አሜሪካ እና ኢራን በመጀመሪያው ዙር የኒውክሌር ድርድር "ገንቢ ውይይት" ማካሄዳቸውን ገለፁ

ኢራን እና አሜሪካ በቴህራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ላይ በኦማን ያደረጉትን የመጀመሪያ ዙር ውይይት አጠናቀቁ።

ውይይቱ እአአ ከ 2018 ወዲህ በሁለቱ አገራት መካከል የተደረገ ከፍተኛ ደረጃ ያለው ስብሰባ ነው ተብሎለታል።

ሁለቱም አገራት ስብሰባው "ገንቢ" በማለት የገለፁት ሲሆን በሚቀጥለው ሳምንት ሁለተኛው ዙር ውይይት እንደሚካሄድ አረጋግጠዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ "የቀጥታ ውይይቱ" ከስምምነት ለመድረስ ቁልፍ ነው በማለት አወድሳዋለች።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በ2018 በኢራን እና የዓለም ኃያላን መንግሥታት ቀደም ሲል ተደረሰውን የኒውክሌር ስምምነት አሜሪካን በማስወጣት "የተሻለ" ስምምነት እንደሚያደርጉ ሲናገሩ ቆይተዋል።

ንግግሮቹ ስምምነት መድረስ ይቻል እንደሆነ ለማረጋገጥ እንደ አንድ አስፈላጊ የመጀመሪያ እርምጃ ታይተዋል።

ለሁለት ሰዓት ተኩል የቆው የመጀመርያው ስብሰባ አጭር ቢሆንም በአክብሮት የተሞላ እና ለሁለተኛው ዙር መድረኩን ያዘጋጀ ሆኗል።

ትራምፕ በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው አሜሪካን ከ2015ቱ የኢራን የኒውክሌር ስምምነት ካስወጧት በኋላ በጣም ጠቃሚ ንግግር ተብሏል።

የኢራን ዋና ተደራዳሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራግቺ የሰጡት አስተያየትም አዎንታዊ ነበር።

"በእኔ አስተያየት እንደ መጀመሪያው ስብሰባ በጣም ሰላማዊ እና መከባበር በተሞላበት መንገድ የተካሄደ ገንቢ ስብሰባ ነበር። ምክንያቱም ምንም አይነት ተገቢ ያልሆነ ቋንቋ አልነበረም" ሲሉ ለኢራን መንግሥት ቴሌቭዥን ተናግረዋል።

የኢራኑ ተደራዳሪ ዲፕሎማሲያዊ ቃላት እንደሚጠቁመው ከሆነ በትራምፕ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ የሚመራው የአሜሪካ ቡድን ይህ ውይይት ካልተሳካ ኢራን "ትልቅ አደጋ ሊደርስባት ይችላል" በማለት ፕሬዚዳንቱን ደጋግመው የተናገሩትን ዛቻ አለመጠቀሙን ነው።

ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ላይ ወታደራዊ ጥቃቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ በተደጋጋሚ አስጠንቅቀዋል።

ውይይቱ ሁለቱ ልዑካን በተለያየ ክፍሎች ሆነው፣ በኦማን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በድር ቢን ሀማድ አል ቡሰይዲ በኩል መልዕክቶችን በማስተላለፍ የተካሄደ ነበር።

የአሜሪካ ልዑካንን እየመሩ ያሉት ዊትኮፍ ከዚህ ቀደም ፊት ለፊት ስለመገናኘት ብቻ ተናግረው ነበር።

አራግቺ እና ዊትኮፍ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቡሳይዲ ባሉበት ለተወሰኑ ደቂቃዎች ተነጋግረዋል።

የአሜሪካ ባለስልጣናት ይኖራል ያሉት ቀጥተኛ ንግግር ሳይሆን አነስተኛ የመክፈቻ ንግግር ሊሆን የሚችል ነው።

ኢራን በአገር ውስጥ ያሉ አክራሪዎችን ጫና በማስታወስ የፊት ለፊት ንግግር የተገደበ እንደሆነ አስረድታለች።

ኋይት ሀውስ ከንግግሩ በኋላ በሰጠው መግለጫ ውይይቶቹ "በጣም አወንታዊ እና ገንቢ ነበሩ" ከማለት ባለፈ ልዩነቶችን "ከተቻለ በውይይት እና በዲፕሎማሲ ለመፍታት እንደሚፈለግ" አጽንኦት ሰጥተው ዊትኮፍ ለኢራን ገልፀዋል ብሏል።

መግለጫው አክሎም "እነዚህ ጉዳዮች በጣም የተወሳሰቡ ናቸው።ልዩ መልዕክተኛው ዊትኮፍ ቀጥታ ግንኙነት ማድረጋቸው የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ አንድ እርምጃ ነበር" ብሏል።

