በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የሚፈለጉት የሩሲያዋ ፖለቲከኛ እና የኦርቶዶክስ ካህን ባለቤት ማሪያ

የፎቶው ባለመብት, Presidential Commissioner For Children's Rights
በቅርቡ የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በተጨማሪ በ38 ዓመቷ ሩሲያዊ ፖለቲከኛም ላይ የእስር ትዕዛዝ አውጥቷል።
ማሪያ ሎቫቫ ቤሎቫ ህጸናትን እና ታዳጊዎችን በሕገወጥ መንገድ በማፈናቀል ወንጀል ነው ክስ የቀረበባቸው።
የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) በሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ ያወጣው የእስር ትዕዛዝ ችሎቱ ሩሲያን በጦር ወንጀሎች ለመክሰስ ያለውን ቁርጠኝነት አሳይቷል ተብሏል።
ከእነዚህ ጦር ወንጀሎች መካከልም አንዱ የዩክሬን ህጻናትን ወደ ሩሲያ “በሕገወጥ መንገድ ማፈናቀል” የሚል ይገኝበታል።
በእነዚህ የጦር ወንጀሎች ክስ ላይ የሩሲያ የህጻናት መብቶች ኮሚሽነር እና ፖለቲከኛዋ ማሪያ ሎቫቫ ከፑቲን ጋር በማበር ተጠቅሰዋል።
የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረችበት ካለፈው ዓመት ጀምሮ ህጻናት በሕገወጥ መንገድ እንዲፈናቀሉ መደረጋቸውን ጠቅሷል።
ማሪያ እስካሁን ስለግል እና አጠቃላይ ሕይወታቸው ከሩሲያ ውጭ ባለው ዓለም እምብዛም አይታወቅም ነበር።
ለመሆኑ ማሪያ ማን ናቸው? ህጻናቱን ወደ ሩሲያ በመውሰድ ሂደት ውስጥ የነበራቸው ሚናስ ምንድን ነው?
የዩክሬን ህጻናት ለምን ወደ ሩሲያ ተወሰዱ?
የዩክሬን ባለሥልጣናት እንደሚሉት ወደ 20 ሺህ የሚጠጉ ዩክሬናውያን ህጻናት ወደ ሩሲያ ተወስደዋል። ህጻናቱ ያለ ወላጆቻቸው በአስገዳጅ ሁኔታ ወደ ሩሲያ እንዲጓዙ ተደርጓል ተብሏል።
የዩክሬን መንግሥት እንደሚለው በርካታ ቤተሰቦች ልጆቻቸው ጋር ለመገናኘት እየጠየቁ ነው።
ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥም ወደ 300 የሚጠጉ ህጻናት ወደ ዩክሬን ተመልሰዋል።
ዩክሬን እና ምዕራባውያን አጋሮቿ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ህጻናትን ሩሲያ በወረራ ከያዘቻቸው የዩክሬን ግዛቶች ወደ አገሯ መውሰዷ የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው ሲሉ ይከሳኩ።
ህጻናቱን የሩሲያ ዜግነት በመስጠትም ዩክሬንን ከአገርነት ለመፋቅ የሚደረግ ሙከራ እንደሆነም ይናገራሉ።
ይህ ደግሞ በጦርነት አካባባቢ ሰላማዊ ዜጎችን ለመጠበቅ ያለመው የአውሮፓውያኑ 1949 የጄኔቫ ስምምነትን ይጥሳል።
“ልጆቻችንን ነጥቃ በመውሰድ ሩሲያ የወደፊት ተስፋችንን እየሰረቀች ነው” ሲሉ የዩክሬን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አንድሪ ኮስቲን ተናግረዋል።
ወደ 380 የሚጠጉ የዩክሬን ህጻናት በሩሲያ ቤተሰቦች እንክብካቤ ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል። በመደበኛነት ለጉዲፈቻ ባይሰጡም፣ ነገር ግን ወደ ዩክሬን የመመለሱ ሂደት ውስብስብ ሊሆን እንደሚችል ተነግሯል።
የሩሲያ የህጻናት መብቶች ኮሚሽነር ማሪያ ሎቮቫ ቤሎቫ በዚህ ሕገወጥ የህጻናቱ ዝውውር እጃቸው እንዳለበት አይሲሲ ገልጿል።
“በቀጥታ ወይም በሌሎች እርዳታ ህጻናቱን በሕገወጥ መንገድ አዘዋውረዋል” ብሏል ዓለም አቀፉ የወንጀል ችሎት።
