በእስራኤል ጥቃት አንድ የፍልስጤም ቴሌቪዥን ጣቢያ አምስት ጋዜጠኞች ተገደሉ

እስራኤል በመካከለኛው የጋዛ ሰርጥ በፈጸመችው ጥቃት አምስት ጋዜጠኞቹ እንደተገደሉበት ኩዊድስ ቱደይ የተሰኘው የፍልስጤም ቴሌቪዥን ጣቢያ አስታወቀ።

ጥቃቱ ሲፈጸምባቸው በቴሌቪዥን ጣቢያው መኪና ተሳፍረው የአንደኛው ጋዜጠኛ ሚስት ወደምትወልድበት አልአውዳ ሆስፒታል ለመግባት መኪና ማቆሚያው ስፍራ ላይ በነበሩበት ወቅት ነው ተብሏል።

ጣቢያው በኋላው በር ላይ ፕሬስ የሚል ምልክት የተለጠፈበትን የሚያሳይ ተሽካርካሪዬ ነው ያለውን በእሳት ሲነድ የሚያሳይ ቪዲዮ አውጥቷል።

የእስራኤል አየር ኃይል በበኩሉ ጥቃቱ "በስለላ መመሪያ በታገዘ" የፍልስጤም እስላማዊ ጂሃድ (ፒአይጄ) ታጣቂዎች ያሉበት መኪና ላይ "ባነጣጠረ መልኩ" መፈጸሙን አስታውቋል።

በሰላማዎ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመቀነስ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን አክሏል።

ቢቢሲ ሁለቱም አካላት ያሏቸውን ጉዳዮች በገለልተኛነት ማረጋገገጥ አልቻለም።

ኩድስ ቱደይ መስከረም መጨረሻ ላይ በሐማስ መሪነት በእስራኤል በተፈጸመው ጥቃት ተሳታፊ ከነበረው ፒአይጄ ጋር ግንኙነት አለው።

በተያያዘ ዜና እስራኤል ረቡዕ ዕለት በፈጸመችው ጥቃት አምስት ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።

የፍልስጤም የዜና ወኪል የሆነው ዋፋ እና በሐማስ የሚተዳደረው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር በተጨማሪ 20 ሰዎች አል ዘይቱን በተሰኘችው ከተማ መቁሰላቸውን አስታውቀዋል።

የእስራኤል ጦር ስለ ጥቃቱ የሰጠው መግለጫ የለም።

ሐማስ እና እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ በተደረገው የቅርብ ጊዜ ሙከራዎች መዘግየት እየተወነጃጀሉ ይገኛሉ።

ሐማስ የእስራኤል መንግሥት ስምምነቱን የሚያዘገዩ "አዳዲስ ቅድመ ሁኔታዎችን" አስቀምጧል ሲል ከሷል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው ሐማስ ቀደም ሲል መግባባት ሊደረስበት የተቃረበውን የተኩስ አቁም ስምምነት እየሻረ ነው ብለዋል።

እስራኤል በጋዛ ውስጥ እየፈጸመችው ባለው ጥቃት ከ45 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውንም በሐማስ አስተዳደር ሥር ካለው የጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ አመልክቷል።

ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በደቡባዊ እስራኤል ውስጥ በፈጸመው ጥቃት 1 ሺህ 200 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 253 ሰዎች ታግተው መወሰዳቸው ይታወሳል።

እስራኤል በጋዛ ጦርነት በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመች ነው ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል በቅርቡ መግለጹ ይታወሳል። እስራኤል ይህንን አልተቀበለችውም።

መቀመጫውን ዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ የእስራኤል ባለስልጣናት ፍልስጤማውያንን ከሰብዓዊነት ባወረደ መልኩ የሚሰጧቸው ትርክቶች እንዲሁም እስራኤል ሆን ብላ ተቋማት ላይ ካደረሰቻቸው ውድመቶች እና እልቂቶች በመነሳት የዘር ጭፍጨፋ ድምዳሜ ላይ መድረሱን ገልጾ ነበር።

በተጨማሪም በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማውያንን ሆን ብላ በገፍ በማፈናቀል የጦር ወንጀሎች እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል መፈጸሟን ሂውማን ራይትሰ ዋች አስታውቆ ነበር።

እስራኤል በበኩሏ ሪፖርቱን አጣጥላ "ሙሉ በሙሉ ስህተት እና ከእውነታ የራቀ ነው" ማለቷ ይታወሳል።