በመደበኛ የምግብ ሰዓቶች መካከል የምንቀማምሳቸው 'ስናኮች' አመጋገባችንን እንዴት ለወጡት?

በመደበኛ የምግብ ሰዓቶች ማለትም በቁርስ፣ በምሳ እና በእራት መካከል ቀለል ያሉ፣ ጣፋጭ እና ተዘጋጅተው የተቀመጡ ምግቦችን አፍ ላይ ጣል ማድረግ የተለመደ ነው።

እነዚህ ምግቦች በእንግሊዝኛ አጠራራቸው 'ስናክ' ይባላሉ።

እንደ የተቆላ ኦቼሎኒ፣ ችፕስ፣ ቸኮሌቶች፣ ብስኩቶች፣ዶናቶች እና ኬኮች ያሉ ጣፋጮች በብዛት የሚቀርቡ ስናኮች ናቸው።

እነዚህ ምግቦችን መመገብ የቅርብ ክስተት አይደለም። ሰዎች ለሺዎች ዓመታት ሲመገቧቸው ቆይተዋል።አሁን ባለንበት ዘመናዊው ዓለም ደግሞ በዓመት ከትሪሊዮን ዶላሮች በላይ የገበያ ዋጋ ያለው ኢንደስትሪ ሆኗል።

ብዙዎቻችንም አብዛኛውን ካሎሪያችንን የምናገኘው በቀን ውስጥ ሁለት ወይም ሦስት ጊዜ ከምንመገባቸው መደበኛ ምግቦች በበለጠ ከስናኮች ነው።

ይህን ንግድ ግዙፍ ገበያ እንዲሆን ያደረገው አምሮታችን እና ደካማ የአኗኗር ዘይቤያችን ብቻ አይደለም። የምግብ አምራች ኩባንያዎችም በአመጋገባችን ውስጥ ስናኮች እንዲበዙ የራሳቸውን ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል።

በጣም ጥንታዊው 'ስናክ' ምንድን ነው?

የኬምብሪጅ የእንግሊዝኛ መዘገበ ቃላት እንደሚለው ስናክ በመደበኛ የምግብ ሰዓቶች መካከል የምንመገባቸው አነስተኛ መጠን ያላቸው ምግቦች ናቸው።

ሆኖም ስናኮች ተዘጋጅተው የተቀመጡ እና ዝቅተኛ ጠቀሜታ ያላቸው ፈጣን ምግቦች ብቻ አይደሉም።

የእንግሊዝ የምግብ ታሪክ አጥኝ እና ፀሐፊ ዶ/ር አን ግሬይ እንደሚሉት የስናክ ዘመናዊ አረዳድ ብዙውን ጊዜ በጣም ተሳሳተ ነው።

"ስናክ ምግቦች በቀላሉ የምናገኛቸው እና በመደበኛ የምግብ ሰዓቶች መካከል የምንመገባቸው ምግቦች እንደሆኑ እናስባለን።ከዚህ ጋር በተያያዘም ጥፋተኝነት እንዳለ አስባለሁ" ይላሉ ዶ/ር ግሬይ።

ሆኖም ስናኮችን መመገብ አዲስ ክስተት እንዳልሆነ እና ለረዥም ጊዜ አብሮን የነበረ እንደሆነም ግሬይ ያስረዳሉ።

"በጣም ጥንታዊዎቹ ስናኮች ኦቾሎኒዎች፣ እንጆሪዎች እና ፍራፍሬዎች ሊሆኑ ይችላሉ።ዘመናዊ የሆነውን ስናክ ስናስብ በጣም ጥንታዊው ፈንድሻ ሊሆን ይችላል" ይላሉ።

ዶ/ር ግሬይ እንደሚሉት የሥነ ምድር ተመራማሪዎች የፈንዲሻን ፍሬ ያገኙት ከ7 ሺህ ዓመታት በፊት በደቡብ አሜሪካ ዋሻዎች ነው።

በታሪክ ውስጥ በተለያዩ ዘመኖች በመላው ዓለም ያሉ በርካታ ሰዎች መደበኛ ምግቦችን የሚመገቡበት ጊዜ አልነበራቸውም።ይህ ማለት ሰዎች ረሃብ በተሰማቸው ቁጥር በተመቻቸው ማንኛውም ጊዜ ይመገባሉ ማለት ነው።

በመሆኑም በሰው ልጅ ታሪክ ስናኮችን መመገብ የተለመደ ነበር።

ስናኮችን መመገብ የተጀመረው መቼ ነው?

