ብዙም ያልተነገረለት ሴቶች በሥራ ቦታቸው ተቀባይነትን ለማግኘት የሚገጥማቸው ጫና

የ24 ዓመቷ ፌዝ በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ በሚገኘው ቢሮዋ በስብሰባ ላይ እያለች ተጨነቀች።

ስብሰባው ሲጀመር ሁሉ ነገር መልካም ነበር። ፌዝ አለቆቿ በሚቀልዷቸው ያልተገቡ ቀልዶች ጥርሷን ብልጭ እያደረገች የሳቀች ለመምሰል ጥረት ታደርጋለች።

ከዚያ በኋላ ግን የነበረው እንዳልነበር መሆን ጀመረ። ሁኔታዎች ተለዋወጡ።

አንድ በተቋሙ ረዘም ላለ ዓመታት የቆየ ባልደረባዋ ፌዝ በተግባር ይሠራል ብላ የማታምንበትን አስተያየት ሰጠ። ፌዚ ለዚህ አስተያየት ምላሽ ከመስጠቷ በፊት ባልደረባዋ ስሟን ጠራው።

"እና ፌዝ በዚህ ሀሳብ ትስማማለች!" ሲል ባልደረባዋ ሌላው በስብሰባው ላይ ተሳታፊ የነበረ ግለሰብ ወደ እርሷ ዞሮ፣ "ትስማሚያለሽ አይደል?" ሲል ማረጋገጫዋን ጠየቀ።

ፌዝ አልተስማማችም ነገር ግን ጫና ውስጥ ወደቀች።

"እኔ እንደ አስቸጋሪ ወይም ስሜቴ እንደሚቀያየር ሰው ሆኜ መታየት አልፈለኩም" ትላለች ፌዝ፣ "ፈገግ እንድል፣ እንድስማማ፣ እንዳልረብሽ በቃላት ያልተገለፀ ግፊት ሲደረግብኝ ተሰማኝ።"

በዚያን ጊዜ በወቅቱ በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንደነበረች ለማጤን ቆም ብላ ማሰብ ነበረባት።

የመጀመሪያዋ በሆነው በዚያ ትልቅ ኩባንያ ውስጥ መሥራት ከጀመረች ገና ሁለት ዓመት ነው የሆናት፣ ከቤተሰቦቿ ዩኒቨርስቲ ለመግባት የመጀመሪያዋ ሴት የሆነችው እና በርካታ ግቦቿን ለማሳካት የምትፈልገው ፌዝ አጣብቂኝ ውስጥ ወደቀች።

"ገና ከመጀመሪያው ከባልደረባዎቼ ጋር አለመግባባት ከጀመርኩ እንዴት መቀጠል እችላለሁ?" ስትል ትጠይቃለች።

ፌዝ በ2025 በወጣው ሪፖርት በሥራ ቦታ ላይ ያሉ ኬንያውያን ሴቶች ፈታኝ ሁኔታን ይጋፈጣሉ ያለውን ፊት ለፊት እንዳገኘችው ታውቃለች።

በዚህ ጥናት መሠረት ይህ ሁኔታ በተቋማት የዕድገት መሰላል ውስጥ ትልቅ እንቅፋት ሆኖ የተቀመጠ ሲሆን፣ ይህም ከመጀመሪያው ቅጥር ቀስ በቀስ በሚገኝ ዕድገት ወደ አስተዳደራዊ ሚናዎች ከፍ ሲባል የሴቶች ውክልና እየቀነሰ መምጣቱን ያሳያል።

በዚህ ዓመት በማኪንሴይ ማኔጅመንት አማካሪዎች የታተመው ዓመታዊ ሪፖርት ከሰሜን አሜሪካ አልፎ ኬንያን፣ ናይጄሪያን እና ሕንድን በማካተት በከፍተኛ የአመራር ቦታዎች ላይ ሴቶች እጅግ በጣም ዝቅተኛ ውክልና እንዳላቸው አረጋግጧል።

በኬንያ እንደ ጤና አጠባበቅ እና የፋይናንስ አገልግሎት ባሉ የሥራ ዘርፎች በቅጥር ወቅት ሴቶች 50 በመቶ ቢሸፍኑም፣ ከፍ ወዳለ የሥልጣን እርከን ሲመጣ ግን ወደ 26 በመቶ ዝቅ ብሏል። ይህ በናይጄሪያ እና በሕንድም ተመሳሳይ ነው።

ፌዝ በስብሰባው ላይ ባልደረባዋን አልሞገተችውም። ፈገግ ብላ ምንም ሳትናገር አሳለፈችው።

ፌዝ የገባችበት ቅርቃር አሁን በዘርፉ ባለሙያዎች ዘንድ "የመወደድ ጥረት" [ተቀባይነት የማግኘት ጥረት] የሚል መጠሪያ አግኝቷል።

"የመወደድ ጥረት" ምንድን ነው?

