የታዋቂዋ አሜሪካዊት ዘፋኝ ማሪያ ኬሪ እናት እና እህት በአንድ ቀን ሞቱ

የታዋቂዋ አሜሪካዊት ሙዚቀኛ ማሪያ ኬሪ እናት ፓትሪሺያ እና እህቷ አሊሰን በአንድ ቀን ከዚህ ዓለም በሞት መሰናበታቸውን ዘፋኟ አስታወቀች።

“ባለፈው ሳምንት መጨረሻ እናቴ በመሞቷ ልቤ በጣም ተሰብሯል” ስትል ሰኞ ዕለት መግለጫ የለቀቀችው ማሪያ ኬሪ አክላ “በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ እህቴም በተመሳሳይ ቀን ሕይወቷን አጥታለች” በማለት ሐዘኗን ገልፃለች።

የግራሚ ሽልማት አሸናፊዋ ሙዚቀኛ እናቷ ከመሞቷ በፊት በነበረው ሳምንት አብራት ስላሳለፈች ዕድለኛ መሆኗን ተናግራ በሐዘኗ ወቅት ሰዎች እንዳይረብሿት ተማፅናለች።

ስለማሪያ ኬሪ እናት እና እህት ሞት ዝርዝር መረጃ እስካሁን አልወጣም።

አየርላንዳዊ-አሜሪካዊ የሆኑት የ87 ዓመቷ የማሪ ኬሪ እናት ፓትሪሺያ የኦፔራ ሙዚቃ አቀንቃኝ ነበሩ።

ማሪያ ኬሪ በአውሮፓውያኑ 2020 ባሳተመችው የግል ሕይወቷን በሚተርከው ‘ዘ ሚኒንግ ኦፍ ማሪያ ኬሪ’ በተሰኘው መፅሐፏ ከእናቷ ጋር ያላትን ግንኙነት ውስብስብ በመሆኑ ምክንያት “ብዙ ስቃይ እና ግራ መጋባት” ማስተናገዷን አትታ ነበር።

አምስት ጊዜ ግራሚ የተሰኘውን የሙዚቃ ሽልማት ያሸነፈችው ማሪያ ኬሪ በእናቷ እና በእሷ መካከል አንዳች ፉክክር እንደነበር በመፅሐፏ ትናገራለች።

የ55 ዓመቷ ማሪያ ኬሪ ምንም እንኳን ከእናቷ ጋር ያላትን ግንኙነት ፍፁም ባይሆን በጣም እንደምትወዳት መፅሐፏ ላይ ታትሞ ተቀምጧል።

“እናቴ ፓት በዚያ ሁሉ ውጥንቅጥ ውስጥ የቻላትን አድርጋ አሳድጋኛለች። ምንም ጊዜም ቢሆን በቻልኩት አቅም እወድሻለሁ።”

ማሪያ ኬሪ በ2022 በሰጠችው ቃለ-መጠይቅ ልጅ ሳለች እናቷ በምትሰጣት አስተያየት ትነካ እንደነበር ተናግራለች። ቢሆንም እናቷ ለሙዚቃ ሕይወት ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳደረገችላትም አትክድም።

ኬሪ ከ63 ዓመቷ ታላቅ እህቷ አሊሰን ጋር ያላትም ግንኙነት እንዲሁ የተወሳሰበ ነው።

መፅሐፏ ላይ ከታላቅ እህቷ እንዲሁም ከታላቅ ወንድሟ ሞርጋን ጋር ለረዥም ጊዜ ሳትገናኝ እንደቆየች የጠቀሰች ሲሆን “ለኔ ስሜት መልካም የሚሆነው ነገር ምንም ዓይነት ግንኙነት አለመመስረት ነው” ብላለች።

ይህ መፅሐፍ ከታተመ በኋላ አሊሰን እህቷ ማሪያ ኬሪ “የስሜት መረበሽ” ስላስከተለችባት እንዲሁም መፅሐፉ “በቀል የሚታይበት ነው” በሚል 1.2 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፈላት በክስ መዝገብ ጠይቃ ነበር።

የታዋቂዋ አሜሪካዊት ዘፋኛ አባት አልፍሬድ በ72 ዓመታቸው በአውሮፓውያኑ 2002 በካንሰር ምክንያት ነው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት።

ማሪያ ኬሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ ስኬታማ ከሚባሉ የሙዚቃ ሰዎች መካከል ናት።

‘ኦል አይ ዋንት ፎር ክሪስማስ ኢዝ ዩ’ የተባለው ሙዚቃ በገና ሰሞን በጣም በርካታ ቅጂ በመሸጥ ከሴቶች ሙዚቀኞች አንደኛ አድርጓታል።

በቢልቦርድ 100 ምርጥ ዘፈኖች ዝርዝር ውስጥ 19 ዘፈኖቿ አንደኛ ሆነው በመቆየታቸው ምክንያትም ክብረ-ወሰኑን ይዛለች።

በዓለም ዙሪያ 220 ሚሊዮን ቅጅዎች የተሸጡላት ማሪያ ኬሪ ‘አሜሪካን አይድል’ በተሰኘው ውድድር ላይ ዳኛ ሆና አገልግላለች።