እስራኤል ስለ ጉዳያቸው አላውቅም ያለቻቸውን የጋዛ ሆስፒታል ኃላፊ እንዳሰረቻቸው አመነች

እስራኤል ስለ ጉዳያቸው አላውቅም ብላ የነበረውን የጋዛ ሆስፒታል ዳይሬክተር ዶክተር ሁሳም አቡ ሳፊያን እንዳሰረቻቸው አመነች።

እስራኤል ለአንድ ሃገር ውስጥ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ስለ ዳይሬክተሩ ጉዳይ አላውቅም የሚል ምላሽ በመስጠቷ የደህንነታቸው ሁኔታ ስጋት ውስጥ ገብቶ ነበር።

የሆስፒታል ዳይሬክተሩ "በአሁኑ ወቅት በእስራኤል የጸጥታ ኃይሎች እየተመረመሩ ነው" ሲል የእስራኤል መከላከያ ኃይል መግለጫ አውጥቷል።

ስለ ዳይሬክተሩ ጉዳይ የማውቀው ነገር የለም በሚል ምላሽ ለምን እንደተሰጠ እንዲሁም ለተፈጠረው ውዥንብር መግለጫው ማብራሪያ ባይሰጥም የሆስፒታሉን ዳይሬክተር "በአሸባሪነት" እንዲሁም በሐማስ አባልነት ተጠርጥረዋል ተብሏል።

ዶክተር አቡ ሳፊያ በቁጥጥር ስር የዋሉት ባለፈው አርብ የእስራኤል ጦር በሰሜናዊ ጋዛ የሚገኘው ካማል አድዋን ሆስፒታል "የሃማስ መሸሸገጊያ ነው" በሚል ታማሚዎችን እና የህክምና ባለሙያዎችን እንዲወጡ ማድረጉን ተከትሎ ነው።

ጦሩ በሆስፒታሉ ያሉ ህመምተኞች እንዲሁም የሆስፒታሉ ሰራተኞች በ15 ደቂቃ ውስጥ ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ማስተላለፉን የህክምና ባለሙያዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሐሙስ እለት የእስራኤል መከላከያ ኃይል 'ፊዚሻንስ ሂውማን ራይትስ እስራኤል' (ፒኤችአርአይ) ለተሰኘው ድርጅት ዶክተሩ "በቁጥጥር ስር ስለመዋላቸውም ሆነ ስለመታሰራቸው ምንም አይነት ፍንጭ የለንም" ሲል ተናግሮ ነበር።

ለጤና ባለሙያዎች መብት የሚሟገተው ፒኤችአርአይ አይ ሐሙስ ዕለት ለእስራኤል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዶክተር አቡ ሳፊያ ያሉበት ቦታ እንዲገለጽ አቤቱታ አስገብቶ ነበር። ፍርድ ቤቱ በበኩሉ ዳይሬክተሩ ያሉበትን እንዲያሳውቅ ለመከላከያ አንድ ሳምንት ሰጥቷል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የአምነስቲ ኃላፊ አግነስ ካላማድር የእስራኤል ባለስልጣናት ዳይሬክተሩ "ያሉበትን ቦታ በአስቸኳይ ማሳወቅ አለባቸው" ብለዋል።

እስራኤል በመቶዎች የሚቆጠሩ የፍልስጤም የጤና ባለሙያዎች ከጋዛ ያለምንም ክስ በመውሰድ አስራ ለስቃይ እና ለሌሎች እንግልቶች እየዳረገች እንደሆነ እንዲሁም አብዛኛዎቹ የታሰሩበት ስፍራ እንደማይታወቅ ኃላፊዋ ገልጸዋል።

እስራኤል በቁጥጥር ስር ያዋለቻቸውን ፍልስጤማውያን አላግባብ አልይዝም ስትል አስተባብላለች።

የዶክተር አቡ ሳፊያ ቤተሰቦች ቀደም ሲል ለቢቢሲ አረብኛ እንደተናገሩት ዳይሬክተሩ በደቡባዊ እስራኤል በሚገኘው ሴዴቴማን የጦር ካምፕ ታስረው እንደሚኙ ተናግረው ነበር። የእስራኤል ጦር በርካታ ፍልስጤማውያንን ከጋዛ ለምርመራ በሚል ወደዚህ ካምፕ ወስዷል።

በእስር ላይ የሚገኙት እነዚህ ፍልስጤማውያን እጅግ አስከፊ በሚባል ሁኔታ እንደሚገኙ ተነግሮ ነበር። እስራኤል በበኩሏ እዚያ ያሉ እስረኞች በሙሉ "በጥንቃቄና በአግባቡ" እየተጠበቁ ነው ትላለች።

እስራኤል በጋዛ ጦርነት በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመች ነው ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል በቅርቡ መግለጹ ይታወሳል። እስራኤል ይህንን አልተቀበለችውም።

መቀመጫውን ዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ የእስራኤል ባለስልጣናት ፍልስጤማውያንን ከሰብዓዊነት ባወረደ መልኩ የሚሰጧቸው ትርክቶች እንዲሁም እስራኤል ሆን ብላ ተቋማት ላይ ካደረሰቻቸው ውድመቶች እና እልቂቶች በመነሳት የዘር ጭፍጨፋ ድምዳሜ ላይ መድረሱን ገልጾ ነበር።

በተጨማሪም በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማውያንን ሆን ብላ በገፍ በማፈናቀል የጦር ወንጀሎች እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል መፈጸሟን ሂውማን ራይትሰ ዋች አስታውቆ ነበር።

እስራኤል በበኩሏ ሪፖርቱን አጣጥላ "ሙሉ በሙሉ ስህተት እና ከእውነታ የራቀ ነው" ማለቷ ይታወሳል።

እስራኤል በጋዛ ውስጥ እየፈጸመችው ባለው ጥቃት ከ45 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውንም በሐማስ አስተዳደር ሥር ካለው የጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ አመልክቷል።

ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በደቡባዊ እስራኤል ውስጥ በፈጸመው ጥቃት 1 ሺህ 200 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 253 ሰዎች ታግተው መወሰዳቸው ይታወሳል።