ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በርካታ መሰናክሎችን አልፈው ድልን የተቀናጁት የኬንያ ተመራጩ ፕሬዚዳንት
የኬንያ ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በምሥራቅ አፍሪካዊቷ ኬንያ ላይ ከፍተኛ ፉክክር ባስተናገደው ምርጫ በማሸነፍ የተጠበቁ ውጤቶችን ፉርሽ አድርገዋል።
ያሸነፉበት ውጤት ልዩነት በጣም የጠበበ፣ አስደናቂ እንዲሁም ከምርጫ ኮሚሽኑ ሰባት አባላት መካከል አራቱ የምርጫውን ውጤት አንቀበልም በሚል ውድቅ ማድረጋቸው አወዛጋቢ አድርጎታል።
በዋናው የድምጽ መቁጠሪያ ማዕከል ቦማስ የተመሰቃቀሉ ትዕይንቶች ተስተናግደዋል። የኬንያ ምርጫ ኮሚሽን ኃላፊ ዋፉላ ቼቡካቲ ተመራጭ ፕሬዚዳንቱን ውጤት ሊያሳዉቁ በነበረበት ወቅት በመድረኩ ዙሪያ ሽኩቻ ተፈጠረ። ቼቡካቲ እስኪረጋጋ ድረስ የጠበቁ ሲሆን የፀጥታ ኃይሎችም ሲራወጡ ታይተዋል።
ቼቡካቲ በኋላ ተመልሰው መጥተው ዊሊያም ሩቶ አምስተኛው የኬንያን ፕሬዝዳንትነት መንበሩን ማሸነፋቸውን ገልጸው ምርጫው ነጻ እና ፍትሃዊ መሆኑን አበክረው ተናግረዋል።
ይፋዊ ውጤቱ እንደሚያሳየው ሩቶ ዋነኛ ተቀናቃኛቸው በሆኑት ራይላ ኦዲንጋ ጠንካራ ይዞታም ድል ተቀዳጅተዋል።
በተጨማሪም ከራይላ ጋር በምክትልነት የተወዳዳሩት ማርታ ካሩዋ እንዲሁም የተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የፖለቲካ እምብርት በሆነችው ማውንት ኬንያ ያገኙት ድምጽ ከፍተኛ ነው።
እነዚህ ያልተጠበቁ ሁነቶች ዊሊያም ሩቶን አሸናፊ አድርገዋቸዋል።
ሩቶ በሁለቱ ታላላቅ የፖለቲካ ስርወ መንግሥት ኦዲንጋዎችና፣ ኬንያታ ቁጥጥር ስር ናት በሚሏትም አገራቸው ኬንያ፣ የሁለቱን ቤተሰቦች በሥልጣን ለመቆየት መታገላቸውንና ራሳቸውንም ከዝቅተኛ ቦታ ተነስተው ከፍ ያለ ቦታ ደረጃ ላይ እንደደረሱ አድርነው ነው የሚመለከቱት።
ይህ ትርክታቸውም በበርካታ ኬንያውን ወጣቶች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት አስገኝቶላቸዋል።
የ55 ዓመቱ ዊሊያም ሩቶ በዚህም ምርጫ ከፍተኛ ተፎካካሪ የሚባሉት ዕጩ ናቸው የገጠሟቸው። በተጨማሪም ራይላ ኦዲንጋ ባልተለመደ ሁኔታም የረዥም ጊዜ ተቀናቃኛቸው የነበሩት ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታም ድጋፋቸውን ሰጧቸው።
ኡሁሩ በምርጫ ዘመቻው ወቅት ዊሊያም ሩቶን “የማይታመኑ” ናቸው ሲሉ ወርፈዋቸዋል። አሁን ያ ሁሉ አልፎ ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ኩራታቸውን ዋጥ አድርገው በአንድ ወቅት ምክትላቸው ለነበሩት ዊሊያም ሩቶ ሥልጣናቸውን ማስረከብ አለባቸው።
ሆኖም ውጤቱን የራይላ ኦዲንጋ ደጋፈዎች የተጭበረበረ ነው በሚል አልተቀበሉትም፤ ይህም የዚህ ምርጫ መጨረሻ አለመሆኑን ማሳያ ነው።