ስናኮችን መመገብ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የተለመደ ከሆነ በመደበኛ የምግብ ሰዓቶች መካከል የምንመገባቸው ምግቦች አድርገን ያየናቸው መቼ ነው? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም።

ይህ ጥያቄ ስናክ የሚለው ቃል ጥቅም ላይ ወደዋለበት ዘመን ይወስደናል።

ቃሉ የተሰማው በዘመናዊው የሥልጣኔ ዘመን መጀመሪያ ላይ ነው።

"ስናክ የሚለው ቃል በእንግሊዝኛ ጥቅም ላይ መዋል የጀመረው "የሆነ ነገር አካል" ወይም 'ቁራሽ' በሚል ትርጓሜ ነበር" የሚሉት ዶ/ር ግሬይ፤ በውስጡ 'ማካፈል' የሚል ሃሳብን ያዘለ እንደሆነም ያስረዳሉ።

"ስለሆነም ከምግብ ጋር ብቻ የተያያዘ አልነበረም።የትርፍ ወይም የገንዘብ ጉርሻ [ስናክ] ሊኖራችሁም ይችላል" ይላሉ።

ከዚያን ጊዜ በኋላ ግን ቃሉ ከምግብ ጋር በፍጥነት መያያዝ ጀመረ። በኢንደስትሪው ውስጥ ያሉ ሠራተኞች "ርቦኛል የሆነ ቀለል ያለ ምግብ እጎርሳለሁ" ሲሉ መስማት እየተለመደ መጣ።

ሆኖም ዶ/ር ግሬይ እንደሚሉት ስናክ የሚለው ቃል በግልጽ ከመደበኛው የአመጋገብ ልምድ ወጣ ባለ መልኩ እና ከምግብ ጋር በተያያዘ ጥቅም ላይ የዋለው በ18ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ነበር።

ይህ ወቅት ሳንዲዊች የተባለው ቀላል ምግብ የተፈጠረበት ጊዜ ነበር።

ሳንድዊችን የፈጠሩት አራተኛው ኢርል ኦፍ ሳንዱዊች- ጆን ሞንታግ ናቸው።

ሞንታግ በአውሮፓውያኑ 1762 ቁማር እየተጫዎቱ ሳሉ ምንም እንኳን ቢርባቸውም አቋርጠው መውጣት አልፈለጉም ነበር።

በዚህ ጊዜ ሠራተኛቸውን በሁለት የተቆረሱ ዳቦዎች መካከል የተወሰነ ሥጋ አድርጋ እንድታመጣላቸው አዘዙ። "ይህም ዋነኛ የስናክ ትርጓሜን በግልጽ የሚያሳይ ነው" ይላሉ ግሬይ።

ሳንዱዊች ስያሜውን ያገኘውም ከእርሳቸው የክብር ማዕረግ ስም ነበር።

የኢንደስትሪዎችን መስፋፋት ተከትሎ በአሜሪካ ስናክ ምግብ አምራቾች የፋብሪካ ሠራተኞችን ዒላማ ማድረግ ጀመሩ። ወዲያው ለመመገብ የተዘጋጁ የስናክ ምግቦች በፋብሪካዎች ደጆች ታዩ። እንደ ኦይስተር እና ሳንዱዊች ያሉ ስናኮችም ይሸጡ ጀመር።

ከዚያም በ19ኛው ክፍለ ዘመን ፈንዲሻ በአሜሪካ ታዋቂው ስናክ ሆነ።ሌሎችም ተከተሉ።

"ደረቅ ብስኩት ዓይነት [ክሪፕስ] ለመጀመሪያ ጊዜ ገበያ ላይ የዋለው በ1910 ነው። ይህ ወቅት በርካታ ምግብ አምራቾች እና ኢንደስትሪዎች የተስፋፉበት ነበር" ይላሉ ግሬይ።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የታየው የምግብ ማቀነባበሪያ ወሳኝ የሆነ መስፋፋት እና የምግቦች አስተሻሸግ መሻሻል ምክንያት የስናክ ምግቦች በእጥፍ ጨምረዋል።

