ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በጦር ወንጀል ለፍርድ ይቀርቡ ይሆን?

በለንደን የጦርነቱ ተቃውሞ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሄግ ተቀማጭነቱን ያደረገው ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ የእስር ትዕዛዝ አውጥቷል።

ሆኖም ይህ ገና ጅማሮ እንደሆነ እና በጣም የረዘመ ሂደትም እንደሚኖረው ተነግሯል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሩሲያ መሪን በዩክሬን ወረራ ምክንያት የጦር ወንጀል ለመክሰስ በቂ ማስረጃ እንዳለው በግልፅ ያምናል።

ይሁን እንጂ የዓለም ዓቀፉ ፍርድ ቤት አንድ ፕሬዝዳንትን ፍርድ ቤት ለማቆም ፈታኝ ሥራ ነው የሚሆንበት።

ፕሬዝዳንት ፑቲን ሊታሰሩ ይችላሉ?

በአሁኑ ጊዜ ፕሬዝዳንት ፑቲን በትውልድ አገራቸው ሩሲያ ያልተገደበ ሥልጣን ስላላቸው ክሬምሊን ለዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት አሳልፎ ይሰጣቸውል የሚለው እሳቤ የመነመነ ነው።

ፑቲን፣ በሩሲያ ውስጥ ብቻ እስከተወሰኑ ድረስ በቁጥጥር ስር የመዋል ስጋት የለባቸውም።

ሆኖም ፕሬዝዳንቱ ሩሲያን ለቀው ወደ ሌሎች አገራት ከተጓዙ ሊታሰሩ ይችላሉ።

ነገር ግን አስቀድሞም በዓለም አቀፍ ደረጃ በተጣለባቸው ዕቀባ ምክንያት የመዘዋወር ነጻነታቸው በእጅጉ ተገድቧል። በአሁኑ ወቅትም ለዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት አሳልፎ ሊሰጣቸው በሚፈልግ አገር ላይ ሊገኙም አይችሉም።

የሩሲያ ወታደሮች ዩክሬንን ከወረሩበት ጊዜ ጀምሮ ባለው አንድ ዓመት ውስጥ የጎበኟቸው ስምንት አገራትን ብቻ ነው።

ከእነዚህም ውስጥ ሰባቱ የቀድሞዋ የሶቭዬት ኅብረት አባል አገራት ናቸው።

ፕሬዝዳንቱ የጎበኟት ሌላኛዋ አገር ኢራን ናት። ኢራን በዩክሬን ጦርነት ድሮኖችን ጨምሮ ሌሎች የጦር መሳሪያዎችን ለሩሲያ በማቅረብ ክስ የሚሰነዘርባት ሲሆን የፑቲን አጋር ከመሆኗ አንጻር ኢራንን እንደገና ቢጎበኙ ምንም ስጋት አይኖርባቸውም።

ፑቱን ለፍርድ ይቀርቡ ይሆን?

ፕሬዝዳንት ፑቲንን በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ለማቅረብ ሁለት ትላልቅ እንቅፋቶች አሉ።

በመጀመሪያ ደረጃ ሩሲያ ለፍርድ ቤቱ ሥልጣን ዕውቅና አልሰጠችም።

ፍርድ ቤቱ በአውሮፓውያኑ 2002 ሮም ስታቹ ተብሎ በሚጠራው ስምምነት ነው የተቋቋመው።

በዚህም ስምምነት መሠረት አገራት ማንኛውንም ወንጀሎች በራሳቸው ሥልጣን እና ሕግ መጠየቅ፣ መመርመር እንዲሁም መክሰስ ይችላሉ።

ፍርድ ቤቱ ጣልቃ ሊገባ የሚችለው አንዲት አገር ምርመራ ለማካሄድ እና ወንጀለኞችን ለፍርድ ለማቅረብ ካልቻለች ወይም ካልፈለገች ብቻ ነው።

123 አገራት በፍርድ ቤቱ ሕግጋት ለመገዛት ቢወስኑም ሩሲያ ሥልጣኑን አትቀበለውም።

ዩክሬንን ጨምሮ አንዳንድ አገሮች ስምምነቱን ቢፈርሙም አላፀደቁትም።

ስለዚህ ፕሬዝዳንቱን በፍርድ ቤቱ ላይ የማቅረብ ሕጋዊ መሠረት የላትም።

ፕሬዝዳንቱ በሌሉበት ክስ ቢመሠረትባቸውስ? የሚል አማራጭ ሊቀርብ ይችላል። ነገር ግን ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪ በሌለበት ክስ መመሥረት ስለማይችል ይህም አማራጭም ውሃ አይቋጥርም።

ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን

በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የተከሰሱ አሉ?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በሰብአዊነት ላይ ለሚፈጸሙ ወንጀሎችን ወደ ፍርድ የማቅረቡ ሂደት ሙከራ የተጀመረው ፍርድ ቤቱ ከመቋቋሙ በፊት ነው።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በአውሮፓውያኑ 1945 በኑረምበርግ ችሎት ተሞክሯል።

በዚህም በናዚ ጀርመን ጭፍጨፋ እና ሌሎች አሰቃቂ ድርጊቶችን የፈጸሙ ባለሥልጣናትንም ለመቅጣት ተሞክሯል።

የናዚ መሪ አዶልፍ ሂትለር ምክትል ሩዶልፍ ሄስ በዚህ የፍርድ ሂደት የዕድሜ ልክ እስራት የተፈረደበት ሲሆን፣ በአውሮፓውያኑ 1987 ራሱን አጥፍቷል።

ፕሬዝዳንት ፑቲን በሰብዓዊነት ላይ በሚፈጸሙ ወንጀሎች አልተከሰሱም፤ ምንም እንኳን የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ በዚህ ወንጀል መከሰስ አለባቸው ብለው ቢከራከሩም።

በዚህ ወንጀል ቢከሰሱ እንኳን ሌላ የሕግ ክፍተት አለ፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ራሱ እንደሚያትተው፣ “የዘር ማጥፋት እና የጦር ወንጀሎች በዓለም አቀፉ ሕግ ስምምነት ቢካተቱም በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እስካሁን አልተካተቱም። ሆኖም ለማካተት ጥረቶች እየተደረጉ ነው” ብሏል።

ከዚህ ቀደም አንዳንዶች በጦር ወንጀል ተከሰው ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል።

ከእነዚህም መካከል ከ1993 አስከ 2017 የነበረው የተባበሩት መንግሥታት የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ዓለም አቀፍ የወንጀል ችሎት ይጠቀሳል።

በዚህ የወንጀል ችሎት 90 ባለሥልጣናት ጥፋተኛ ተብለው የተፈረደባቸው ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል የቀድሞ የዩጎዝላቪያ ፕሬዝዳንት ስሎቦዳን ሚሎሶቪች ይገኙበታል። ሚሎሶቪች በእስር ላይ እያሉ በአውሮፓውያኑ 2006 በልብ ህመም ሕይወታቸው አልፏል።

የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት በ40 ግለሰቦች ላይ ክስ የመሠረተ ሲሆን፣ ከፕሬዝዳንት ፑቲን በስተቀር ሌሎቹ አፍሪካውያን ናቸው።

ከእነዚህም ውስጥ 17ቱ በሄግ በቁጥጥር ስር የሚገኙ ሲሆን፤ 10ሩ በወንጀል ተከሳዋል እንዲሁም አራቱ ክሳቸው ተቋርጧል።

የፑቲን ክስ በዩክሬን ለሚካሄደው ጦርነት ምን ማለት ነው?

በፕሬዝዳንቱ ላይ የወጣው የእስር ማዘዣ በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጻረር ስለመሆኑ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንደ ምልክት እየታየ ነው።

ፍርድ ቤቱ መጀመሪያ ላይ የእስር ማዘዣውን በምስጢርነት ሊይዘው አስቦ የነበረ ቢሆንም፣ ተጨማሪ ወንጀሎች እንዳይፈጸሙ እና እንዲቆሙ ለማድረግ በሚል ለሕዝብ ይፋ ለማድረግ ወስኗል።

ሩሲያ የፍርድ ቤቱን እርምጃ ውድቅ ያደረገችው ሲሆን፣ ትርጉም የለሽም ነው ብላለች።

ሩሲያ በዩክሬን ፈጽማዋለች የሚባሉ መጠነ ሰፊ ጥሰቶች የማትቀበል ሲሆን፣ የፕሬዝዳንት ፑቲን ቃለ አቀባይ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ “አሳዛኝ እና ተቀባይነት የሌለው” ብለውታል።

ፍርድ ቤቱ እንዲህ ዓይነት ፈተናዎች በተጋረጡበት ሁኔታ የወሰደው እርምጃ በዩክሬን ጦርነት ላይ ተጽእኖ ላያመጣ እንደሚችል እና የፕሬዝዳንት ፑቲንም "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" እንደሚቀጥልም እየተነገረ ይገኛል።