ኩባ በነዳጅ እጥረት ምክንያት ለመጀመሪያ ጊዜ የሜይዴይ ሰልፍን ሰረዘች

የኩባ ኮሚኒስት ፓርቲ ዘንድሮ የዓለም ላብ አደሮች ቀን - የሜይዴይ ሰልፍ እንደማይኖር አስታወቀ።

የሜይዴይ ሰልፍ እንዲሰረዝ የተደረገው በነዳጅ እጥረት የተነሳ ነው።

በኩባ ዋና ከተማ ሃቫና በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚቀጠሩ ሰዎች የሠራተኞች ቀንን በማስመልከት በአብዮት አደባባይ ሠልፍ ይወጡ ነበር።

የኩባ አብዮት ከተካሄደበት ከ1959 ወዲህ ይህ የሠራተኞች ቀን በዓል በኢኮኖሚ ምክንያት ሲሰረዝ የዘንድሮው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በአገሪቱ ነዳጅ ለመቅዳት ዜጎች ረዥም ሰልፍ ለመጠበቅ ተገደዋል።

አንድ ዜጋ ነዳጅ ለመቅዳት ቀኑን ሙሉ ብቻ ሳይሆን ለቀናት ሰልፍ መጠበቅ ሊኖርበት ይችላል።

በዚህ ወር መጀመሪያ የኩባው ፕሬዝዳንት ሚጉል ዲያዝ ካነል አገራቸው ከሚያስፈልጋት የነዳጅ መጠን ሁለት ሦስተኛውን ብቻ ነው እያገኘች ያለችው ሲሉ ቅሬታ አሰምተዋል።

የነዳጅ አቅራቢዎች በኮንትራታቸው መሠረት ውላቸውን እያከበሩ እንዳልሆነ ጠቅሰውም ወቅሰዋል።

ኩባ ዝቅተኛ ደረጃ ያለው ድፍድፍ ነዳጅ ያላት ቢሆንም በአሜሪካ ማዕቀብ የተነሳ ግን ድፍድፍ ነዳጁን ማጣራት አልቻለችም።

ከፍተኛ ጥራት ያለው ነዳጅ ኩባ የምታገኘው ከቬንዝዌላ ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የፍላጎቷን 50 ከመቶ ብቻ ነው ቬንዝዌላ ለኩባ እየላከች ያለችው።

ተንታኞች እንደሚሉት የኩባ ወዳጅ ቬንዝዌላ የራሷ በርካታ ችግሮች ያሉባት ሲሆን፣ የሶሻሊስት አጋሯ ኩባን ለመደጎም ለጊዜው አቅም አንሷታል።

ይህ በአገሪቱ የተከሰተው ከባድ የነዳጅ እጥረት በኩባ ያለውን የኑሮ ክብደት እጥፍ ድርብ-ድርብርብ እንዲሆን ምክንያት ሆኗል።

የስፔኑ ኤልፓይስ ጋዜጣ እንደዘገበው በኩባ አማካይ የደመወዝ መጠን በወር ከ150 አስከ 200 ዶላር ነው። አንድ ሊትር የምግብ ዘይት ደግሞ 30 ዶላር ያስወጣል።

የኩባ መንግሥት የሶሻሊስት ሥርዓት ለአገሪቱ ምርጡ ሥነ አስተዳደር ነው ብሎ ያምናል።

አሁን በአገሪቱ ያሉት የምጣኔ ሃብት ችግሮች እና ምስቅልቅሎች ሁሉ ምክንያታቸው የሚመነጨው ከአሜሪካ አሻጥር እና ማዕቀብ ነው ይላል።

ከዚህ ቀደም የሜይዴይ በዓል በኩባ ሲከበር መንግሥት ሰፊ ዝግጅት ያደርግ ነበር። በዓሉን ለማስተባበርም መንግሥት ሁነኛውን ሚና ይጫወት ነበር።

ሜይዴይ ከዘንድሮ ሌላ በኮቪድ ምክንያት በፈረንጆቹ 2020 እና 2021 ሳይከበር ቀርቷል።

ከዚያ ሌላ ግን የኩባ አብዮት ከፈነዳ ወዲህ አንድም ጊዜ ይህ በዓል ተሰርዞ አያውቅም።

ዘንድሮ በዓሉ በድምቀት በሃቫና አብዮት አደባባይ ባይከበርም በየሰፈሩ ግን አንዳንድ መለስተኛ ዝግጅቶች ይኖራሉ ተብሏል።