"በፈረቃ የሚሠሩ ሠራተኞች እና ምግብ ለማዘጋጀት ጊዜ የሌላቸው ከቤታቸው ውጭ የሚሠሩ በርካታ ሰዎች አሉ" የሚሉት ዶ/ር ግሬይ የኢንደስትሪው መስፋፋት፣ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች መበራከት፣ በሰዓት የሚፈጸሙ ክፍያዎች መኖር ሰዎች ገንዘባቸውን በስናኮች የማውጣት ልምድ እንዲጨምር ማድረጉን ያስረዳሉ።

በዚሁ ወቅትም የምግቦች አስተሻሽግ ቴክኖሎጂ እየዘመነ የመጣበት ነበር።

የስናክ ገበያ ምን ያህል ትልቅ ነው?

የአስተሻሸጋቸው እና የአገጃጀታቸው መዘመን ስናኮች እንዲሁም ተጠቃሚዎች እንዲበራከቱ ምክንያት ሆኗል።

እንደ የደረቅ ምግቦችን ማሸጊያ ፕላስቲክን በናይትሮጅን ጋዝ መሞላት ያሉ ትንንሽ ፈጠራዎችም በማጓጓዝ ወቅት ችፕሱ ሳይሰባበር ለማድረስ ረድተዋል።

በዚህም ምክንያት አምራቾች ምርቶችን፤ ጎን ለጎን ደግሞ ማሸጊያዎችን ማምረት ጀመሩ። ለዚህም ነው በጣም ትላልቅ ፋብሪካዎች በጥቂት ቦታዎች የሚገኙት።

እንደ አውሮፓውያኑ 1979 ፖል ፖልማን ግዙፉን የአሜሪካ ፕሮክተር እና ጋምብል የተባለ አምራች ኮርፖሬሽንን በተቀላቀሉ ጊዜ በዓለም የስናክ ምግቦች ዓለም ውስጥ 'ክሪስፕ' የተባለው ደረቅ ምግብ ገበያውን ተቆጣጥሮት ነበር።

ፖልማን በቅርቡም ከድንች የሚሠራ እና በጣሳ የሚታሸግ አዲስ ችፕስ መሥራት ጀመሩ።

በዚህ ጊዜ ትልልቅ ኩባንያዎች ትንንሽ ንግዶችን የተቆጣጠሩ ሲሆን፣ ገንዘባቸውንም ለብራንዳቸው እና ለማስታወቂያ አፍስሰው ነበር።

አሁን ላይ ፖልማን ኢንደስትሪውን "ከወታደራዊ ዘመቻ" ጋር ያወዳድሩታል።

"ስኬት በቀላሉ ሊመጣ ይችላል፤ ሆኖም ቶሎም ሊጠፋ ይችላል። በመሆኑም አዋጭ በሆነ ንግድ ላይ መሰማራት ያስፈልጋል። ምርቱ ጥራት፣ ተመጣጣኝ ዋጋ፣ ትክክለኛ አስተሻሸግ፣ የሚቀመጥበት ቦታ፣ ካስፈለገም ማስታወቂያ ሊኖረው ይገባል" ይላሉ።

ሆኖም የስናክ ፍጆታ እየጨመረ በመምጣቱ ዘርፉ አትራፊ ነው።

በዓለም ተወዳጅ የሆኑ ስናኮች የትኞቹ ናቸው?

ቢቢሲ ዓለም አቀፍ አገልግሎት አድማጮችን ሲርባቸው ምን መመገብ እንደሚፈልጉ በመጠየቅ ለስናኮች ያለንን ፍቅር ለመረዳት ሞክሯል።

አርጀንቲናዊቷ ባርባራ ኦይቫሪ "የምወደው ስናክ 'ቺፓ' ይባላል። በአነስተኛ መጠን ክብ ተደርጎ ከካሳቫ፣ ከአይብ፣ ከቅቤ፣ ከወተት እና ከጨው የሚሠራ ምግብ ነው። ልክ እንደ ጎልፍ ኳስ ያህል ከተድቦለቦለ በኋላ ተዳምጦ የሚጋገር ነው።"

