ግብረ ኃይሉ በውጭ የሚገኙ ተጠርጣሪዎች ተላልፈው እንዲሰጡት እየሰራ መሆኑን ገለጸ

በውጭ አገራት ሆነው ግጭት በመፍጠር የክልል እና የፌደራል መንግሥትን በኃይል ለመጣል ተንቀሳቅሰዋል ያላቸው ግለሰቦች ተላልፈው እንዲሰጡት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት ገለጸ።

የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል በተጨማሪም “ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፍረስ እና በሽብር ወንጀል” ውስጥ በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ ነበር የተባሉ ግለሰቦችን ሀብት የመቆጣጠር እርምጃ እንደሚወሰድ አሳውቋል።

የአገሪቱ ዋነኞቹ የፀጥታ እና የደኅንነት ተቋማት የተካተቱበት ግብረ ኃይል እሁድ ምሽት ባወጣው መግለጫ፣ ወደ ሃምሳ የሚጠጉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር መዋላቸውን እና ከ10 በላይ የሚሆኑት ደግሞ እንደሚፈልጉ ገልጿል።

ግብረ ኃይሉ “ጽንፈኛ” ያላቸው ኃይሎች “የሐሰት ወሬዎችን በመፍጠር እና የሽብር ፕሮፓጋንዳ በመንዛት” በአገሪቱ ውስጥ የብሔር እና የሃይማኖት ግጭት እንዲፈጠር በህቡዕ ተደራጅተው እየሰሩ ነው በማለት ከሷል።

ጨምሮም በአገር ውስጥ እና በውጭ አገራት ሆነው አገሪቱ ውስጥ “ሁከት እና ትርምስ” እንዲፈጠር በማድረግ የክልል እና የፌደራል መንግሥትን በኃይል ለመጣል አላማም አላቸው ብሏል።

በዚህም ሳቢያ በህቡዕ አደረጃጀቱ ውስጥ አሉ በተባሉት እና በአገር ውስጥ እንዲሁም በውጭ ባሉ ግለሰቦች ላይ “በሽብርተኝነት ምርመራ” እየተደረገባቸው መሆኑን የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ አመልክቷል።

ግብረ ኃይሉ “የሽብር ኃይሎች” ያላቸው ግለሰቦች ካሉባቸው አገራት በዓለም አቀፉ የፖሊስ ተቋም - ኢንተርፖል፣ እንዲሁም ከሚኖሩባቸው አገራት መንግሥታት የፀጥታ እና የደኅንነት ተቋማት ጋር በመተባበር “ተላልፈው እንዲሰጡ እና በሕግ እንዲጠየቁ እየሰራ መሆኑን” ገልጿል።

በተጨማሪም ግብረ ኃይሉ በውጭ አገራት የሚኖሩ ናቸው ያላቸውን ግለሰቦች “ከውጭ አገር በሚያገኙት እና በአገር ውስጥ ያላቸውን ሀብት” አቅደውታል ላለው አላማ እንዳያውሉ፣ በአገር ውስጥ ያላቸውን ሀብት የመለየት እና በሕግ የመቆጣጠር እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አስታውቋል።

ከዚህ በተጨማሪም የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል እሁድ ባወጣው መግለጫው ላይ እንዳስታወቀው “በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ እና የሽብር ተግባር ሲፈጽሙ የተገኙ” ያላቸውን 47 ተጠርጣሪዎችን ከተለያዩ የጦር መሳሪያዎች እና የግንኙነት መገልገያዎች ጋር መያዙን አመልክቷል።

ግብረ ኃይሉ የተያዙት ግለሰቦች የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮችን “ለመግደል፣ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል በመናድ የክልሉን መንግሥታዊ መዋቅር በመቆጣጠር የፌደራል መንግሥትን ለመጣል” በአገር ውስጥ እና በውጭ አገራት ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ እንደደረሰባቸው ገልጿል።

የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ ይህንን እርምጃ መውሰዱን ያሳወቀው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ሚያዝያ 19/2015 ዓ.ም. የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል እና የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ በታጣቂዎች መገደላቸውን ተከትሎ ነው።

ግብረ ኃይሉ እሁድ ዕለት የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው የተፈጸመውን የገዢው ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ግድያን ተከትሎ “በአማራ ክልል ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በማፍረስ ሥልጣን በኃይል ለመያዝ” በአገር ውስጥ እና በውጭ በሚንቀሳቀሱ “ጽንፈኛ ኃይሎች” ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን አስታውቆ ነበር።

የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ ካወጣው መግለጫ ጋር “ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፍረስ እና በሽብር ወንጀል” ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለዋል ያላቸውን የ42 ተጠርጣሪዎችን ምስል አያያዞ አቅርቧል።

በተጨማሪም ታዋቂውን ፖለቲከኛ አቶ ልደቱ አያሌውን፣ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚሰሩ እና የፋኖ አባላት ያሉበት ተፈላጊ ናቸው ያላቸውን የአስራ አንድ ተጠርጣሪዎችን ምስልም ግብረ ኃይሉ ለመገናኛ ብዙኃን አሰራጭቷል።

ቁጥጥር ስር ከዋሉት ተጠርጣሪዎች መካከል ከሳምንታት በፊት በፀጥታ ኃይሎች ተይዘው ፍርድ ቤት መቅረብ የጀመሩ የሚገኙበት ሲሆን፣ በጋዜጠኝነት እና በተለያዩ ሙያዎች ላይ የተሰማሩ መሆናቸው መዘገቡ ይታወሳል።

የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል፤ የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር እና የአዲስ አበባ ፖሊስ የተካተቱበት ነው።

ግብረ ኃይሉ ዋነኛ በተባሉ የአገሪቱ የአገሪቱ የመከላከያ እና የደኅንነት ጉዳዮች ላይ በጥምረት የሚሰራ የተለያዩ አካላት ጥምረት ነው።