በመንግሥት እና በህወሓት ወታደራዊ መሪዎች ሲካሄድ የነበረው ንግግር ውጤት ዛሬ ይፋ ይሆናል

በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት ወታደራዊ መሪዎች በዚህ ሳምንት ናይሮቢ ውስጥ ሲካሄድ የቆየው ንግግር ተጠናቆ ውጤቱ ዛሬ ቅዳሜ በሚሰጥ ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ ይደረጋል።

ሁለት ዓመት የሆነውን የሰሜን ኢትዮጵያውን የእርስ በርስ ጦርነት ለመቋጨት በመንግሥት እና በህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መካከል ደቡብ አፍሪካ ላይ የተፈራረሙን ስምምነት ተከትሎ ነው ንግግሩ ናይሮቢ ውስጥ የቀጠለው።

አርብ ዕለት መጠናቀቁ በተነገረው ንግግር ሁለቱም ወገኖች የደረሱበትን ዝርዝር ስምምነት ይፋ ባድረግ ፊርማቸውን ያኖራሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው።

ለዚህ ሥነ ሥርዓት ረፋድ ላይ ቀጠሮ ተይዞ የነበረ ቢሆንም እስከ ከሰዓት ዘጠኝ ሰዓት ድረስ እየተጠበቀ ይገኛል።

በሁለቱም ወገኖች በኩል የንግግሩ ተሳታፊዎች በስፍራው እንደተገኙ ቢቢሲ የተመለከተ ሲሆን፣ ሥነ ሥርዓቱ የሚካሄድበት ሰዓት እየተጠበቀ ነው።

ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ውስጥ ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. የተደረሰው ስምምነት ደም አፋሳሹን ጦርነት ለማብቃት በዘላቂነት ግጭትን ማስቆም፣ የእርዳታ አቅርቦት እና የመሠረታዊ አገልግሎቶች መጀመር እንዲሁም ትጥቅ መፍታትን የሚያካትት ነው።

በዚህ መሠረት ዋነኛው ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ሁለቱም ወገኖች በ24 ሰዓታት ውስጥ በከፍተኛ የጦር መሪዎቻቸው ንግግር እንደሚያደርጉ የተገለጸ ሲሆን፣ በአምስት ቀናት ውስጥ ደግሞ ትጥቅ የማስፈታቱ ሂደት ተግባራዊ በሚሆንበት ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር በወጣ መረሃ ግብር አማካይነት ነው ናይሮቢ ላይ ሲመክሩ የሰነበቱት።

ከሰኞ ጥቅምት 28/2015 ዓ.ም. ጀምሮ ናይሮቢ ውስጥ በዝግ መካሄድ የጀመረው ንግግር ለሦስት ቀናት የሚቆይ እንደሆነ ቢነገርም ለተጨማሪ ሁለት ቀናት ተራዝሞ እስከ አርብ ድረስ ዘልቋል።

በወቅቱ ዲፕሎማቶች እና የኬንያ የውጭ ጉዳይ ባለሥልጣናት ለቢቢሲ እንደተናገሩት እንደታሰበው ንግግሩ ጥቅምት 30/2015 ዓ.ም. እንደማይጠናቀቅና አስከ አርብ ሊቆይ እንደሚችል ገልጸው ነበር።

ንግግሩ ሲካሄድበት የቆየው የናይሮቢው፣ ካረን ሞራን ማዕከል ከሁለቱ ወገኖች እና ከአሸማጋዮች በስተቀር ማንም እንዲገባ ስላልተፈቀደ፣ አስካሁን በየዕለቱ ስለነበረው ሁኔታ፣ ስለንግግሩ ሂደት እና ስለተደረሰበት ውጤት የታወቀ ነገር የለም።

በንግግሩ መጀመሪያ ዕለት ሁለቱም ወገኖች አስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው የትግራይ ነዋሪዎች ያለ ገደብ እንዲቀርብ ማስቻል ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑንና መሠረታዊ አገልግሎቶች በፍጥነት ሥራ እንዲጀምሩ ይደረጋል ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን አርብ ዕለት በትዊተር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት፣ ከዚህ በፊት ከነበረው በተለየ ሁኔታ የእርዳታ አቅርቦት ወደ ትግራይ እየገባ መሆኑን ገልጸዋል።

ነገር ግን የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ይህን ያለው ሁኔታ እንደተባለው እንዳልሆነ ለፈረንሳይ ዜና ወኪል ተናገረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግሥት ወደ ትግራይ ክልል የሚወስዱ ሁሉም ኮሪደሮች ለሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ክፍት እንዲሆኑ መደረጋቸውን አርብ ዕለት አስታውቋል።

ይህንን ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማስቆም በመንግሥት እና በህወሓት መካከል የተደረሰውን ስምምነት እና አሁንም እየተካሄደ ያለውን ንግግር የመራው የአፍሪካ ኅብረት ነው።

በአሸማጋይነትም የናይጄሪያ እና የኬንያ የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች እንዲሁም የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ምክትል ፕሬዝዳንት ጉልህ ሚና ተጫውተዋል።