ኦይቫሪ ስናኮችን ከመግዛት ይልቅ ማዘጋጀትን ትመርጣለች። ልጇ ግን ተዘጋጅተው የሚሸጡትን ነው የሚወደው።

"በሚገርም ሁኔታ ልጄ የሚወደው ቺዝ ተደርጎበት የተጋገረ ነገር ነው። እኔ ከምወደው ጋር ተመሳሳይ ነው። ጨዋማ ጣዕም ያለው ነገር መውደዱ ከእኔ የወረሰው መሆኑ ይገርማል። ልጅ እያለሁ እኔም እንዲህ ዓይነት ጣዕም ያለው ምግብ እወድ ነበር። ነገር ግን ያኔ - ድሮ የነበረውን ዓይነት ነው በጣም የምወደው።"

በደልሂ ነዋሪ የሆኑት ዶ/ር ስዋቲ ሚሽራ ደግሞ የተቀቀለ ድንች ኮረሪማ፣ ሽንኩርት እና ጥራጥሬ ተደርጎበት የሚዘጋጅ ሳሞሳ ትወዳለች።

እርሷ እንደምትለው ምን ዓይነት ድግስ እና ሰርግ ያለ እዚህ ሙሉ አይደለም።

ሚሽራ ትኩስ የሚሰሩ ስናኮች አሁን ላይ ተዘጋጅተው ወደሚቀመጡ ምግቦች እየተቀየሩ መሆናቸውን የታዘበች ሲሆን ሕፃናትም እነዚህን ምግቦች እንዳይመገቡ ማድረግ አዳጋች ነው ትላለች።

"ብዙ ጊዜ በቂጣ የተጠቀለለ ዓሳ ለመግዛት በአካባቢያችን ወደሚገኝ ሱቅ እሄዳለሁ" የምትለው ስቴላ ኦሴግቡ በበኩሏ "ይህ ምግብ ከካሳቫ ዱቄት፣ ከዓሳ፣ ከጨው እና ከስኳር የሚዘጋጅ ምግብ ነው።"

ማዲጋ በደቡብ ምዕራብ ናይጀሪያ የተለመደ ዳቦ ነው። በውፍረቱ እና በጣዕሙ ይታወቃል ትላለች ኦሴግቡ።

የባንኮኳ ፓፓትቻያ ኒፓናን ደግሞ በየቀኑ ስናክ እንደምትመገብ ትናገራለች።

"ብዙ ጊዜ የምንመገባቸው ስናኮች ኩርሽም ኩርሽም የሚሉ ናቸው፣ አንዳንዴ ደግሞ ቸኮሌት፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ናቾስ የተባለውን እመገባለሁ" ትላለች።

የሥራ እረፍት ሲኖራት ስናኮችን ገዝታ ታስቀምጣለች። ከዚያም በሥራ ቀናት አፍታ በምታገኝበት ሰዓት ትመገባቸዋለች።

ፈጣን እድገት

የገበያ ጥናት ኩባንያው ሲርካና እንዳው ከሆነ ግማሽ የሚሆኑት በአሜሪካ የሚኖሩ አዋቂዎች በየቀኑ ከሦስት ጊዜ ወይም ከዚያ በላይ ስናኮችን ይመገባሉ።

በሌሎች በርካታ አገራትም ስናኮችን መመገብ የተለመደ ሲሆን፣ ስናክ ምግቦችን መመገብ ከጀመርን ፍላጎታችንን መግታት አዳጋች ነው።

"የስናክ ገበያ ውስጥ መሥራት ስጀምር ከሌሎች ገበያዎች አንጻር በጣም ትንሽ ነበር። ከ300 ቢሊዮን ዶላር ያነሰ ነበር" የሚሉት የግዙፉ ዩኒሊቨር ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ፖልማን፤ "አሁን ላይ በስናክ ምድብ የሚሸጡ ፍጆታዎች አጠቃላይ የገበያ ዋጋ ከ1.2 እስከ 1.5 ትሪሊዮን ዶላር ዋጋ አላቸው" ይላሉ።

ይህ ግዙፍ ኢንደስትሪ በ2035 እጥፍ እንደሚሆንም ይጠብቃሉ።