ መኪናቸው ከላ ሳንቴ ማረሚያ ቤት ሲወጣ ታይቷል።
ከሳርኮዚ ጠበቆች አንዱ የሆኑት ክሪስቶፊ ኢንግሪን ደንበኛቸው መለቀቃቸውን "ትልቅ እርምጃ" ሲሉ ገልጸውታል።
ከእስር እንዲለቀቁ ውሳኔ ሲሰጥ ከተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች መካከል አንዱ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ከየትኛውም ምስክር ወይም የፍትሕ ቢሮ ሠራተኛ ጋር እንዳይገኙ መከልከላቸው ነው።
ሳርኮዚ በእስር ላይ ሳሉ የፍትሕ ሚኒስትር ዤራልድ ዳርማኒን ጎብኝተዋቸዋል። ጉብኝታቸው ከፍተኛ ቁጣ ያስነሳ ሲሆን፤ 30 ጠበቆች ቅሬታቸውን በይፋ ገልጸዋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት የእስር ቆይታቸውን "ስቃይ የበዛበት" እና "ክፉ ሕልም" ሲሉ ገልጸዋል።
"ጋዳፊን ገንዘብ የሚያስጠይቅ የእብደት ሐሳብ አልነበረኝም። ያላደረግኩትን አድርጌያለሁ አልልም" ያሉት ሳርኮዚ የእስር ቆይታቸውን "ቀላል" ያደረጉላቸውን የማረሚያ ቤት ሠራተኞች "ሰብአዊነት አሳይታችሁኛል" ሲሉ አመስግነዋል።
ሙዚቀኛ እና ሞዴል የሆነችው ባለቤታቸው ካርላ ብሩኒ-ሳርኮዚ እንዲሁም ሁለት ልጆቻቸውም ፍርድ ቤት ተገኝተው ድጋፍ ሰጥተዋቸዋል።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ የታሰሩ የመጀመሪያው የቀድሞ የፈረንሳይ መሪ ናቸው።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከናዚ ጋር በመተባበር የፈረንሳይ ወታደራዊ መሪ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ፊሊፔ ፔቴን በአገር ክህደት ተከሰው መታሰራቸው ይታወሳል።
ሳርኮዚ በአንድ ክፍል ውስጥ ተነጥለው እንዲታሰሩ ውሳኔ ተላልፎ ነበር። ክፍሉ መጸዳጃ፣ ቴሌቭዥን፣ የምግብ ማቀዝቀዣ እና የክፍል ማሞቂያ አለው። ለቴሌቭዥኑ በየወሩ 12 ዶላር ይከፍሉም ነበር።
ቤተሰቦቻቸው እንዲጎበኟቸው እንዲሁም የስልክ እና የጽሑፍ መልዕክት እንዲቀበሉም ተፈቅዶላቸዋል።
በቀን ለአንድ ሰዓት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ተፈቅዶላቸዋል። ሁለት ጠባቂዎች ተመድበውላቸውም ነበር።
እአአ ከ2007 እስከ 2012 ፈረንሳይን የመሩት ሳርኮዚ ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ በወንጀሎች ክስ ምክንያት ከተወሰነ ርቀት ውጪ ሲንቀሳቀሱ ለፖሊስ ጥቆማ የሚሰጥ ኤሌክትሮኒክ የእግር ሰንሰለት እንዲያደርጉ ተወስኖ ነበር።