ኢትዮጵያውያን የተገደሉበት አሜሪካ በየመን የስደተኞች ማቆያ ላይ የፈጸመችው ጥቃት እንዲመረመር አምነስቲ ጠየቀ

በአሜሪካ በተፈጸመው እና ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካታ ስደተኞች የተገደሉበት የየመን የስደተኞች ማቆያ የአየር ጥቃት እንዲመረመር አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ።

አሜሪካ በሰሜን ምዕራብ የመን የሚገኘው የሳዓዳ የስደተኞች ማቆያ ማዕከል ሚያዝያ 20/2017 ዓ.ም. የፈጸመችው ጥቃት በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ሕግ ጥሰትነት ምርመራ ሊደረግበት እንደሚገባ ተቋሙ ግንቦት 11/2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ጠይቋል።

አሜሪካ ጥቃቱን በፈጸመችበት ወቅት በስደተኞች ማቆያ ማዕከሉ 115 አፍሪካውያን ስደተኞች እንደነበሩና ከእነዚህ 68ቱ በጥቃቱ መገደላቸውን እና 47 እንደቆሰሉ በሁቲ የሚተዳደረው የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።

ቢቢሲ ያናገራቸው ኢትዮጵያውን እንደሚሉት በጥቃቱ ከተገደሉት እና ከቆሰሉት በርካቶቹ አንዳንዶቹም ሁሉም ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ያምናሉ።

በጥቃቱ ከተገደሉት ኢትዮጵያውያን መካከልም ሦስት የአጎት እና የአክስት ልጆች በአንድ ላይ ሕይወታቸው ማለፉን ቢቢሲ ከቤተሰቦቻቸው ለመረዳት ችሏል።

አሜሪካ ከመጋቢት ጀምሮ በጦርነት በደቀቀችው የመን ላይ እየፈጸመችው ባለው ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን እንዲሁም መቁሰላቸው ሪፖርት መደረጉን የመብት ተቆርቋሪው በመግለጫው አስፍሯል።

አምነስቲ ባደረገው የሳተላይት ምሥሎች ትንተና አሜሪካ በፈጸመቻቸው የአየር ጥቃቶች በሰዓዳ ማረሚያ ግቢ ውስጥ የስደተኞች ማቆያ ማዕከል እንዲሁም በስፍራው ያለ ሌላ ህንጻ መመታቱን ለይቷል።

በሳዓዳ ግዛት የሚገኘውን የሪፐብሊካን እና አል ታልህ አጠቃላይ ሆስፒታልን የጎበኙ የዓይን እማኞች ለአምነስቲ እንደተናገሩት በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የከፋ የአካል መጉደል እና የአጥንት ስብራትን ጨምሮ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።

አንደኛው የዓይን እማኝ በሪፐብሊካን ሆስፒታል 25 እንዲሁም በአልታላህ ዘጠኝ የቆሰሉ ስደተኞች መመልከታቸውን ገልጸዋል።

ሁለቱንም ሆስፒታል የጎበኙ እና በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ያነጋገሩ ሌላ እማኝ በበኩላቸው "ከሌሊቱ አስር ሰዓት በመጀመሪያው ሚሳኤል ሲመቱ ተኝተው እንደነበር ነገሩኝ። ሲነቁም ዙሪያቸው በተቆራረጡ አስክሬኖች ተከበው ነበር። ድንጋጤ እና መሸበር ፊታቸው ላይ ይነበባል። አንዳንዶቹም በደረሰባቸው ድንጋጤ መናገር ተስኗቸዋል" ብለዋል።

በሆስፒታሎቹ የሚገኙ የአስክሬን ማቆያ ስፍራዎች በመሙላታቸው ምክንያት በአየር ጥቃቱ የሞቱ ግለሰቦች አስክሬን ውጭ ላይ ተደርድሮ እንደነበር አምነስቲ የዓይን እማኞችን ዋቢ አድርጓል።

ሳዓዳ ግዛት ውስጥ በሚገኘው ማዕከል ላይ በተፈጸመው ጥቃት የሞቱት እና የቆሰሉት ሰዎች አፍሪካውያን ስደተኞች ከመሆናቸው ውጪ በትክክል ከየትኞቹ አገራት የመጡ እንደሆኑ የታወቀ ነገር ባይኖርም፤ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ሳይሆኑ እንዳልቀሩ ቢቢሲ የመን ውስጥ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን አረጋግጧል።

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ከአፍሪካውያን ስደተኞች ጋር የሚሠሩ ሦስት ግለሰቦች በበኩላቸው በዚህ የማቆያ ስፍራ የነበሩት ከአንድ ኤርትራዊ በስተቀር ሁሉም ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአሜሪካ የአየር ጥቃትን ተከትሎ የስደተኛ ማቆያ ማዕከሉን፣ ሆስፒታሎችን እንዲሁም የአስከሬን ማቆያ ስፍራን ከጎበኙ በየመን ከሚገኙ የአፍሪካ ስደተኞች ጋር የሚሠሩ ግለሰቦች በርካታ ሰዎች መገደላቸውን መስማቱን አምነስቲ በዚሁ መግለጫው ላይ አስፍሯል።

