ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሱዳን ተኩስ አቁም ተጥሶ ካርቱም ውስጥ የአየር ጥቃት እና ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ነው
በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም በተፋላሚ ኃይሎች መካከል የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት ያፈረሰ ከባድ ውጊያ ተባብሶ መቀጠሉ ተዘገበ።
ከተቀናቃኙ የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ጋር ግጭት ውስጥ የሚገኘው የሱዳን ሠራዊት ዛሬ እሁድ ጠዋት በዋና ከተማዋ ካርቱም ውስጥ መጠን ሰፊ የማጥቃት እርምጃ እየወሰደ መሆኑን አስታውቋል።
ምንም እንኳን የተኩስ አቁም የተደረሰ ቢሆንም የሱዳን ሠራዊት ታንኮች እና ከባድ መድፎችን በማሰማራት ጥቃት መክፈቱ ተነግሯል።
ባለፈው ሐሙስ ለሦስት ቀናት እንዲራዘም ስምምነት ተደርሶበት የነበረው የተኩስ አቁም ዛሬ ምሽት ያበቃል ተብሎ ነበር።
ሁለት ሳምንት በሆነው ግጭት የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ጥቃቱን እያካሄደ ያለው በጄኔራል ሞሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ ወይም ሔሜቲ በሚመሩት ኃይሎች የተያዙትን የከተማዋን አካባቢዎች መልሶ ለመቆጣጠር መሆኑን ገልጿል።
ሱዳን ውስጥ አስካሁን በተካሄዱት ወታደራዊ ግጭቶች ቢያንስ አምስት መቶ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ነገር ግን በውጊያ የሞቱም ሆነ የተጎዱ ሰዎች አሃዝ ከዚህ በከፍተኛ ሁኔታ የበለጠ ሊሆን እንደሚችል ተሰግቷል።
የሱዳን ጦር ሠራዊት እንዳለው በዋና ከተማዋ ውስጥ በፈጥኖ ደራሹ ኃይል ቁጥጥር ስር ያሉ አካባቢዎችን መልሶ ለመቆጣጠር ከባድ መድፎችን በመጠቀም ከሁሉም አቅጣጫ በካርቱም ላይ ጥቃት ከፍቷል።
በዚህ ዘመቻ ወቅት የከተማዋ ነዋሪዎች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ከቤታቸው እንዳይወጡ እና ከመስኮቶች አካባቢ እንዲርቁም ጦሩ አስጠንቅቋል።
ካርቱም ውስጥ ከባድ ውጊያ መደረግ የጀመረው ቅዳሜ ምሽት ሲሆን፣ የአገሪቱ ሠራዊት በከተማዋ ማዕከላዊ ክፍል በስተሰሜን በኩል በሚገኙት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አባላት ላይ በከፈተው ዘመቻ ምክንያት ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን ገልጿል።
በጄኔራል ሔሜቲ ኃይሎች ቁጥጥር ስር በሚገኙት የጦር ሠራዊቱ ዋና መሥሪያ ቤት እና በፕሬዝዳንታዊው ቤተ መንግሥት አቅራቢያም ከባድ ውጊያዎች እንደተደረጉ ሩፖርቶች አመልክተዋል።
የዐይን እማኖች ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት የሠራዊቱ ድሮኖች በዋነኛው የነዳጅ ማጣሪያ አቅራቢያ በሚገኝ የጄኔራል ሔሜቲ ኃይሎች ይዞታ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል።
“በሰፈራችን አካባቢ ማለዳ ላይ ሲበሩ በነበሩት በጦር አውሮፕላኖች እና በፀረ አውሮፕላን መሳሪያዎች ተኩስ እና ፍንዳታ ነው ከእንቅልፋችን የነቃነው” ሲል አንድ ነዋሪ ለፈረንሳዩ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ ተናግሯል።
