ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሥራ ቦታ ላይ ማልቀስ ሥራችንን የሚጎዳ ወይስ የሰውነት መገለጫ?
ስምንት ሰዓታት እና ከዚያ በላይ በምናሳልፍባቸው የሥራ ቦታዎች የተለያዩ ስሜቶችን ማፈራረቃችን አይቀርም።
በሥራም ይሁን በሌሎች ምክንያቶች ሐዘን ተሰምቶን ብናለቅስ፤ በሥራ ባልደረቦቻችን ዘንድ እንዴት እንታያለን? በአለቆቻችን ዘንድስ?
በቅርቡ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ዋና የፋይናንስ ሚኒስትር እና ፖለቲከኛዋ ሬቸል ሪቭስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክር ቤቱ ካነሷቸው ጥያቄዎች ጋር ተያይዞ ሲያለቅሱ መታየታቸው የበርካታ መገናኛ ብዙኃን ርዕስ ሆኖ ነበር።
ከፖለቲከኛዋ ዕንባ ጋር ተያይዞ በሥራ ቦታቸው ላይ ያለቀሱ በርካታ ሰዎች ለቢቢሲ ያለፉባቸውን ሁኔታዎች አጋርተዋል።
በላንካስተር ነዋሪ የሆነችው የ48 ዓመቷ ክላራ ገና ተመርቃ ሥራ እንደጀመረች "በደስታ ምክንያት" እንዲሁም ከዓመታት በኋላ "ተበሳጭታ" ስሜታዊ ሆና እንዳለቀሰች ትናገራለች።
"ከቤት መጥፎ ዜና ደርሶኝ አልቅሼም አውቃለሁ፤ በዚሁ ወቅት ወዲያውኑ ከሥራ ወጥቼ ሄድኩኝ" ትላለች።
ኤማ በበኩሏ በዋነኝነት ወንዶች በሚበዙበት መሥሪያ ቤት ስለምትሠራ ስሜቷን በውስጧ መደበቅ አለባት። "ስሜቷን በመግለጿ ወይም ደካማነትን በማሳየት" ራሷን ትወቅሳለች።
ምንም እንኳን አንዳንድ ጥናቶች ሴቶች ከወንዶች በበለጠ እንደሚያለቅሱ ቢጠቁሙም በርካታ ወንዶች በሥራ ባልደረቦቻቸው ፊት እንዳለቀሱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ዶክተር ጋይ ክሌተን "ከታካሚዎች፣ ከሥራ ባልደረቦች እና ከቤተሰቦች ጋር ለበርካታ ዓመታት ሐዘናቸውን ተካፍዬ" ብዙ ጊዜ እንዳለቀሱ ይገልጻሉ።
በፋይናንስ ዘርፈ የሚሠራ የለንደን ነዋሪው የ38 ዓመቱ ግለሰብ በበኩሉ በሥራ ቦታው ላይ በግል ጉዳዮችም ቢሆን ሐዘኑን እንደሚገልጽ እንዲሁም በዚህ ስሜት ውስጥ ሆኖ ሥራ ቦታው ላይ መገኘቱ "ሙያዊ ቁርጠኝነት" እንዳለው ማሳያ ነው ይላል።
በሥራ ቦታ ላይ ማልቀስ ደካማነት ወይስ ጥንካሬ?
