ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የ96 ዓመቷ ጸሐፊ እንዴት የ9 ሚሊዮን ዶላር ባለቤት ለመሆን በቁ?
እአአ መስከረም 11/2001 አንዲት ሴት ኒው ዮርክ በሚገኘው ወርልድ ትሬድ ሴንተር ወዳለው ቢሮዋ እያቀናች ነበር።
የደረሰውን የሽብር ጥቃት ተከትሎ አካባቢው እንደቀደሙት ቀናት አልነበረም። ሴትየዋም ወደቤቷ እንድትመለስ ተነገራት።
ያቺ ሴት ሲልቪያ ብሉም ትባላለች። በወቅቱ 84 ዓመቷ ነበር።
ሲልቪያ ከፍተኛ ገንዘብ ማግኘት ብትችልም ቅንጡ ሕይወት አልነበራትም። በወቅቱ በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ አግኝታለች።
ለ67 ዓመታት በአንድ የሕግ አማካሪ ተቋም ውስጥ በጸሐፊነት ሠርታለች። በድርጅቱ የሚሠሩ ጠበቆች የሚያደርጉትን ኢንቨስትመንት እሷም በመከተል ነው ገንዘቡን ያገኘችው።
እስከ 2018 ድረስ ታሪኳ አይታወቅም ነበር። ስለ ሲልቪያ የታወቀው ከሞተች ከሁለት ዓመታት በኋላ ነው።
ሃብቷን ያወረሰችው በኒው ዮርክ ወጣቶችን ለሚደግፍ ድርጅት ነው። የለገሰችው ገንዘብ 6.24 ሚሊዮን ዶላር ይደርሳል።
በድርጅቱ የ125 ዓመታት ታሪክ በግለሰብ ደረጃ የተለገሰው ትልቁ ገንዘብ ነው። ለሌሎች ተራድኦ ድርጅቶች 2 ሚሊዮን ዶላር ለግሳለች።
'ብልህና መሰሪ'
ሲልቪያ የተወለደችው እአአ በ1919 በብሩክሊን ነበር። ቤተሰቦቿ ከምሥራቅ አውሮፓ ወደ አሜሪካ የተጓዙ ስደተኞች ናቸው።
ያደገችው በታላቁ የምጣኔ ሃብት ውድቀት ዘመን ነው። እንደአብዛኛው ሰው በፈተና ውስጥ ነበር ያለፈችው።
ኒው ዮርክ ታይምስ ያወጣው ዘገባ እንደሚጠቁመው ሲልቪያ በተለያዩ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ተምራለች። ቀን እየሠራች ማታ ላይ ትማርም ነበር።
በ1947 በዋል ስትሪት በሚገኘው የሕግ አማካሪ ተቋም የሆነው 'ክሊሪ ጎታሊብ ስቲን ኤንድ ሀሚልተን' ተቀጠረች። በዚህ ዕውቅ የሕግ አማካሪ ተቋም ከተቀጠሩ የመጀመሪያዎቹ ሠራተኞች አንዷ ናት።
የምታገኘውን ደመወዝ ኢንቨስት ለማድረግ ወሰነች። ውሳኔዋ ሕይወቷን ሙሉ በሙሉ ለውጦታል።
የእህቷ ልጅ ጄን ሎክሺን "ብልህና መሰሪ የኒው ዮርክ ሰው ነበረች" ስትል ነው የምትገልጻት።
"እሷ ሥራ በጀመረችበት በ1940ዎቹ እና 1950ዎቹ ጸሐፊዎች የአለቆቻቸውን ኃላፊነት የመወጣት ግዴታ ነበረባቸው። ክፍያ መፈጸም፣ የስቶክ ድርሻ መግዛትና ሰነዶችን መከታተል የሷ ድርሻ ነበር። አለቃዋ 'ኤቲኤንድቲ ደውለሽ አንድ ሺህ ድርሻ ግዢልኝ' ሲላት ለራሷ ከኤቲኤንድቲ መቶ ድርሻ ትገዛ ነበር።"
ሲልቪያ ሕግ ባለመማሯ ትቆጭ ነበር። እሳት አደጋ ተከላካይ የሆነው ሬይመንድማርጎሊስ ጋር ትዳር መሥርታለች።
ባሏ ጡረታ ከወጣ በኋላ መምህር ሆኗል።
ባለቤቷም ሆነ በቅርብ የሚያውቋት ሰዎች ከፍተኛ ገንዘብ እያገኘች እንደሆነ አላወቁም።
ሲልቪያ ልጆች አልነበሯትም። ከባለቤቷ ጋር ብሩክሊን በሚገኝ አፓርትመንት ይኖሩ ነበር።
ባለቤቷ በ2002 ሲሞት፤ በ96 ዓመቷ ጡረታ ወጥታለች። የሕይወቷን የመጨረሻ ዓመታት የአረጋውያን መንከባከቢያ ማዕከል ውስጥ ነው ያሳለፈችው።
2016 ላይ በተደረገላት ዝክር ላይ ንግግር ያደረገ ሰው "የሥራ ባልደረቦቿ ድንቅ ጠበቃ መሆን ትችል እንደነበር ይናገራሉ። በጣም ብልህ፣ አሰላሳይ፣ ታጋሽና ታማኝ ናት" ሲል ገልጿታል።
ቀልደኛ፣ የሚጋባ ሳቅ ያላትና ፈገግታ የማይለያት እንደነበረች የሚያውቋት ይመሰክራሉ።
