ቴይለር ስዊፍት "የማደርጋቸውን በረራዎች የሚከታተለውን ተማሪ እከሳለሁ" ስትል አስፈራራች

እውቋ አቀንቃኝ ቴይለር ስዊፍት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቴይለር ስዊፍት

የታዋቂ ግለሰቦችን በረራ በመተከታተል በሚታወቀው ተማሪ ላይ ክስ እንመሰርታለን ሲሉ የእውቋ አቀንቃኝ ቴይለር ስዊፍት ጠበቃዎች አስፈራሩ።

የ21 ዓመቱ ጃክ ስዊኒ ማንኛውም ሰው ሊያገኘውን የሚችለውን መረጃ ተጠቅሞ የታዋቂ ሰዎች በረራን እየተከታተለ መነሻ እና መድረሻቸውን በማሕበራዊ ሚዲያው ላይ በመለጠፍ ይታወቃል።

ጠበቃዎቹ የተማሪው ተግባር የቴይለር ስዊፍትን ስሜት ከሚረብሽ መከታተል ጋር ይስተካከላል ይላሉ።

ከዚህ ቀደም ቴይለር ስዊፍት በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሴንትራል ፍሎሪዳ ተማሪ የሆነው ወጣት ከተግባሩ እንዲቆጠብ በጽሑፍ አስጠንቅቃው ነበር።

ኅዳር 2016 ዓ.ም. በላከችለት ደብዳቤ መነሻዋን፣ የበረራ አቅጣጫዋን እና መዳረሻዋን ማሕበራዊ ሚዲያ ላይ መለጠፉ “ለደኅንነቷ አደጋ” መሆኑን እና ጉዳዩ ለእርሷ “የሞት ወይም የሕይወት” መሆኑን ገልጻለች።

ደብዳቤው ላይ ጨምራ እንደጻፈችው እንቅስቃሴዋን ማሕበራዊ ሚዲያ ላይ መለጠፉ ወንጀለኛ ቡድኖች መገኛዋን በቀላሉ እንዲደርሱበት ሊያደርግ ይችላል ብላለች።

ቴይለር ስዊፍት በዚህ ወጣት ላይ ተመሳሳይ ክስ ያቀረበችው ብቸኛዋ ታዋቂ ግለሰብ አይደለችም።

የዓለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋው ኢላን መስክ "ሊገድሉኝ ለሚፈልጉ አድራሻዬን ይሰጣል" ሲል ከሶታል። ከዚያም ከትዊተር አግዶት ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የ21 ዓመቱ ጃክ ስዊኒ ግን መረጃዎቹን የማጋራው “ማንም ላይ ጉዳት እንዲደርስ አይደለም” ሲል ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ ሰጥቷል።

“እንደውም ስዊፍት ጥሩ ሙዚቃዎች እንዳሏት አስባለሁ። በግልጽነት እና መረጃ ለሕዝብ ይፋ መደረግ አለበት በሚለው አምናለሁ” ብሏል።

ጃክ ስዊኒ እንደሚለው ከሆነ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤው የደረሰው መገናኛ በዙሃን ቴይለር ስዊፍት በግል በምታደርጋቸው በረራዎች በከባቢ አየር ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት በተመለከተ ዘገባ ማውጣት ከጀመሩ በኋላ ነው።

ያርድ የተባለ የገበያ ጥናት ኩባንያ በ2022 በካርበን ልቀት በታዋቂ ግለሰቦች ዝርዝር ውስጥ ቴይለር ስዊፍትን አንደኛ አድርጎ አስቀምጦ ነበር።

ኩባንያው ከቴይለር ስዊፍት የግል ጀት የሚመነጫው የካርበን ልቀት አንድ አማካይ ሰው ከሚያመነጨው ካርበን በ1185 እጥፍ ይበልጣል ብሎ ነበር።

በቅርቡ ድምጻዊቷ በተለያዩ ከተሞች በምታደርጋቸው የሙዚቃ ድግሶች ምክንያት የአውሮፕላን ጉዞ እንቅስቃሴዋን የሚከታተሉ ሰዎች ቁጥር ከፍ ብሏል።

ስዊፍት የፊታችን እሁድ በቶኪዮ ጃፓን የሙዚቃ ድግስ ለማቅረብ አንድ ቀን እየቀራት እጮኛዋ በኤንኤፍኤል ሱፐር ቦል ሲጫወት ለመመልከት ወደ ላስ ቬጋስ እንደምትበር እቅድ ተይዟል።

ጃክ ስዊኒ ይፋ የሚያደርጋቸው መረጃዎች የየትኛው ተዋቂ ግለሰብ አውሮፕላን ከየት ተነስቶ የተ አረፈ የሚለውን እንጂ በአውሮፕላኖቹ ማን ተሳፍሯል እንዲሁም ታዋቂ ግለሰቦችስ በመዳረሻቸው ወደየት ሄዱ የሚለውን በተመለከተ መረጃ አያወጣም።

ስዊኒ የበረራ አቅጣጫቸውን ይፋ ከሚያደርግባቸው ግለሰቦች መካከል የማይክሮሶፍት መስራች ቢል ጌትስ፣ የአማዞኑ ጄፍ ቤዞስ እንዲሁም የሜታ ሥራ አስኪያጅ ማርክ ዙከርበርግ ይገኙበታል።