ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኒጀር መፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን የተባረሩት ፕሬዝዳንት በአገር ክህደት ሊከሰሱ ነው
በዴሞክራሲያዊ መንገድ ተመርጠው ሥልጣን ላይ የነበሩትን ሞሐመድ ባዙምን በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን ያስወገዳቸው የኒጀር ወታደራዊ ጁንታ በከባድ የአገር ክህደት ሊከስ ነው።
የመንግሥት ግልበጣ ያደረገው የኒጀር ወታደራዊ ቡድን ፕሬዝዳንት ባዙምን “በአገር ክህደት እና የአገሪቱን ደኅንነት አደጋ ላይ መጣል” በሚል ከሷቸዋል።
የጦር ሠራዊቱ ቃል አቀባይ ኮሎኔል አማዱ አብደራማኔ፣ ከሥልጣን የተገለበጡት ፕሬዝዳንት ባዙም ፈጽመውታል ለተባሉ ጥፋቶች ማስረጃዎች እየተሰበሰበባቸው ነው ሲሉ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው መግለጫ አንብበዋል።
ፕሬዝዳንቱ “በአገር ክህደት” እና “የአገር ደኅንነትን አደጋ ላይ መጣል” የሚለው ክስ የተመሠረተባቸው ከአገር ውስጥ እና ከውጭ ኃይሎች ጋር በማበር ነው ብለዋል ቃል አቀባዩ።
ፕሬዝዳንት ባዙም ሐምሌ 19/2015 ዓ.ም. መፈንቅለ መንግሥት ከተፈጸመባቸው በኋላ በኒጀር መዲና ኒያሚ በሚገኘው ቤተ መንግሥት ምድር ቤት ውስጥ ከቤተሰባቸው ጋር በቁም እስር ይገኛሉ።
የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማኅበር በሆነው ኤኮዋስ አማካይነት በኒጀር የከሰተውን ቀውስ ለመፍታት ሲደረግ የነበረው ጥረት አስካሁን ስኬታማ አልሆነም።
በፕሬዝዳንቱ ላይ ክስ የመመስረቱ መግለጫ ይፋ የተደረገው፣ ወታደራዊው ቡድን በአገሪቱ ውስጥ የተከሰተውን ቀውስ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት ፍላጎት እናዳለው ካሳወቀ ከሰዓታት በኋላ መሆኑ ግራ መጋባትን ፈጥሯል።
ትናንት እሁድ የኃይማኖት መሪዎች ልዑካን መሪ፣ የወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ጄኔራል አብዱራህማኔ ቺያኒ በኤኮዋስ አማካይነት ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ እንዲገኝ ፍላጎት እንዳላቸው እንደተናገሩ ገልጸው ነበር።
የናይጄሪያ አንድ የእስልምና እምነት እንቅስቃሴ መሪ የሆኑት ሼክ አብዱላሂ ባላ ሉ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፣ ጄኔራል ቺያኒ “ችግሩን በዲፕሎማሲ እና በሰላም ለመፍታት በራቸው ክፍት መሆኑን ተናግረዋል።”
በተጨማሪም በጉዳዩ ዙሪያ ከወታደራዊው ቡድን ጋር ለመነጋገር ቀደም ሲል ወደ ኒጀር የመጣውን የኤኮዋስ ቡድንን ባለማናገራቸው ጄኔራሉ ይቅርታ መጠየቃቸውን ገልጸዋል።
በዩራኒየም ማዕድን የበለጸገችው ኒጀር ላይ ምዕራባውያን ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። ሩሲያም ወታደራዊ ቡድኑን በመደገፍ ከጎኑ ቆማለች።
የምዕራብ አፍሪካ አገራትም ችግሩን በወታደራዊ ኃይል ለመፍታት ፍላጎት እንዳላቸው ቢገልጹም፣ የሚያስከትለውን አደጋ በመስጋት ሌሎች አማራጮችን እየፈለጉ ነው።
አሜሪካ እና ፈረንሳይ በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን የተወገዱት የፕሬዝዳንት ባዙም ደኅንነት እንደሚያሳስባቸው በተደጋጋሚ እየገለጹ ነው።