የሱዳን ሠራዊት በተቃውሞ ሰልፎች ላይ ጭካኔ የተሞላበት እርምጃዎችን በመውሰድ የሚታወቀውን ማዕከላዊ ተጠባባቂ ፖሊስ የተባለውን ቡድን በማሰማራት ግጭቱ እንዲስፋፋ እያደረገ ነው ሲል የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እየከሰሰ ነው።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተካሄዱት ግጭቶች ምክንያት በዋና ከተማዋ ካርቱም የመሠረታዊ ፍጆታዎች እና አገልግሎቶች አቅርቦት የተቋረጠ ሲሆን፣ ባለፉት ቀናት የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት የነዋሪዎችን ችግር ለመፍታት በር ይከፍታል ቢባልም ውጊያው እንደቀጠለ ነው።
የአገሪቱ ጦር ሠራዊት በከባድ መሳሪያዎች በመታገዝ በካርቱም ላይ ከከፈተው ጥቃት ለመሸሽ ዕድሉ እና አቅሙ ያላቸው ነዋሪዎች ከከተማዋ እየወጡ ይገኛሉ።
ባለፉት ቀናት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ባገኙት መንገድ ሁሉ ወደ ጎረቤት አገራት እየተሰደዱ ሲሆን፣ ውጊያው ተባብሶ የሚቀጥል ከሆነ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ይሰደዳሉ ተብሎ ተሰግቷል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም በአሁኑ ወቅት ሱዳንን ጥለው ሊሰደዱ ለሚችሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለመርዳት ከወዲሁ ዝግጅት መደረግ እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።
ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ለሦስት ቀናት የቆየው የተኩስ አቁም በተደረገበት ጊዜ አገራት ዲፕሎማቶቻቸውን እና ዜጎቻቸውን በአየር፣ በባሕር እና በየብስ ከሱዳን ያስወጡ ሲሆን፣ የተኩስ አቁሙ ለተጨማሪ ሦስት ቀናት እንዲራዘም ተደርጓል።
አገራት፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የጦር ሠራዊቱ መሪ ጄኔራል አል ቡርሐን እና ጄኔራል ዳጋሎ ውጊያ አቁመው ለድርድር እንዲቀመጡ በተደጋጋሚ ቢጠይቁም፣ ከተኩስ አቁም ስምምነቱ ውጪ ውጤት አልተገኘም።
ጄኔራል አል ቡርሐን ለንግግር ዝግጁ መሆናቸው የገለጹ ሲሆን፣ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ ጄኔራል ሔሜቲ ግን በተዋጊዎቻቸው ላይ “ያልተቋረጠ” ጥቃት እየተካሄደ መሆኑን በመጥቀስ፣ ጦርነቱ አስካላበቃ ድረስ ድርድር እንደማይኖር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሱዳን ወደ ሲቪል አስተዳደር በምትመለስበት እና አንድ መቶ ሺህ የሚሆኑት የሰለጠኑ አባላት ያሉት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ወደ አገሪቱ ሠራዊት በሚካተትበት ዕቅድ ላይ በሁለቱ ጄኔራሎች መካከል አለመግባባት መፈጠሩ ነበር ሚያዝያ 07/2015 ዓ.ም. ለውጊያው መቀስቀስ ምክንያት የሆነው።
ሁለቱ ጄኔራሎች ከኦማር ሐሰን አልበሽር ከሥልጣን መውረድ በኋላ የተቋቋመውን የሽግግር አስተዳደር በመፈንቅለ መንግሥት በማስወገድ ሥልጣን ከያዙ በኋላ አገሪቱን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለመመለስ የነበረውን ዕቅድ ሲገፉት ቆይተዋል።
ለዚህም ምክንያቱ ጄኔራሎቹ እና በስራቸው ያሉ ባለሥልጣናት ከመሪነት መንበሩ ከተነሱ ከ20 ዓመት በፊት ዳርፉር ውስጥ ከተፈጸሙ የጦር ወንጀሎች ጋር በተያያዘ በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ተጠያቂ እንሆናለን የሚል ስጋት ስላላቸው እንደሆነ ይነገራል።