ተቋሙ በስፍራው የወደቁ አስክሬኖች እንዲሁም የነፍስ አድን ሠራተኞች በከፋ ሁኔታ የቆሰሉ ሰዎችን ከተቀበሩባቸው ፍርስራሾች ስር ለማውጣት የሚሞክሩበት አሰቃቂ የሳተላይት ምሥሎች እና ቪዲዮዎችን ፈትሿል።

ጥቃቱን ተከትሎ በስፍራው የነበሩ የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ሠራተኞች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሟቾች መመልከታቸውን አብዛኞቹም ስደተኞች መሆናቸውን ማረጋገጣቸውን ተቋሙ ያወጣውን መግለጫ አምነስቲ ጠቅሷል።

"አሜሪካ ሁቲዎች መጠለያ የሌላቸው ስደተኞችን የሚያቆዩበትን ታዋቂ ማዕከል ላይ የአየር ጥቃት ፈጽማለች። ሰላማዊ ዜጎች በዚህ ጥቃት መገደላቸው፤ አሜሪካ በዓለም አቀፉ የሰብዓዊ ሕግ መሠረት ጥንቃቄ እና መለየትን ጨምሮ የተጣሉባትን ግዴታዎችን ተወጥታ ይሆን የሚለው አሳሳቢ ስጋቶችን የሚጭር ነው" ሲሉ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዋና ፀሐፊ አግነስ ካላማርድ ተናግረዋል።

"አሜሪካ ይህንን የአየር ጥቃትን ጨምሮ ሲቪሎች የተገደሉበት እንዲሁም የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ሕግ ተጥሶ ሊሆኑ የሚችሉበት የአየር ጥቃት በአስቸኳይ ገለልተኛ እና ግልጽ የሆነ ምርመራ ልታደርግ ይገባል" ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የአሜሪካ ወታደራዊ ማዕከላዊ ዕዝ የጥቃቱን ዒላማ ባያስታውቅም የአገሪቱ መከላከያ ባለሥልጣን በጥቃቱ ሞተዋል የተባሉ ሲቪሎችን ጉዳይ እንዲሁም የጉዳቱን ግምገማ እያካሄዱ መሆናቸው በዚሁ መግለጫ ላይ ተጠቅሷል።

ግምገማውን እንዲሁም ከሲቪሎች ጉዳት ጋር የተያያዙ ማናቸውንም ድምዳሜዎች እንዲሁም ሊሰጡ የሚችሉ ምላሾች በአስቸኳይ ለሕዝብ ይፋ ሊደረግ እንደሚገባ ነው አምነስቲ የገለጸው።

አሜሪካ የሰዓዳ እስር ቤት ሁቲዎች ስደተኞችን ለማቆየት ይጠቀሙበት የነበረ እንዲሁም በመደበኛነት በዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል የሚጎበኝ የስደተኞች ማቆያ ማዕከል እንደሆነ ማወቅ እንደነበረባትም ነው አምነስቲ በዚሁ መግለጫ አጽንኦት የሰጠው።

በተጨማሪም ማንኛውም በዚህ ማዕከል ላይ የሚፈጸም የአየር ጥቃት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርስ አሜሪካ ልታውቅ እንደሚገባም አምነስቲ አትቷል።

በዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ መሠረት ተፋላሚ ወገኖች ወታደራዊ እና ሲቪል ዒላማዎችን መለየት ብቻ ሳይሆን ወታደራዊ ዒላማ መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው።

እንዲሁም ጥርጣሬዎች የሚያጭሩ ከሆነ ጥቃቶቹን የመሰረዝ ግዴታ አለባቸው። ተፋላሚዎች ወታደራዊ ዒላማ ላይ ጥቃት በሚያደርሱበት ወቅት በስፍራው ባሉ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ጉዳቶችን ለመቀነስ ሁሉንም ጥንቃቄዎች ማድረግ እንደሚገባ ይደነግጋል።

በሲቪሎች ላይ ጉዳት መድረሱ ከተረጋገጠ ተጎጂዎች እንዲሁም ቤተሰቦቻቸው ለደረሰባቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግ ጥሰት ሙሉ ካሳ ሊያገኙ እንደሚገባ አመልክቷል።

በሲቪሎች እና በሲቪሎች ንብረቶች ላይ ላይ ቀጥተኛ ጥቃቶችን ወይም ወታደራዊ ዒላዎችን ባልለየ መልኩ ጥቃቶችን በመፈጸም ሰላማዊ ነዋሪዎችን መግደል ወይም ማቁሰል ከተረጋገጠ የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት ወይም የጦር ወንጀል ተደርጎ ይወሰዳል።

አምነስቲ በሰዓዳ የማረሚያ ቤት ግቢ ውስጥ ሕጋዊ የሆነ ወታደራዊ ዒላማን መለየት እንደተቸገረም አስፍሯል።

ከጥቃቱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ከሚያዝያ 7/2017 ዓ.ም. ጀምሮ በየመን ከ800 በላይ ዒላማዎችን መምታቱን ገልጾ፣ ለደኅንነት ሲባል ስለ ጥቃቶቹ መረጃዎችን ከመግለጽ እንደታቀበ ጠቅሶ ነበር።