አራግቺ ከውይይቶቹ በፊት አገራቸው "ፍትሃዊ ስምምነት" እንደምትፈልግ ተናግረው ነበር።

ውይይቶቹ ከተጠናቀቁ በኋላ በሚቀጥለው ሳምንት ውይይቶች በኦማን ላይደረጉ ቢችሉም አሁንም በመካከለኛው ምሥራቅ አገር አሸማጋይነት ይካሄዳሉ ብለዋል። ኋይት ሀውስ ቀጣይ ውይይት በመጪው ቅዳሜ እንደሚካሄድ ተናግሯል።

አራግቺ ለኢራን መንግሥታዊ ቴሌቪዥን እንደተናገሩት "እኛም ሆንን ሌላኛው አካል ፍሬ አልባ ድርድር፤ ለውይይት ሲባል የሚደረግ ውይይት፤ጊዜ ማባከኝ ንግግሮችን አንፈልግም" ብለዋል።

ዋናው ጉዳይ ሁለቱ ወገኖች ምን ዓይነት ስምምነት ለመቀበል ፈቃደኛ ይሆናሉ የሚለው ነው ።

ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዳታበለጽግ ለመከላከል እና በአሜሪካ እና በእስራኤል ሊደርሱ የሚችሉ ወታደራዊ ጥቃቶችን ለመከላከል ስምምነት እንደሚፈልጉ በመግለጽ ትራምፕ ባለፈው ወር ለኢራን ሃይማኖታዊ መሪ በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ በኩል ደብዳቤ ልከዋል።

ኢራን የተጣለባትን ማዕቀብ በማንሳት የኒውክሌር መርሃ ግብሯን የሚገድብ እንጂ፣ የማያስቆም ስምምነት ላይ ለመድረስ ተስፋ አድርጋለች።

በኦማን የሚገኙ አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ምንጭ ለሮይተርስ እንደተናገሩት ከሆነ ውይይቱ በአካባቢው ያለውን ውጥረት ለማርገብ እና የእስረኞችን ልውውጥ ለማረጋገጥ ጥረት ያደርጋል።

ትራምፕ ውይይቱ እንደሚካሄድ የገለጹት ሰኞ ዕለት ቤንያሚን ኔታንያሁ ኋይት ሀውስን በሚጎበኙበት ወቅት ነው።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ማክሰኞ ዕለት እንዳሉት ሁለቱም መሪዎች ኢራን "የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዳይኖራት" ተስማምተዋል።

ኔታንያሁ በ2003 ከምዕራባውያን ኃያላን ጋር በተደረገው ስምምነት የሰሜን አፍሪካዊቷ ዐገር ሊቢያ የጦር መሣሪያ መርሃ ግብሯን ሙሉ በሙሉ የሚያስቆም ዓይነት ስምምነት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

ይህ ግን በኢራን በኩል ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም።

ኢራን የኒውክሌር እንቅስቃሴዋ ሙሉ በሙሉ ሰላማዊ እንደሆነ እና የኒውክሌር መሣሪያ መቼም እንደማትታጠቅ አጥብቃ ገልጻለች።

የኢራን ባለስልጣናት ድርድሩ የሚያተኩረው በኒውክሌር ፕሮግራሟ ላይ ብቻ እንጂ እንደ ባላስቲክ ሚሳኤል ፕሮግራም ባለው በተቀረው የመከላከያ አቅሟ ላይ እንደማይሆን ግልጽ አድርገዋል።

ከንግግሩ በፊት ኢራን "አስደናቂ፣ ታላቅ፣ ደስተኛ ዐገር እንድትሆን ነገር ግን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዲኖራት" እንደማይፈልጉ ትራምፕ አርብ ዕለት ተናግረዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ ስምምነት ላይ ካልተደረሰ ወታደራዊ ኃይል እንደምትጠቀም ትራምፕ አስጠንቅቀዋል። ኢራንም በበኩሏ በጫና ውስጥ ሆና እንደማትደራደር ደጋግማ ተናግራለች።

ይህ ሂደት ግን በከፍተኛ ጫና ውስጥ በመከናወን ላይ ነው።

ይህንን ስብሰባ ለማዘጋጀት ዝግጅት በሚደረግበት ወቅት አሜሪካ ተጨማሪ የጦር መርከቦችን እና ቦምብ ጣዮችን ወደ አካባቢው ከማዛወር ባለፈ ተጨማሪ ማዕቀቦችን ጥላለች።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ሰኞ ዕለት በኦቫል ኦፊስ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ውይይቱ ካልተሳካ "ለኢራን በጣም መጥፎው ቀን ነው" ብለው ነበር።