ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አንዳንድ እውነታዎች ከጂቡቲ ተነስታ ባሕር ዳር ለመድረስ ለወራት በጉዞ ላይ ስላለችው 'ጣና ነሽ 2'
ከጂቡቲ ወደብ ተነስታ የየብስ ጉዞ ከጀመረች ከሁለት ወር በላይ ያስቆጠረችው 'ጣና ነሽ 2' ጀልባ ከአንድ ወር በኋላ ባሕር ዳር ከተማ ትደርሳለች ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ገለጸ።
በተቋሙ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ደምሰው በንቲ ለቢቢሲ እንደገለጹት ጀልባዋ ከጂቡቲ ወደብ የተነሳችው መጋቢት 30/2017 ዓ.ም. ሲሆን ሰኔ 13/2017 ዓ.ም. አዲስ አበባ ከተማ ደርሳለች።
ለአገር ውስጥ የውሃ ትራንስፖርት እንድታገለግል የተሠራችው ጣና ነሽ 2 እና ሌላ መለስተኛ ዕቃ ጫኝ ጀልባ ከቻይና ተነስተው ጂቡቲ ዶራሌህ ወደብ መድረሳቸው የተገለፀው ባለፈው ዓመት መጋቢት 23 ነበር።
ከወራት በኋላ አዲስ አበባ ከተማ የደረሰችው ጣና ነሽ 2 ከ500 በላይ ኪሎ ሜትሮችን አቆራርጣ ጣና ሐይቅ በሚገኝበት ባሕር ዳር ከተማ ለመድረስ አንድ ወር ገደማ ይወስድባታል ተብሎም ይጠበቃል። ይህም መንገድ ላይ በሚያጋጥሙ ሁኔታዎች የሚወሰን ይሆናል።
ጣና ነሽ 2 ጀልባ 150 ሜትሪክ ቶን ክብደት እና 38 ሜትር ርዝመት ያላት ሲሆን፣ 188 ሰዎችን የመያዝ አቅም እንዳላት ተገልጿል።
ጀባዋ ጣና ሐይቅ ከደረሰች በኋላም በኢትዮጵያ በስፋቱ ትልቅ በሆነው ጣና ሐይቅ ላይ ለጎብኝዎች እና ለነዋሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎት ትሰጣለች ተብሎ ይጠበቃል።
"በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ትልቅ እና ዘመናዊ ጀልባ" እንደሆነች የተነገረው ጣና ነሽ 2፣ በደረሰችባቸው ከተሞች አቀባበል ሲደረግላት የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች ተጋርተዋል።
ሆኖም 'የዔሊ ጉዞዋ' አልጋ በአልጋ አይደለም። በአውራ ጎዳናዎች ላይ በተዘረጉ የኤሌክትሪክ መስመሮች፣ በጠባብ መዞሪያዎች እንዲሁም በድልድዮች ስትፈተን ታይታለች።
ጀልባዋ በየብስ ጉዞ ላይ ረጅም ጊዜ ማሳለፏም በበርካቶች ዘንድ ጥያቄዎችን አስነስቷል።
"በዚህ ዘመን እንዴት ሌላ አማራጭ አይኖርም? እንዴት የጀልባ መገጣጠሚያ ተቋም አይኖርም?" ሲሉ የተቹም አሉ።
ጀልባዋን ለማሳለፍ በሚደረጉ ጥረቶች ምክንያትም በርካታ መሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት በመድረሱ ነዋሪዎች መብራት እና ውሃን ጨምሮ ከተለያዩ አገልግሎቶች መስተጓጎላቸውን ሲገልጹም ነበር።
የባሕር በር የሌላቸው አገራት በአገር ውስጥ ለውሃ ትራንስፖርት የሚያገለግሉ እና በኮንቴነር ውስጥ ሆነው መጓጓዝ የማይችሉ ትላልቅ ጀልባዎችን በከባድ ተሽከርካሪዎች አሊያም በባቡር ያጓጉዛሉ።
ባለፈው ዓመትም ምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር ኡጋንዳ፣ ኬንያ ሞምባሳ ወደብ የደረሰውን አነስተኛ መርከብ በከባድ ተሽከርካሪ ያጓጓዘች ሲሆን፣ ኡጋንዳ ድንበር ለመድረስ በወሰደባት ጊዜ ትችቶችን አስተናግዳ ነበር።
አቶ ደምሰው፣ ጀልባዋ "ግዙፍ" ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ጉዞውን በጥንቃቄ ማድረግ ስለሚያስፈልግ እንዲሁም በየቦታው በድልድዮች ምክንያት በሚገጥማትን እንቅፋት፣ ተቀያሪ መንገዶችን ለማመቻቸት፣ መንገድ ለመጥረግ እና የኤሌክትሪክ መስመሮችን ለማንሳት በሚደረገው ሒደት ምክንያት ጉዞዋ መጓተቱን ገልጸዋል።
