በድምጽ ቆጠራ ወቅት ጠፍቶ የነበረው የኬንያ ምርጫ አስፈጻሚ አስክሬኑ ተገኘ

የዛሬ ሳምንት የተካሄደውን የኬንያ ጠቅላላ ምርጫ ተከትሎ አድራሻው ጠፍቶ የቆየው ምርጫ አስፈጻሚ ሕይወቱ አልፎ ተገኘ።

ዳንኤል እምቦሉ ሙስዮካ የተባለው የኬንያ ገለልተኛ የድንበር እና ምርጫ ኮሚሽን ሠራተኛ ተመድቦ ከነበረበት ናይሮቢ ከተማ ርቆ በሚገኝ ቦታ አስክሬኑ ጫካ ውስጥ ተጥሎ ተገኝቷል።

ግለሰቡ የተገደለው ከሥራው ጋር በተያያዘ ስለመሆኑ በይፋ የተባለ ነገር የለም። በግድያውም ተጠርጥሮ የተያዘ የለም።

ፖሊስ የግለሰቡ ማንነት በቅርብ የቤተሰብ አባላት መረጋገጡን ገልጾ ለግለሰቡ ሞት ምክንያት ምን እንደሆነ ለመረዳት የአስክሬን ምርመራ ይደረጋል ብሏል።

በርካታ ኬንያዊያን በማሕበራዊ ሚዲያዎች ላይ በምርጫ ውጤት ላይ ሕጋዊ ባልሆነ መልኩ ጫና ማሳደር የፈለጉ የኮሚሽኑን ሠራተኛ ገድለው ጥለዋል የሚሉ መላ ምቶችን በስፋት እየሰጡ ነው።

ትናንት የድንበር እና ምርጫ ኮሚሽን ሰብሳቢ ዋፉላ ቼቡካቲ የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤቱን ይፋ ሲያደርጉ በኮሚሽኑ ሠራተኞች ላይ ማስፈራራቶች፣ ዛቻ እና ያለ ሕግ መታሰር አጋጥሟል ብለው ነበር።

ትናንት ይፋ በተደረገው ውጤት መሠረት ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ተቀናቃኛቸውን ራይላ ኦዲንጋን በጠባብ ውጤት አሸንፈዋል።

ትናንት ነሐሴ 9/2014 ዓ.ም. የድንበር እና ምርጫ ኮሚሽን ሰብሳቢ ውጤቱን ይፋ በሚያደርጉበት ማዕከል ውጥረት እና ውዝግብ ተከስቶ ነበር።

በምርጫው ተሸንፈዋል የተባሉት ራይላ ኦዲንጋ የምርጫውን ውጤት አለቀበልም ስለማለታቸው የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን አባላቸው ለቢቢሲ ተናግሯል።

ሳሊም ሎን የተባለው የራይላ ኦዲንጋ አጋር፤ ኦዲንጋ የምርጫ ውጤቱን “በጭራሽ አይቀበሉትም” ካለ በኋላ ከሰባቱ የገለልተኛ የድንበር እና ምርጫ ኮሚሽን ኮሚሽነሮች መካከል አራቱ በውጤቱ አለመስማማታቸውን በመግለጽ የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር መሸነፋቸውን አይቀበሉም ብለዋል።

ትናንት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤትን ዋፉላ ቼቡካቲ ይፋ ከማድረጋቸው በፊት ኮሚሽኑ ካሉት ሰባት ኮሚሽነሮች መካከል አራቱ ይፍ ለሚደረገው የምርጫ ውጤት ኃላፊነት አንወስድም ሲሉ መግለጫ ሰጥተው ነበር።

አራቱ ኮሚሽነሮች ማብራሪያ ሳይሰጡ የምርጫ ሂደቱ ግልጸኝነት ይጎድለዋል ብለዋል።

ለራይላ ኦዲንጋ ድጋፋቸውን የሰጡት ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ምርጫው ከተካሄደ ጀምሮ በይፋ አልታዩም በምርጫው ላይም አስተያየት አልሰጡም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አሸናፊ ተብለው በታወጁት ዊሊያም ሩቶ ትውልድ ከተማ ኤልዶሬት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አደባባይ ወጥተው ደስታቸውን በጭፈራ ሲገልጹ ታይተዋል።

በርካታ የኦዲንጋ ደጋፊዎች በሚገኙበት ኪሱሙ ግዛት ደግሞ በሕዝቡ ውስጥ ያለው ስሜት የተለያ ነው። በምርጫ ውጤቱ ደስተኛ ያልሆኑት ደጋፊዎች መንገድ በመዝጋት ጎማ ሲያቃጥሉ ታይተዋል። የተቀሩት ደግሞ ራይላ የሚሰጡትን መግለጫ እየተጠባበቁ መሆኑን ገልጸዋል።