ሩሲያ በበኩሏ በዩክሬን “ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” ብላ የምትጠራው ጦርነት ከተጀመረበት ዕለት ጀምሮ የዩክሬን ህጻናት ወደ ሩሲያ እንደተወሰዱ አልደበቀችም።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሆኖም ከዩክሬን በተጻራሪ የተወሰዱ ህፃናት ቁጥር ወደ 2 ሺህ 500 መሆኑን ከወራት በፊት የሩሲያ ባለሥልጣናት ተናግረዋል። ቢቢሲ የቅርብ ጊዜ መረጃን በተመለከተ የማሪያን ቢሮ ጠይቆ ምላሽ እየጠበቀ ነው።
የሩሲያ ባለሥልጣናት እና የህፃናት መብቶች ኮሚሽነር ወደ ሩሲያ የተወሰዱት የዩክሬን ህጻናት ወላጅ አልባ እና ለደኅንነታቸው ሲባል እንደሆነ የሚናገሩ ሲሆን፣ በግዳጅ አልተወሰዱም ሲል ያስተባብላል።
ማሪያ ሎቫቫ ዋነኛ ሥራቸው ሩሲያ በልጆች ላይ ያላትን ፖሊሲዎች መቅረጽ እና ማስፈጸም ነው። በህጻናቱ ዝውውር ምክንያት ታዋቂ የሆኑት ማሪያ፣ ህጻናቱን ከውጊያ ቀጣናዎች መጠበቅ እንዲሁም በሩሲያ ማኅበረሰብ ውስጥ የማዋሃድ ሙከራ ነው ሲሉም በተደጋጋሚ ሲሟገቱ ተደምጠዋል።
ፖለቲከኛዋ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቻቸው እንዲሁም በመግለጫዎቻቸው ላይ የዩክሬንን ህጻናትን ወደ ሩሲያ መውሰድ ለህጻናቱ ጥቅም እንደሆነ ይናገራሉ። ህጻናቱ በሩሲያ ቆይታቸው ደስተኛ እንደሆኑ እና ብዙዎቹም መመለስ አይፈልጉም ብለዋል።
የቀድሞ ሴናተር፣ የካህን ሚስት እና የበርካታ ልጆች እናት ማሪያ
ባለፈው የአውሮፓ የበጋ ወቅት ማሪያ ራሳቸው ከደቡባዊ ዩክሬን ማሪዩፖል ከተማ አንድ ልጅ በማደጎ ወስደዋል።
የማሪዩፖል ከተማ ለወራት ከዘለቀው መራራ ጦርነት በኋላ በሩሲያ ወታደሮች ቁጥጥር ስር ውስጥ ገብታለች።
በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኘው ፊሊፕ ጎሎቭኒያ የሩሲያ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ከሆነ ወላጆቹን ያጣ ልጅ ነው። ፊሊፕ ከሌሎች የዩክሬን ህጻናት ጋር ወደ ሩሲያ መጥቶ ማሪያ ልክ ዐይናቸው ሲያርፍበት “የእኔ መሆኑን” አወቅኩኝ ይላሉ።
የእሱንም ፎቶግራፍ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቻቸው ላይ በተደጋጋሚ ይለጥፋሉ። ፊሊፕ የማሪያ ብቸኛ ልጅ አይደለም። ማሪያ አስር ልጆች ያሏቸው ሲሆን፣ አምስቱ በማደጎ ሌሎቹ ደግሞ የወለዷቸው ናቸው። አንዳንዶቹም ዕድሜያቸው ትልቅ ነው።
ፖለቲከኛዋ የሚንከቧከቧቸው ህጻናት ቁጥር የሚለዋወጥ ሲሆን፣ በአንድ ወቅት 18 ደርሶ እንደነበር ተነግሯል።
ከሞስኮ ደቡብ ምሥራቅ 750 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ፔንዛ ከተማ የተወለዱት ማሪያ፣ የሩሲያ የህጻናት መብቶች ኮሚሽነር የሆኑት በአውሮፓውያኑ 2021 ነው።
ከዚያ በፊት ክልላቸውን በመወከል የሩሲያ የላይኛው ምክር ቤት ውስጥ (ሴናተር) እንደራሴ ነበሩ። በሩሲያ ገዢ ፓርቲ “ዩናይትድ ሩሲያ” ውስጥም ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ይታወቃሉ።
ባለቤታቸው የኦርቶዶክስ ካህን ሲሆኑ አብዛኛውን ጊዜ በሃይማኖታዊ አገልግሎቶች ላይ የራስ መሸፈኛ ለብሰው ሲሳተፉ የሚያሳዩ ፎቶዎች ወጥተዋል።
በህጻናት እና ታዳጊዎች ላይ ያተኮረ የማኅበራዊ አገለግሎት ሥራ ላይ መሳተፍ የጀመሩት በአውሮፓውያኑ 2000ዎቹ ሲሆን “ሉዊስ ኳርተር” የተሰኘ ድርጅትም አቋቋመዋል።
የድርጅታቸው ስም ሉዊስ ስያሜውን ያገኘው አሜሪካዊው የጃዝ ሙዚቀኛ ሉዊስ አርምስትሮንግን ለማስታወስ ነው። ሙዚቀኛው በአስራዎቹ ዕድሜ ላይ ከምትገኝ እናት የተወለደ ሲሆን፣ ያደገውም በድህነት ነው።