በአፋር ክልል የነበራት ጉዞ ሜዳማ በሆነው መልከዓ ምድር ምክንያት ጥሩ እንደነበር የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ ሆኖም "ጥንቃቄ ስለሚያስፈልግ በቀን ውስጥ በጣም ውስን ርቀት ስትጓዝ ነበረ" ብለዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ከሆነ ጣና ነሽ 2ን በሌላ የትራንስፖርት አማራጭ ለማጓጓዝም ሆነ አገር ውስጥ ለመገጣጠም የሚያስችሉ አማራጮች የሉም።
"የጀልባ መገጣጠሚያ ፋብሪካም ሆነ ማዕከል የለም፤ በጀልባ ግንባታ ላይ የተሰማሩ ብቁ ባለሙያዎችም የሉም" ያሉት አቶ ደምሰው፤ ለረጅም ጊዜ ሰፊ ጥናት ከተደረገ በኋላ በከባድ ተሽከርካሪዎች ተጭና እንድትጓጓዝ መወሰኑን አስረድተዋል።
ይህ ብቻም ሳይሆን የጀልባዋ ዘመናዊ መሆንም ነገሩን ውስብስብ እንዳደረገው ገልጸዋል። "የኤሌክትሪክ ሥርዓቷ እና የውሃ መስመር አሠራሯ በጣም ውስብስብ ስለሆነ የብዙ አካላትን ጥምረት የሚፈልግ በመሆኑ ሌሎች አማራጮችን መጠቀም አልቻልንም" ብለዋል።
የጣና ነሽ 2 ጉዞ በከፍተኛ የአገሪቱ አመራሮች በሚመራ ኮሚቴ ክትትል የሚደረግለት ሲሆን፣ ደኅንነቷን ለመጠበቅም በፀጥታ ኃይሎች ትታጀባለች።
የፌደራል ፖሊስ እና የመከላከያ አባላትን ጨምሮ የፀጥታ ኃይሎች፣ የትራፊክ ፖሊሶች እና የኤሌክትሪክ ባለሙያዎች ከእርሷ እየቀደሙ በጉዞዋ ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ እንቅፋቶችንም ያስወግዳሉ።
"በተለየ ሁኔታ የተለየ አደጋ ያጋጥማታል ብለን አናስብም፤ ለአገራችን የመጀመሪያ የሆነች ዘመናዊ ጀልባ ናት የትኛውም ዜጋ እንደሚጓጓው ሁሉ የሥራ ኃላፊዎችም በብርታት እየሠሩ ነው" ብለዋል ዳይሬክተሩ።
አቶ ደምሰው ጣና ነሽ 2 ስንት እንደወጣበት ከመግለጽ ቢቆጠቡም፤ ግዥን ጨምሮ ለማጓጓዣ እና ሌሎች ወጪዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እንደሚወጣ ይታመናል።
ከጂቡቲ ወደብ ተነስታ ባሕር ዳር እስከምትደርስ ድረስም "የጉዞ ደኅንነት ዋስትናዋ" ጉዳይም ከአጓጓዥ ድርጅቱ ጋር በተገባው ውል ውስጥ መካተቱን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
ጣና ነሽ 2 በጣና ሐይቅ ላይ ለጎብኝዎች፣ በደሴቶች ለሚኖሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ምቹ የባሕር ትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት በቱሪዝሙ ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ታደርጋለች ተብሎ ይታመናል።
ጣና ሐይቅ በውስጡ 37 ደሴቶችን የያዘ ሲሆን ከ15 ሺህ በላይ ሰዎች እንደሚኖሩበት ይገመታል። በደሴቶቹ ውስጥም ገደማት እንዲሁም የተለያዩ ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ የቱሪስት መስህቦች ይገኛሉ።
እስካሁን በሐይቁ ላይ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠች ያለችው ለሰው፣ ለእንስሳት እና ለዕቃ ማጓጓዣነት የምታገለግለው ዕድሜ ጠገቧ ጣና ነሽ 1 ጀልባ ናት።
ጀልባዋ ጣልያኖች ኢትዮጵያን በወረሩበት ወቅት ካስገቧቸው እና በኋላም ጥለዋቸው ከወጡ ሦስት ጀልባዎች መካከል አንዷ እንደሆነች ይነገራል።
አቶ ደምሰው እንዳሉት አሁን በጉዞ ላይ ያለችው "ግዙፍ ጀልባ" ጣና ነሽ 2 የሚል ስያሜ ያገኘችው በሐይቁ ላይ እያገለገለች ካለችው ጥንታዊ ጀልባ ቀጥሎ አገልግሎት የምትሰጥ ሁለተኛዋ ጀልባ በመሆኗ ነው።
በቀጣይም እንደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ፣ አባያ እና ባሮ ባሉ ለውሃ ትራንስፖርት አመቺ በሆኑ ቦታዎች ሁሉ የጀልባ ትራንስፖርትን ለማዘመን እና ለማሳደግ መታቀዱንም ዳይሬክተሩ ጨምረው ገልጸዋል።