ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በስዊዲን የ113 ዓመት ዕድሜ ያላት ቤተ ክርስቲያን ሳትፈርስ ተነቅላ ወደ ሌላ ቦታ ልትወሰድ ነው
በስዊዲን የመሬት መሰንጠቅ አደጋ የተጋረጠበት 113 ዓመት ዕድሜ ያለው ታሪካዊ ቤተክርስቲያን ሙሉ በሙሉ ወደ ሌላ ቦታ የማዘዋወር ሥራ ተጀምሯል።
በአውሮፓውያኑ 1912 ሙሉ በሙሉ ከእንጨት የተገነባው ግዙፍ ቤተክርስቲያን በዝግታ ማንቀሳቀስ በሚያስችል ተሽከርካሪ ላይ ተጭኖ አዲስ ወደተዘጋጀለት የከተማዋ መሀል መሄድ ይጀምራል።
በሰዓት 500 ሜትር የሚጓዘው ይህ ተሽከርካሪ ጥንታዊቷን ቤተክርስቲያን ከታቀደላት ስፍራ ለማድረስ ሁለት ቀናትን ይወስዳል ተብሎ ይጠበቃል።
የድሮው የከተማ ማዕከል በአካባቢው ይካሄድ በነበረ የማዕድን ማውጣት ሥራ ምክንያት መሬቱ የመሰንጠቅ አደጋ አጋጥሞታል ተብሏል።
ከአርክቲክ ክበብ በስተሰሜን 145 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ በምትገኘው ኪሩና ውስጥ ያሉ ሕንፃዎችን ወደ ሌላ አካባቢ ለማዛወር የታቀደ ሲሆን፣ የቤተክርስቲያኒቷ ተነቅላ ወደ ሌላ አካባቢ መወሰድ አስደናቂም ተምሳሌታዊም ነው ተብሏል።
በባህል ባለሙያዋ ሶፊያ ላገርሎፍ ማቴት "በመጨረሻም፤ በቃ እንውሰደው አልን፤ ለብዙ ዓመታት ጠበቅን" ብላለች።
ቤተክርስቲያኒቷን ነቅሎ ወደ አዲስ ስፍራ የማጓጓዝ ኃላፊነትን የተረከበው የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ስቴፋን ሆምብላድ ጆንሰን "በጣም ተዘጋጅተናል" ብሏል።
"ይህ ታሪካዊ ክስተት ነው፤ በጣም ትልቅ እና ውስብስብ ሥራ ነው፤ መሳሳት አንችልም ነገር ግን ለሁሉም ነገር ተዘጋጅተናል።"
እርጋታው እና በራስ መተማመኑ ለዓመታት ማቀዳቸውን ያሳያል።
በአውሮፓውያኑ 2010ቹ አጋማሽ፣ በኪሩና የነበሩ ሌሎች ሕንፃዎች ወደ ሌላ አካባቢ ተዘዋውረዋል።
አብዛኛዎቹ ፈርሰው እንደገና ተገንብተዋል፣ ነገር ግን አንዳንድ ሕንጻዎች ምንም ሳይሆኑ ተንቀሳቅሰዋል።
ከእነዚህም መካከል ሦስት ጥንታዊ የእንጨት ቤቶች እና የማዕድን ማውጫ ሥራ አስኪያጁ የቀድሞ ቤት ለሦስት ተከፍሎ እንዲንቀሳቀስ ተደርጓል።
በአሮጌው ማዘጋጃ ቤት ጣሪያ ላይ ያለው የሰዓት ማማ እንዲሁ ተነስቶ አሁን ከአዲሱ ማዘጋጃ ቤት አጠገብ እንዲቀመጥ ተደርጓል።
በስዊድን ሕግ መሠረት የማዕድን ቁፋሮ በሕንፃዎች ስር ሊከናወን አይችልም።
የኪሩና ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሮበርት ኢሊታሎ "ሰዎች በመሬት ስንጥቃት ውስጥ ሊወድቁ የሚችሉበት ምንም ዓይነት ስጋት የለም። ነገር ግን ስንጥቆች ውሎ አድሮ የውሃን፣ የመብራት እና የፍሳሽ አቅርቦትን ያስተጓጉላሉ። መሠረተ ልማቱ ከመበላሸቱ በፊት ሰዎች መነሳት አለባቸው።"
የብረት ማዕድን የሚያወጣው እንዲሁም በኪሩና ትልቁ ቀጣሪ የሆነው ኤልኬኤቢ 1 ቢሊየን ዶላር ይፈጃል የተባለውን ነዋሪዎችን እና ሕንጻን ወደ ሌላ ቦታ የማዘዋወር ወጪን ይሸፍናል።
የኪሩና ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን 35 ሜትር ከፍታ፣ 40 ሜትር ስፋት እና 672 ቶን ክብደት አለው።
ሕንጻው እአአ ከ1950 በፊት የተገነባ ሲሆን በአንድ ወቅት የስዊዲን ውብ ኪነ ሕንጻ ተብሎ ተመርጧል።
እንዲህ ያለውን ትልቅ ሕንፃ ወደ ሌላ ስፍራ ማዛወር ያልተለመደ ተግባር ነው።