ማሪያ ወደ ፖለቲካ ሕይወት ከመግባታቸው በፊት በሌሎች በርካታ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ውስጥ ተሳታፊ ነበሩ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ክሶቹን የሚያጣጥሉት ማሪያ
ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረችበት ጊዜ ጀምሮ ለፕሬዝዳንት ፑቲን ከፍተኛ ድጋፍ በማድረግ የሚታወቁት ማሪያ ሎቮቫ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል። ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤትም (አይሲሲ) ከሁለት ሳምንት በፊት የእስር ትዕዛዝ ያወጣባቸው ሲሆን፣ ክሱንም ውድቅ አድርገውታል።
“አይሲሲ ስለ ምን ዓይነት ጉዳዮች እንደሚያወራ አናውቅም። ምንም ዓይነት፣ ስሞች እና አድራሻዎች አልተጠቀሱም። ስለዚህ ይህንን መረጃ ማረጋገጥ አንችልም” የሚሉት ማሪያ፣ “ህፃናት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተለያይተው ከሆነ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለማገናኘት ሁሉንም ጥረት እናደርጋለን” ይላሉ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቻቸው ላይ በአገሪቱ የተለያዩ ማዕዘናት ካሉ ወላጆች፣ የሥራ ባልደረቦች ስለተሰጣቸው ሞቅ ያለ የድጋፍ እና የአጋርነት ጥሪ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
“የምንደብቀው ምንም ነገር የለም። እውነት ከእኛ ጎን ናት” የሚሉት ማሪያ “ሩሲያ ለዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት እውቅና ስለማትሰጥ ውሳኔዎቹ ለእኛ ትርጉም የለሽ ናቸው” በማለትም ክሱን አጣጥለውታል።
‘ሜሞሪያል’ ለተሰኘው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት የሚሰሩት እና የሕግ ባለሙያ የሆኑት ናታሊያ ሴክሬታሬቫ፣ ሩሲያ የጄኔቫ ስምምነቶችን ፈራሚ መሆኗን አመልክተው “የዓለም አቀፉን ፍርድ ቤት ክስ ውድቅ ማድረግ ውሃ የሚቋጥር አይደለም” ብለዋል።
ባለፈው የአውሮፓውያኑ የበጋ ወቅት ፕሬዝዳንት ፑቲን የዩክሬን ታዳጊዎች የሩሲያ ዜግነት የሚያገኙበት ሂደት እንዲቀል አንድ አዋጅ ፈርመዋል። የዩክሬን ህጻናት የሩሲያ ሰነዶችን ሲቀበሉ የሚያሳይ የዜና ዘገባዎች እና የማኅበራዊ ሚዲያ ቪዲዮዎች ማሪያን ጨምሮ በሩሲያ ባለሥልጣናት ተሰራጭተዋል።
የሩሲያ ፓስፖርቶችን ለዩክሬናውያን መስጠት “በጅምላ” እየተፈጸመ መሆኑን የሩሲያ ባለሙያዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ዩክሬን የሩስያ ፓስፖርቶችን ለዩክሬን ህጻናት የመስጠትን ሂደት “ሕጋዊ የሆነ አፈና” ስትል ገልጻዋለች።
የተባበሩት መንግሥታት ልዩ ኮሚሽን የዩክሬን ህጻናትን ለሩሲያ ቤተሰቦች መስጠት እና የሩሲያ ዜግነት እንዲኖራቸው ማድረግ የእነዚህን ህፃናት ማንነት በመጠበቅ ላይ ከፍተኛ መዘዝ እንደሚያስከትልም በሪፖርቱ አስጠንቅቋል።
ማሪያ ሎቮቫ በሩሲያ የተወሰዱ የዩክሬን ህጻናት የሩሲያ ዜግነት የሚሰጣቸው የጤና አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ እና ሌሎች እርዳታዎችን እንዲያገኙ ለማስቻል ነው ሲሉም በበርካታ አጋጣሚዎች ሲናገሩ ይደመጣሉ።