የራይላ ደጋፊዎች ብቻ አይደሉም አብዛኛዎቹ የምርጫ ኮሚሽነሮች፣ ከሰባቱ አራቱ ይህንን የምርጫ ውጤት “ግልጽነት የጎደለው በመሆኑ፣ ውጤቱን በኃላፊነት ለመውሰድ አንችልም” በማለት የራይላን ደጋፊዎች አቋም ያጠናከረ ንግግር አድርገዋል።
ቼቡካቲ ግን ውጤቱ የኬንያውያን ምርጫ የሚያንጸባርቅ ነው ሲሉ ጽኑ አቋማቸውን አሳውቀዋል።
“ማስፈራራት እና ትንኮሳዎች ቢደርሱብኝም እናንተ ፊት ለመቆም ችያለሁ። ኃላፊነቴን በአገሪቱ ሕገ መንግሥት መሰረት ተወጥቻለሁ” ሲሉ ቼቡካቲ ተናግረዋል።
የዊሊያም ሩቶ በጠባብ ልዩነት ማሸነፍ እንዲሁም በኮሚሽኑ ውስጥ ያለው መለያየት አገሪቱ መከፋፈሏን እንደሚያሳይ ምንም ጥርጥር የለውም።
በቀጣይም ዊሊያም ሩቶ እንዴት መንግሥታቸውን እንደሚመሰርቱ እና አገሪቱን በአንድነት እንደሚመሩም የቤት ሥራቸው ይሆናል።
ብሔር በኬንያ ፖለቲካ ውስጥ ትልቅ ስፍራ ያለው ከመሆኑ አንጻር ዊሊያም ሩቶ መንግሥታቸው የኬንያ ዋና ዋና ብሔሮችን በተለይም ኦዲንጋ የመጡበት ብሔር ሉዎን መወከሉን ማረጋገጥ አለባቸው።
የሉዎ ብሔር በኬንያ ታሪክ የፕሬዚዳንትነቱን ቦታ ተቆጣጥሮ አያውቅም እናም ከካለንጂን ብሔር የተወለዱት ዊሊያም ሩቶ አሸናፊ መሆናቸው ብሔሩ ከፖለቲካና ከመሪነት እንደተገለለ እንዲሁም ቁጣዎችን ሊፈጥር ይችላል።
ሩቶ በድል ንግግራቸው “ከሁሉም መሪዎች” ጋር እንደሚሰሩ እና አገሪቱ “አንድነት እና የበለፀገች” እንድትሆን እንደሚጥሩ ተናግረዋል።
አሸናፊው ከመታወጁ በፊት ራይላ ኦዲንጋን በስልክ አግተዋቸው እንደነበርና ውጤቱ ምንም ይሁን ምን መነጋገር እንዳለባቸው መስማማታቸውን ሩቶ ተናግረዋል።
ራይላ ኦዲንጋ እስካሁን በውጤቱ ላይ ምንም አስተያየት አስተያት ከመስጠት የተቆጠቡ ሲሆን፣ ውጤቱ በይፋ ከሚገለጽበት ስፍራም ድርሽ አላሉም።
ከዚህ ቀደም እንዳደረጉት ውጤቱን በፍርድ ቤት ይሞግቱት እንደሆነ እስካሁን ግልፅ አይደለም።
ራይላ ኦዲንጋ ከዚህ ቀደም በአራት ምርጫዎች ተሸንፈዋል።
በዘንድሮው ምርጫ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ለእሳቸው ከፍተኛ ቅስቀሳ በመካሄድ እና መራጮች ለሩቶ ድምፃቸውን እንዳይሰጡ በማሳሰባሰባቸው የአሁኑን ምርጫ ሊያሸንፉ ይችላል የሚል ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷቸዋል ነበር።
ፕሬዝዳንት ኡሁሩ በምርጫ ዘመቻው ወቅት ሩቶን በዚህ ምርጫ ለመደገፍ የገቡትን ቃል ማፍረሳቸውን አምነዋል። ምክትል ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶን ሹፌሩ እያሽከረከረ እያለ እቃዎችን ከመኪና እያወጣ ከሚጥል ረዳት ጋር በማነጻጸር ተግባራቸው ምክትል እንደሆነ አስረድተዋል።
ሩቶ በበኩላቸው ኡሁሩ ኬንያታ ራይላ ኦዲንጋን በመደገፍ የምርጫ ቅስቀሳ ያደረጉት “የአሻንጉሊት ፕሬዝዳንት” ስለሚፈልጉ ነው ብለው ያምናሉ።