"[ይህ] ለሚያስገርም ተስፋ አስቆራጭ እውነታ በጣም የሚያስቅ ስያሜ ነው" ትላለች ቃሉን በፈጠረው ጉድ ሻውት ኮሙኒኬሽን ውስጥ የምትሠራው ኤሚ ኪን።

"ይህ የሚያመለክተው ሴቶች በሥራ ቦታ ለመወደድ ሲሉ በየዕለቱ የሚያደርጉትን የማያቋርጥ የይሆናል መላምቶችን፣ ከመጠን በላይ ማሰብ፣ ፍርሃትን፣ ያልሆኑትን መሆንን ያጠቃልላል።"

መቀመጫውን ዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው ይህ የኪን ተቋም "ሼፕሺፍተርስ፡ ዋት ዊ ዱ ቱ ቢ ላይክድ" በሚል ርዕስ ያሳተመው ጥናት 56 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች በሥራ ቦታ ለመወደድ ጫና እንደሚሰማቸው አስቀምጧል። ይህ ከወንዶች ጋር ሲነጻጸር 36 በመቶው ብቻ ነው።

በመላው ዩናይትድ ኪንግደም በአንድ ሺህ ሴቶች ላይ የተደረገ ጥናትን መሠረት በማድረግ ሪፖርቱ በሥራ ቦታ ለመወደድ የሚደረግ ጥረት ምን ያህል ሥር የሰደደ እና በኢፍትሐዊነት የተከፋፈለ መሆኑን አጉልቶ አሳይቷል።

ሴቶች በሚሰነዝሩት ሃሳብ ላይ መተማመን እንኳ ኖሯቸው ምን ያህል ንግግራቸውን እንደሚያለሰልሱት፣ እንደሚያለዝቡት ጥናቱ በዝርዝር አስፍሯል። እነዚህ ሴቶች ከሚጠቀሟቸው የተለመዱ ሐረጎች መካከል "ይህ ምን ፋይዳ አለው?" ወይም "አንድ ጊዜ ይቅርታ..." የሚሉ ይገኙበታል።

ኪን ይህ ዓይነቱ የማያቋርጥ ራስን የማረም ተግባር፣ እንደ መከላከያ ጋሻ ወይም ከመጠን በላይ ተጋፊ ሆኖ ላለመታየት መሞከር፣ ካመነችበት ነገር ፍንክች የማትል ተደርጋ ላለመቆጠር ሊያገለግል ይችላል ትላለች።

ዩናይትድ ኪንግደምን በመጥቀስ "የመደብ መልክም አለው" ብላለች። "በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ ራሳቸውን ለማስተካከል ብዙም ያልተለማመዱ የሠራተኛው መደብ ሴቶች ግትር ናቸው ተብለው ይወቀሳሉ፤ እንዲሁም በኮርፖሬቱ ዓለም ፍዳቸውን ይበላሉ።"

በግል መኖሪያቸው ለራሳቸው መብት መሟገትን ያልተለማመዱ በርካታ ሴቶች ጉዳቱ ከመመሳሰል ወይም ከመወደድ ያልፋል።

ኪን አክላም "ተወዳጅ መሆን ያን ያህል ቀላል አይደለም፤ ደኅንነት የመሰማት፣ የመደመጥ እና በቁም ነገር የመታየት ነው።"

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ኪን የመወደድ ጥረት በማድረግ ጫና ውስጥ እንዳሉ ለሚሰማቸው ሴቶች በለንደን ወርክሾፕ አዘጋጀች።

