ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ስለ አዲሱ የገቢ ግብር አዋጅ የሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ምን ይላሉ?
የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ዝቅተኛው ከግብር ነጻ የሚሆነው ደሞዝ 8,324 እንዲሆን ቢጠይቅም፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2000 ብር አድርጎ ከወሰነ በኋላ ፓርላማው የወሰነውን ተቀብሎ እንደሚቀጥል አስታወቀ።
የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አሁን ያለው መፍትሄ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል መወሰን መሆኑን ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅት አስረድተዋል።
ከመንግሥት የተለያዩ ኃላፊዎች ጋር በረቂቅ አዋጁ ላይ ተደጋጋሚ ውይይት ማድረጋቸውን የሚናገሩት አቶ ካሳሁን ፎሎ፤ ምክር ቤቱ ያረቡትን ሃሳብ ሳይቀበለው ቀርቷል።
በዚህ ውሳኔ ላይ አስተያየታቸውን በቢቢሲ የተጠየቁት አቶ ካሳሁ "አሁን ባለው ሁኔታ ፓርላማው የወሰነውን መቀበል ነው። ይህ ነው በእኛ በኩል ያለው" በማለት ተናግረዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሁለት ሳምንት በፊት የቀረበውን የገቢ ግብር ረቂቅ አዋጅ ሐሙስ ሐምሌ 10/2017 ዓ.ም. ከደሞዝ የሚቆረጠውን ታክስ በተመለከተ ማስተካከያ ሳይደረግበት አጽድቋል።
ይህ አዋጅ ከግብር ነጻ የሚሆንን ደመወዝ ከነበረበት 600 ብር ወደ 2,000 ብር ከፍ አድርጓል።
በአገሪቱ ከፍተኛ የሆነው 35 በመቶ ግብር መጣል የሚጀምርበትን የደመወዝ መጠን ደግሞ ቀድሞ ከነበረበት 10,900 ብር ወደ 14 ሺህ ብር ከፍ አድርጓል።
ይህ ከዘጠኝ ዓመት በኋላ የተደረገው ማሻሻያ፤ ከግብር ነጻ በሚሆነው እና ከፍተኛ ግብር በሚጣልበት የደመወዝ መጠን ላይ ያደረገው ለውጥ ዝቅተኛ ነው የሚል ቅሬታ ቀርቦበታል።
የሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በዚህ የገቢ ግብር አዋጅ ላይ በተለይ ከደሞዝ የሚቆረጠው የገቢ ግብር፣ ከግብር ነጻ የሚሆነው ከፍ እንዲል ብዙ ለማስረዳት መሞከራቸውን ያስረዳሉ።
"ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ አስረድተናል። በዚሁ መሠረት ገንዘብ ሚኒስቴር አጥንቶ ባቀረበው ውይይት ላይ እዚያ ላይ ቀርበን አስተየየት ሰጥተናል" ሲሉ የነበረውን ሂደት ያስረዳሉ።
አቶ ካሳሁን ይህንኑ አስተያየታቸውን ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በጽሑፍም ማቅረባቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"መጀመሪያ በጥናቱ ቀርቦ የነበረው 1,200፣ 1,600 እና 2,300 የሚል ሦስት አማራጭ ነበር" የሚሉት አቶ ካሳሁን "በዚያ ላይ ቀርበን በቃልም ተከራክረናል። በኋላ ደግሞ በጽሑፍ ለገንዘብ ሚኒስቴር አቅርበናል" ብለዋል።
ከግብር ነጻ የሚሆነው ደመወዝ 2,000 እንዲሆን አጥንቶ ያቀረበው ገንዘብ ሚኒስቴር መሆኑን ያስታወሱት አቶ ካሳሁን፤ ይኽው ምክረ ሃሳብ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ መጽደቁን ይናገራሉ።
ከዚህ በኋላ ረቂቅ አዋጁ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲሄድ በድጋሚ ተገኝተው ያላቸውን አቋም በቃልም በጽሑፍም ማስረዳታቸውን የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ገልጸዋል።
"ለፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ [ያለንን አቋም] በጽሑፍ ልከናል። በግንባርም ቀርበን አስረድተናል። መጨረሻ ላይ ፓርላማው 2000 ላይ እንደወሰነ ይታወቃል።"
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐሙስ ሐምሌ 10/2017 ዓ.ም. አዋጁን ማጽደቁን ተከትሎ ቀጣዩ እርምጃቸው ምን እንደሚሆን የተጠየቁት አቶ ካሳሁን "መፍትሄው ዝቅተኛ ደሞዝ ላላቸው ሠራተኞች ዝቅተኛ የደሞዝ ወለልን መወሰን ነው" ብለዋል።
ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልን ለመወሰን መጀመሪያ የደሞዝ ቦርድ መቋቋም አለበት የሚሉት አቶ ካሳሁን፣ የደሞዝ ቦርድ የሚቋቋምበት ደንብ ሰነድ ላይ መወያየታቸውን ተናግረዋል።
በቃልም በጽሑፍም በደንቡ ላይ አስተያየታቸውን መስጠታቸውን ያስታወሱት ፕሬዝዳንቱ በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር በኩል ለጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ ተልኮ ይወጣል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
"ቢያንስ እርሱ በቅርቡ ይወጣል ብለን እናስባለን። ልክ ደንቡ እንደወጣ ስንት ነው መሆን የሚችለው የሚለውን ድርድር ማድረግ ነው የሚቀረው። እና ይኼ በቅርቡ ለሚኒስቴሮች ምክር ቤት ይቀርባል ብዬ አስባለሁ" ብለዋል።
ዝቅተኛ የደሞዝ መጠን ላይ እንዴት ተደረሰ?