የ77 ዓመቱ ራይላ ኦዲንጋ በሚቀጥለው በአውሮፓውያኑ 2027 ለሚካሄደው ምርጫ ለስድስተኛ ጊዜ ለፕሬዝዳንትነት ይወዳደሩ እንደሆኑ ግልጽ የሆነ ነገር የለም።
በአገሪቱ ካሉ ከፍተኛ የበቆሎ አምራቾች አንዱ የሆኑት ዊሊያም ሩቶ ለመጀመሪያ ጊዜ በተወዳደሩበት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ማሸነፍ ችለዋል። በአውሮፓውያኑ 2013፣ በ50 ዓመታቸው ፕሬዝዳንት የሆኑትን ኡሁሩ ኬንያታንም በመከተል ሁለተኛው ወጣት ፕሬዝዳንት ይሆናሉ።
ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት በገዥው ፓርቲ የወጣቶች ክንፍ ውስጥ በመሳተፍ የፖለቲካ ሕይወታቸውን 'ሀ' ብለው የጀመሩት ዊሊያም ሩቶ ኃይለኛ ተናጋሪም ናቸው። በዚህ የምርጫ ዘመቻ ወቅትም የበርካቶችን ቀልብ መሳብ ችለዋል።
በአገሪቱ የባሕር ጠረፍ፣ ምዕራብ እና ሰሜን ምሥራቅ ክፍሎች የሚገኙትን የኦዲንጋ ደጋፊ ይዞታዎችንም ድምጽ ማግኘት ችለዋል።
በኬንያ ከፍተኛ ድምጽ ሰጭ የሆነው የኩኩዩ ሕዝብ እምብርት በሆነውና የፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጠንካራ ይዞታ ማሸነፋቸው ድሉን ይበልጥ አስደናቂ አድርጎታል።
የሩቶ ፓርቲ በዚሁ ክልል ለፓርላማ፣ ለሴኔትና፣ ለአስተዳዳሪነት በተካሄደውም ምርጫ ከፍተኛውን ቦታ በማግኘት የኡሁሩ ኬንያታ ጁቢሊ ፓርቲን ማሸነፍ ችሏል።
በፕሬዝዳንታዊ ምርጫውም በማርታ ካሩዋና በኡሁሩ ኬንያታ የምርጫ ክልል ውስጥ ራይላ ኦዲንጋን አሸንፈዋል።
ከምርጫው በፊት በማውንት ኬንያ የሚገኙ ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ልጃቸውን ኡሁሩ ኬንያታን በአውሮፓውያኑ 2013 ምርጫ በመደገፍ የተገባውን ስምምነት እንደሚያከብሩ ነበር።
አሁን በኪኪዩ ሕዝብ ዘንድ ስማቸው ለጎደፈው ለተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ይህ ኡሁሩ አሳፋሪ ውድቀት ነው።
የሽማግሌዎች ማኅበር ሰብሳቢ የሆኑት የኡሁሩ የአጎት ልጅ ሩቶን እንደሚደግፉ ተናግረዋል።
የሩቶ ድል በአብዛኛው የድጋፍ መሰረታቸው በሆነው ወጣቱ ዘንድ ከፍተኛ ደስታን ያስገኘ ነው።
ሩቶ “ሃስለር ኔሽን” የሚለውን ሐረግ የፈጠሩት ኑሮሯቸውን ለማሸነፍ ደፋ ቀና እያሉ የሚታገሉ ወጣቶች ለማመላከት ሲሆን፣ ለአገራቸው ምጣኔ ሀብትም ከታች ወደ ላይ የሚሄድና ድሆችን የሚጠቅም ስትራቴጂ እንደሚከተሉ ቃል ገብተዋል።
ፕሬዝዳንቱ የገቡትን ቃል መፈጸምም ይኖርባቸዋል።
በኬንያ ከ18 እስከ 34 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ያለው የሥራ አጥ ቁጥር 40 በመቶ የሚጠጋ መሆኑ ኢኮኖሚው በየዓመቱ 800 ሺህ ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስችል በቂ ሥራ እየፈጠረ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ ፈታኝ ሥራ ይጠብቃቸዋል።