ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቻይና የስለላ አውሮፕላን የአየር ክልሌን ጥሷል ስትል ጃፓን ከሰሰች
የቻይና የስለላ አውሮፕላን የአየር ክልሌን ጥሷል ስትል ጃፓን ከሰሰች።
ቻይና የጃፓንን የአየር ክልል በይፋ ጥሳለች ተብሎ ክስ ሲቀርብባት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
የቻይና ዋይ-9 የተሰኘው የስለላ አውሮፕላን በዳንጆ ደሴቶች ላይ የጃፓንን ግዛት የአየር ክልል ጥሶ የገባውም ሰኞ አምስት ተኩል ገደማ ነው።
ይህንንም ተከትሎ ጃፓን ተዋጊ ጄቶቿን በተጠንቀቅ አሰማርታለች ተብሏል።
የጃፓን የካቢኔ ዋና ጸሃፊ ይህንን ጥሰት “ፍጹም ተቀባይነት የለውም” በማለት አውግዘው በቶኪዮ የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ባለስልጣንንም ጠርተው አነጋግረዋቸዋል ተብሏል።
የአሁኑ ክስተት የተሰማው በቀጣናው ውጥረት እየጨመረ መምጣቱ በተሰማበት ወቅት ነው። ቻይና እና አሜሪካ ከአጋሯ ጃፓን ጋር በመሆን በከባቢው ላይ የበላይነትን ለማግኘት እየተወዳደሩ ይገኛሉ።
ቻይና የአየር ክልል ጥሰቱን ክስ በተመለከተ የሰጠችው ይፋዊ ምላሽ የለም።
ሰኞ እለት የተፈጸመው የአየር ክልል ጥሰት ለሁለት ደቂቃዎች የቆየ ሲሆን በዚህም ወቅት ጃፓን ለቻይናው የስለላ አውሮፕላን ማስጠንቀቂያ መስጠቷ ተገልጿል። ለማስጠንቀቂያነት የሚውለው እሳት የሚተፋው ሽጉጥ ሆነ ሌሎች መሳሪያዎች ጥቅም ላይ አለመዋላቸውን የጃፓን ብሮድካስቲንግ ኤንኤች ኬ ዘግቧል።
ጃፓን በቅርቡ የይገባኛል ጥያቄ በሚነሳባቸው ቻይና ዲያዩስ ተብሎ በምትጠራው በምስራቅ ቻይና ባህር በሚገኙ የሴንካኩ ደሴቶች ላይ የቻይና መርከቦች መሰማራታቸውን አስታውቃ ነበር።
ቻይና የግዛቶቼ አካላት ናቸው በምትላቸው ታይዋን እንዲሁም ደቡባዊ የቻይና ባህር ላይ ያላትን የባለቤትነት መብት ጠንከር ባለ ቃላት እየገለጸች ትገኛለች።