ከ300 በላይ ሴቶች ልምዳቸውን ለማካፈል ተገኝተው ነበር።

ዓለም አቀፋዊ ጉዳይ

የዩናይትድ ኪንግደም ጥናት ከዚህ የተለየ አይደለም። የማኅበራዊ ኑሮ ጠበብት ሴቶች በሙያቸው ለማደግ ተወዳጅ መሆን አንዳለባቸው የሚሰማቸው ጫና ዓለም አቀፋዊ ነው ይላሉ።

መቀመጫውን በዩናይትድ ስቴትስ ያደረገው ቴክስቲዮ የተሰኘ የቅጥር ድርጅት በ2024 ያደረገው ጥናት ይህንን ይደግፋል።

በ253 ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ ከ25 ሺህ ግለሰቦች ያገኘውን መረጃ በመተንተን፣ ሴቶች በሰብዕናቸው ላይ የተመሠረተ ግብረ መልስ የማግኘት ዕድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ እና 56 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች በአፈጻጸም ግምገማዎች ላይ "የማይወደዱ" የሚል ስያሜ እንደተሰጣቸው፣ ይህንንም አስተያየት 16 በመቶ ወንዶች ብቻ እንዳገኙ አስፍሯል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ወንዶች ከሌሎች ፆታዎች በአራት እጥፍ በበለጠ "የሚወደድ" የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል።

በኬንያ መልቲሚዲያ ዩኒቨርሲቲ የሶሺዮሎጂ ባለሙያ እና የማኅበራዊ ሳይንስ ፋኩልቲ ከፍተኛ መምህርት የሆኑት ዶክተር ግላዲስ ኒያቺዮ "ሴቶች በማኅበራዊ እና ባህላዊ ምክንያቶች ለመወደድ ጥረት ያደርጋሉ" ይላሉ።

"ሴቶች በአጠቃላይ ተንከባካቢ እንዲሆኑ፣ እንዲያገለግሉ እና የሌሎችን ፍላጎት ከራሳቸው በፊት እንዲያስቀድሙ ተደርገው ይሳላሉ። እናም ይህ ሁልጊዜ ወደ ሥራ ቦታ ይመጣል" ብለዋል ዶክተር ኒያቺዮ። "በኪስዋሂሊ የቢሯችን እናት የሚል ቃልም አለ።"

የሥራ ቦታን ለማስቀጠል የቢሮው እናቶች ተጨማሪ ጉልበት ያፈስሳሉ።

ሻይ ያፈላሉ፣ ጣፋጭ መግዛት እና በአጠቃላይ የሁሉ አገልጋይ መሆንን ይጨምራል።

አንዲት ሴት ማድረግ የምትፈልግ ከሆነ ይህ ምን ችግር እንዳለበት እጠይቃለሁ።

ዶ/ር ኒያቺዮ "ምንም ችግር የለውም። ነገር ግን ለእሱ ክፍያ አታገኝበትም። አሁንም ሥራሽን እና ምናልባትም ተጨማሪ ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅብሻል።"

መፍትሄው ምንድን ነው?

ዶ/ር ኒያቺዮ ለመወደድ የሚደረግን ጎንበስ ቀና ለመቅረፍ የሥርዓት ለውጥ ከሥር መሠረቱ መምጣት እንዳለበት ያምናሉ።

ይህም ሴቶች በተለዋዋጭ ሰዓት ውስጥ እንዲሠሩ የሚፈቅዱ ፖሊሲዎችን መተግበር እና ለእነሱ ጥብቅና የሚቆሙ አማካሪዎች እንዲኖሩ ማድረግንም ይጨምራል።

ዶ/ር ኒያቺዮ ራሳቸው በኬንያ ሥራ የጀመሩ በርካታ ወጣት ሴቶችን አማክረዋል።

ዶ/ር ኒያቺዮ "ወጣት ሴቶችን ማማከር በጣም በአትክሮት የማየው ሥራ ነው" ይላሉ። "ሁልጊዜ ሰዎችን ለማስደሰት የምትጥሩ ከሆነ፣ የትም አትደርሱም። ለራሳችሁ መደራደር አለባችሁ።"

ከተመካሪዎቿ አንዷ ፌዝ ናት።

ፌዝ "ሁሌ ፈገግ እንድል እና ጥሩ መሆን እንዳለብኝ ጫና እንዳይሰማኝ አስተምራኛለች። እየሰራሁበት ነው" ስትል ምክሩን ተግባራዊ እያደረገች መሆኑን አመልክታለች።