ነገር ግን መሐንዲሶች ከማፍረስ ይልቅ በብረት ምሰሶዎች በመደገፍ እና በዝግታ የሚንቀሳቀሱ ማጓጓዣዎችን በመጠቀም እየገፉ መውሰድን መርጠዋል።
የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ጆንሰን "ትልቁ ፈተና መንገዱን ለዚህ ሰፊ ሕንፃ ማዘጋጀት ነበር" ብሏል።።
መንገዱን "ወደ 24 ሜትሮች (79 ጫማ) አስፍተነዋል። በመንገዱ ላይ አምፖሎችን፣ የትራፊክ መብራቶችን እና እንዲፈርስ እቅድ ተይዞለት የነበረውን ድልድይ አንስተናል።"
ቤተክርስትያኑን በማጓጓዝ ሂደት በጣም አሳሳቢ ከሆኑት ጉዳዮች መካከል በውስጡ የያዛቸውን ሀብቶች፣ በተለይም የስዊድን ንጉሣዊ ቤተሰብ አባል በሆነው በልዑል ኢዩገን የተሠራውን ሥዕል ሳይጎዳ እንዲደርስ ማድረግ ነው።
ሚስተር ጆንሰን "ዝም ብለህ አንጠልጥለህ የምትወስደው በመንጠቆ ላይ የተንጠለጠለ ነገር አይደለም። በግድግዳው ላይ የተጣበቀ በመሆኑ ያለምንም ጉዳት ማንሳት አስቸጋሪ ነው። ስለዚህ በማጓጓዝ ሂደቱ ሙሉ በሙሉ ተሸፍኖ እና እንዳይዋዥቅ ተደርጎ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ እንዳለ ይቆያል፤ እሱ ብቻ ሳይሆን 1,000 ቱቦዎች ያሉት ኦርጋን እንዲሁ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ እንዳለ ይጓጓዛል።"
ለአካባቢው ነዋሪዎች እርምጃው ከምህንድስና ብቃት የበለጠ ስሜት የሚነካ ውሳኔ ነው።
ሶፊያ ላገርሎፍ ማትታ "ቤተክርስቲያኒቷ ለብዙ ትውልዶች እንደ መንፈሳዊ ቦታ እና የማኅበረሰብ መሰብሰቢያ ቦታ ሆና አገልግላለች" ስትል በልጅነቷ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ቤተክርስቲያኒቷ ከአያቷ ጋር የመጣችበትን ጊዜ ታስታውሳለች።
"እርምጃው ያሉንን የደስታ እና የሐዘን ትውስታዎች ዳግም እንዲሰማን አድርጓል። እናም አሁን እነዚያን ትውስታዎች ከእኛ ጋር ይዘን ወደ አዲሱ ስፍራ እንሄዳለን።"
የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ስቴፋን ሆምብላድ ጆንሰን፣ የቤተክርስቲያኒቷ የመዘምራን ቡድን አባል በመሆን ያሳለፈውን ጊዜ በማስታወስ ስሜቱን ይጋራል።
"ይህ ለእኔ ልዩ ሥራ ነው" ይላል።
"ቤተክርስቲያኒቱ ለከተማዋ በኤልኬኤቢ የተገነባችው ከ100 ዓመታት በፊት ነው። አሁን ወደ አዲስ ከተማ ወስደነዋል። ሌላ መንገድ ሊኖር አይችልም።"
የቤተክርስቲያኒቱ ቄስ የሆኑት ሌና ቲጃርንበርግ ወቅቱ ተጨማሪ ትርጉም አለው።
"ቤተክርስቲያኒቷ የምትገኝበትን ቦታ እየለቀቀች ነው" ይላሉ።
"ወደ ሌላ ቦታ መዘዋወር እንዳለበት ሁሉም ሰው ያውቃል። የምንኖረው በማዕድን ማውጫ አካባቢ ኑሮውን በማዕድን ማውጣት ላይ ባደረገ ማኅበረሰብ መካከል ነው።
"ቤተክርስቲያኒቷን ከእኛ ጋር ወደ አዲሱ የከተማው መሀል በመውሰዳችን ደስተኛ ነኝ። ነገር ግን ቤተክርስቲያኒቷ ከተመሠረተችበት ቦታ ላይ ስትነሳ በማየቴ አዝኛለሁ።"
የኪሩና ቤተክርስቲያን ግዙፍ ሕንጻዎች ፈቀቅ ማለት ሲጀምሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች፣ ጎብኚዎች የስዊድን ንጉሥ ካርል ጉስታፍን ጨምሮ በመንገዱ ግራ እና ቀኝ በመሆን ይመለከታሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የስዊድን ቴሌቪዥን እንዲሁ ይህንን ታሪካዊ ክስተት ለውጥን ሲቋቋም ብቻ ሳይሆን ከለውጥ ጋር አብሮ ሲሄድ በታሪክ ለማስቀረት "አዝጋሚውን ጉዞ" በቀጥታ ያሠራጫል።