ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አንድ ቤተሰብ ለ100 ዓመታት በጀርመን የቆዩ ቅርሶችን ለኢትዮጵያ መለሰ
ከአንድ መቶ ዓመታት በላይ በአንድ ጀርመናዊ ቤተሰብ ተይዘው የነበሩ አስራ ሁለት የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶች በይፋ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ተደረገ።
አሁን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለኢትዮጵያ ጥናት ተቋም የተሰጡት እነዚህን ቅርሶችን በመጀመሪያ ሰብስበው በባለቤትነት ይዘዋቸው የነበሩት በ1920ዎቹ በኢትዮጵያ የጀርመን መንግሥ መልዕክተኛ የነበሩት ፍራንዝ ዌይስ እና በባለቤታቸው ሄድዊግ ነበሩ።
የተመለሱት የቅርስ ስብስቦች ዘውዶች፣ ጋሻዎች እና ሥዕሎች የተካተቱባቸው ሲሆኑ፤ ለኢትዮጵያ ባሕላዊ እና ታሪካዊ ጠቀሜታ ያላቸው ናቸው።
"ቅርሶቹ አሁንም ድረስ በኢትዮጵያ እና በጀርመን መካከል ያለውን የወዳጅነት የሚያሳዩ ምልክቶች ሆነው አሁንም ይቀጥላሉ" ሲሉ በኢትዮጵያ የጀርመን መልዕክተኛ የሆኑት ፈርዲናንድ ቮን ዌይህ ተናግረዋል።
እነዚህን ቅርሶች ለኢትዮጵያ የመለሱት አባታቸው በኢትዮጵያ የጀርመን ዲፕሎማት በነበሩበት ጊዜ የተወለዱት ፕሮፌሰር ራሞን ዌይስ ናቸው።
ቅርሶቹ የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ በታደሙበት ሥነ ሥርዓት ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለኢትዮጵያ ጥናት ነው የተሰጡት።
ፕሮፌሰር ራሞን ቤተሰባቸው እነዚህን ቅርሶች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ የፈለገው "ውበታቸውን ለሕዝቡ ለማሳየት እና ከአባቴ ሕይወት ጋር ያላቸውን የባህል እና የታሪክ ቁርኝትን ለመጠበቅ ነው" ብለዋል።
የተመለሱት ቅርሶች በስጦታ የተገኙ ወይም የተገዙ መሆናቸውን ቤተሰቡ አሳውቋል።
የቱሪዝም ሚኒስትሯ ቅርሶቹን የመለሰው ቤተሰብ "ቅርሶቹን በጥንቃቄ ጠብቆ በማቆየት፣ ለመጡበት አገር መልሰው በመስጠት ለኢትዮጵያ ያለውን ፍቅር" አሳይቷል በማለት አድናቆታቸውን ገልጸውላቸዋል።
የቅርሶቹን መመለስ የኢትዮጵያን ባሕላዊ ቅርሶች ከመጠበቅ አንጻር ወሳኝ ምዕራፍ በማለት፣ ቅርሶቹ በቅርቡ ለምርምር እና ለትምህርታዊ ጥናት ለሕዝብ ክፍት እንደሚሆኑም ሚኒስትሯ አመልክተዋል።
በተጨማሪም "በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ግለሰቦች እና ተቋማት እጅ ውስጥ የሚገኙ ጥንታዊ ቅርሶችን ወደ ኢትዮጵያ ለማስመለስ የሚደረገው ጥረት ይቀጥላል" ሲሉም ሰላማዊት ካሳ ተናግረዋል።
በቅኝ ግዛት ዘመን በሺዎች የሚቆጠሩ ባህላዊ እና ታሪካዊ ቅርሶች ከአፍሪካ አገራት ተዘርፈው ተወስደዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተዘረፉባቸው ቅርሶች እንዲመለሱላቸው ጥሪ እያቀረቡ ካሉ አገራት መካከል የተወሰኑት የተሳካላቸው ሲሆን፣ አንዳንድ ቅርሶችንም በውሰት ብቻ ለማግኘት የቻሉ አሉ።
"ጨለማውን የቅኝ ግዛት ታሪክ" ለመካስ በሚል በአውሮፓውያኑ 2022 ጀርመን ከነሐስ የተሠሩ ጥንታዊ ቅርሶችን ለናይጄሪያ በመመለስ የመጀመሪያዋ አገር ሆናለች።