በሙያዋ ብቁ፣ ታማኝ፣ ሐቀኛ፣ ለጋስና ታታሪ ሠራተኛ እንደነበረች የሚናገሩም አሉ።
ቀጥተኛ፣ የማታስመስልና የራሷን መንገድ የምትከተል እንደነበረች እንዲሁም ብስል አእምሮ ያላትና ቃላቶችን በአግባቡ የምትጠቀም እንደነበረች ይነገርላታል።
ምሥጢራዊቷ ሚሊየነር
በ2016 ከሞተች በኋላ የእህቷ ልጅ ኑዛዜዋን እንድታስፈጽም ተወሰነ። አክስቷ በምሥጢር ሚሊየነር እንደነበረችም ደረሰችበት።
የአክስቷን ባለሃብትነት ያወቀችበትን ቀን አትረሳውም።
"ሲልቪያ ኑዛዜዋን እንዳስፈጽም ወሰነች። ያላትን ገንዘብ ስመለከት የፈጣሪ ያለህ! አልኩኝ። ችግረኛ ልጆች ነጻ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ገንዘቧን ለተራድኦ ድርጅት ለግሳለች። ይሄንን እንዳስፈጽምላት አምና ኃላፊነቱን ስለሰጠችኝ ደስተኛ ነኝ። ስትሞት ምን ያህል ገንዘብ እንዳላት አላውቅም ነበር።"
የእህቷ ልጅ "ሦስት ሚሊዮን ዶላር በአንድ በኩል አንድ ሚሊዮን ዶላር በሌላ በኩል እያደረግኩ ገንዘቡን ከፋፈልኩ። ገንዘቡን ደልድዬ ስጨርስ ወደ 9 ሚሊዮን ደርሶ ነበር። ማመን አልቻልኩም" ስትልም ታክላለች።
ሲልቪያ በተለይም ከገንዘብ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ምሥጢረኛ እንደነበረች የእህቷ ልጅ ጄን ታስታውሳለች።
ከባለቤቷ ጋር ባለአንድ መኝታ ክፍል ቤት ውስጥ ነበር የሚኖሩት። አዘውትረው ወደ ላስ ቬጋስ ይጓዙ ነበር።
ሲልቪያ ኤልቪስ ፕሪስሊን በጣም ትወደው ነበር። አንድ ጊዜ ላስ ቬጋስ ሲዘፍን ተመልክታዋለች።
ጥንዶቹ አውሮፓ ሄደው ኦፔራ ያደምጡም ነበር። ሆኖም ግን ሕይወታቸው "እምብዛም ቅንጡ" እንደማይባል ጄን ትናገራለች።
ፖል ሀይማስ ከሲልቪያ ጋር ለዓመታት ሠርቷል። ሚሊየነር እንደነበረች ሲሰማ ደንግጧል።
"ስለገንዘብ ስታወራ ሰምቼ አላውቅም። ሕይወቷም ቅንጡ አልነበረም። ወደራሷ ትኩረት መሳብ አትወድም ነበር" ሲል ያስታውሳል።
ሲልቪያ ያደገችው በታላቁ የምጣኔ ሃብት ውድቀት ዘመን እንደመሆኑ ተገቢውን ትምህርት አለማግኘት የሚያደርሰውን ጫና ትገነዘባለች።
ወጣቶች እንዲማሩ ገንዘብ የለገሰችውም ለዚያ ነው።
"አክስቴ ሲልቪያ ዲግሪ ያገኘችው የማታ ተምራ ነው። ለትምህርት ትልቅ ዋጋ ትሰጣለች። ትምህርት ማግኘት ለማይችሉ ሰዎች ነው ገንዘቧን የለገሰችው" ስትል ጄን ትገልጻታለች።
ነጻ የትምህርት ዕድል
ጄን የአክስቷን ውርስ ለተራድኦ ተቋማት አስረክባለች።
የተራድኦ ድርጅቱ ዋና ኃላፊ ዴቪድ ገርዛ "በጣም ነው የተደነቅነው። ስሜታችንን ለመግለጽ ቃላት ያጥረናል" ብሏል።
በሲልቪያ ብሉም ስም ብሉም-ማርጎሊስ የተባለ የነጻ ትምህርት አገልግሎት ተከፍቷል። ከዘጠነኛ ክፍል እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ ተማሪዎችን ያግዛል።
ነጻ የማማከርና የብሔራዊ ፈተና ሥልጠናም ይሰጣል። ተማሪዎችን የማስጠናትና ዲግሪያቸውን እስከሚያገኙ ድረስ ድጋፍ የማድረግ ኃላፊነትንም ይወጣሉ።
የተቋሙ ድረ ገጽ "በተደረገው የገንዘብ ድጋፍ መሠረት ለተማሪዎች ነጻ የትምህርት ዕድል ይመቻቻል" ይላል።
የሲልቪያ እህት ልጅ ከካናዳው ሲቢሲ ጋር በ2018 ቃለ መጠይቅ ስታደርግ "አክስትሽ ይሄን ሁሉ ትኩረት ማግኘቷን ብታውቅ ምን የሚሰማት ይመስልሻል?" ተብላ ተጠይቃለች።
"በጣም ትጠላው ነበር። ትኩረቱ እንዲሆን የምትፈልገው ነጻ የትምህርት ዕድሉ ላይ ነው" ስትል መልሳለች።