አቶ ካሳሁን የገቢ ግብር አዋጁ ከመጽደቁ በፊት ከደሞዝ የሚቆረጠውን ታክስ በተመለከተ ምክረ ሃሳብ ሲያቀርቡ ያለውን ድህነት፣ የኑሮ ውድነት፣ የገንዘብ የመግዛት አቅም ከግምት ማስገባታቸውን ይናገራሉ።
ከዚህም ባሻገር የድህነት ወለል ተብሎ በአይኤምኤፍ በዓለም ባንክ የተቀመጠውን መመዘኛም መጠቀማቸውን ለቢቢሲ አስረድተዋል።
"አንድ ሰው በቀን ከ2.15 ዶላር በታች ካገኘ ድህነት ውስጥ ነው ያለው የሚል ነው" የሚሉት አቶ ካሳሁን ይህንን "የድህነት ወለልን ነው መነሻ ያደረግነው" ይላሉ።
ይህ ማለት በወር 64.50 ዶላር ማለት ነው የሚሉት አቶ ካሳሁን "ያኔ ጥያቄውን ስናቀርብ 64.50 ዶላር 8 ሺህ 324 አካባቢ ነበር። አሁን እንዲያውም ጨምሯል" ይላሉ።
ፍፁም ድህነት ውስጥ የሚገኙ ሠራተኞች ደሞዛቸው እስከ 8324 ድረስ ነጻ እንዲሆን ምክረ ሃሳብ አቅርበው የነበረ ቢሆንም መንግሥት ግን "ከምንሰበስበው ገንዘብ ልማት ለማስቀጠል፣ በተለይም ደግሞ በክልሎች ላይ ትልቅ ጫና ይፈጥርብናል" ማለቱን አቶ ካሳሁን ይናገራሉ።
ዝቅተኛ ደሞዝ የሚያገኙ ሠራተኞች በኑሮ ውድነቱ መጎዳታቸውን የመንግሥት ኃላፊዎችም "የካዱት ነገር አይደለም" የሚሉት ፕሬዝዳንቱ፤ የኑሮ ውድነቱ የታችኛው ተከፋይ ላይ የበረታ መሆኑ ሁሉም እንደሚረዳው ተናግረዋል።
"በድህነት ውስጥ ያለ ሰው የኑሮ ውድነቱን መቋቋም በልቶ ማደር አይችልም" የሚሉት አቶ ካሳሁን ፎሎ፤ ከምግብ ቤት ምግብ እየለመኑ ይበላሉ ስማለታቸው ሲጠየቁ ይህ የሚታየው በዝቅተኛ ተከፋይ በሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች ብቻ ሳይሆን በግልም ሠራተኞች ዘንድ ጭምር መሆኑን ተናግረዋል።
"በግል ተቋማትም ውስጥ በጣም ዝቅተኛ ተከፋይ ሠራተኞች አሉ። አሁን መንግሥት ከሚከፍለው በታች የሚያገኝ በግል ተቋማትም ውስጥ አለ። እነርሱንም ለማለት ነው። በግል ተቋማት ደግሞ ደሞዙ ከዚህም በታች ነው። 1200 የሚከፈለው አለ። 1000 የሚከፈለው አለ። 2000 ብር የሚከፈለው አለ። እነዚህን ጭምር በማየት ነው ያንን ያልኩት።"