በሥራ ቦታ ላይ ማልቀስ ደካማነት ወይስ ጥንካሬ? የስኬት አማካሪ እና የቢዝነስ እና ሥራ አስፈጻሚ አሠልጣኝ የሆኑት ሽሪን ሆባን በሥራ ቦታ ላይ ማልቀስ ተቀባይነት የለውም ብሎ ማሰብ ዘመን ያለፈበት እሳቤ ነው ይላሉ።
"ፕሮፌሽናሊዝም ማለት ስሜታችንን ቤታችን ትተን በሥራ ቦታ ላይ መገኘት አለብን የሚለውን ያረጀ እሳቤን ተሻግረናል" የሚሉት አሠልጣኟ "በአሁኗ ዓለም በስሜት ልኅቀትን ማሳየት ጥንካሬ እንጂ ድክመት አይደለም" ሲሉ ያስረዳሉ።
የሙያ አሠልጣኝ የሆኑት ጆርጂያ ብላክበርን በበኩላቸው በሥራ ቦታ ላይ ሠራተኞች መበሳጨታቸው የሚያጋጥም ጉዳይ በመሆኑ ኩባንያዎች እንዲህ ስሜታዊ የሆኑ ሠራተኞችን በምን መንገድ እና እንዴት እንደሚደግፉ ማወቅ አለባቸው ይላሉ።
በዚህም መንገድ ሠራተኞች የበለጠ ምርታማ እንደሚሆኑ ያስረዳሉ።
"ከልብ የሚያደምጡ፣ ርህራሄ የሚያሳዩ እና የሚረዱ አሠሪዎች ለዘለቄታው ሠራተኞቻቸው በሥራቸው ተነሳሸ እና ደስተኛ እንዲሆኑ የማድረግ ዕድሉ ከፍተኛ ነው" ይላሉ።
የማንቸስተር ነዋሪ የሆነችው የአማንዳም ተሞክሮም ይህንኑ ያሳየ ነው።
ከአስራ ሰባት ዓመታት በፊት በማንቸስተር ዩኒቨርስቲ የሥራ ቃለ መጠይቅ እያደረገችበት በነበረበት ጊዜ አባቷ የካንሰር ሕመም እንደተገኘባቸው መስማቷን ተከትሎ አለቀሰች።
ማልቀሷ ሥራውን ከማግኘት አላገዳትም፤ አሁንም በዚያው ሥራ ላይ ናት።
"በሚያሳዝን ሁኔታ አባቴ እስኪሞት ድረስ በሥራ ቦታዬ ላይ ለዘጠኝ ወራት በየቀኑ አለቀስ ነበር። አሠሪዎቼ ምን ያህል አስደናቂዎች እንደሆኑ እንዲሁም የሥራ ቦታዬም እንዴት ግሩም እንደሆነ ያስገነዘበኝ ሁኔታ ነበር። ማልቀስ ምንም ችግር የሌለው ቦታ" ስትል ትገልጻለች።
"ማልቀስን እንመልሰው"
የፋሽን ዲዛይነር ለሆነችው ኤሚ ፓውኒ ያለፈውን ዓመት ያሳለፈችው በፈታኝ ሁኔታዎች ነበር።
በሕይወቷ እየተከሰቱ ያሉ አሰቃቂ ሁነቶች የሥራ ሁኔታዋም ላይ ጫና ማድረሳቸው አልቀረም።
አኪን የተሰኘ የፋሽን ምርት መሥራች የሆነችው ኤሚ፤ በዚህ ሁሉ መካከል ለቀጣዩ ምርቶች ዲዛይን ማውጣት፣ ሠራተኞቹ ደህና መሆናቸውን ማረጋገጥ እንዲሁም ከሥራዋም በተጨማሪ ደግሞ ልጆችን ከትምህርት ቤት መውሰድ፣ ልጆቹን መመገብ የመሳሰሉ በርካታ ተግባሮችንም ማከናወን አለባት።
"በሕዝብ ቦታዎች ላይ፣ መድረክ ላይ አለቅስ ነበር። ማልቀስ ማቆም ያልቻልኩበት ጊዜን ነው ያሳለፍኩት" ትላለች።
በሥራ ቦታ ላይ ስሜታዊነትን ማሳየት "ውግዘት እንደሚደርስበትና"፤ የሰው ልጅ ስብርብር ማለቱን ማሳየት እንደ ችግር ሊታይ አይገባም ትላለች።
"ማልቀስን እንመልሰው፤ ስሜታችንን ማሳየትም እንዲሁ" ስትል አጽንኦት ትሰጣለች።
"በመሪነት ስፍራ ላይ ያሉ ሴቶች ስሜታቸውን ማሳየት መቻል አለባቸው። ይህ ኃያልነት፤ እንዲሁም ጥንካሬ ነው ብዬ አስባለሁ" ብላለች።
የሥራ ኃላፊዎች ቢያለቅሱ እንዴት ይታያሉ?
ማልቀስን ሁሉም ሰው እንደ በጎ ነገር አያየውም።
አንዳንዶች በሰው ልጅ ላይ መፍረድ ሊቃጣቸው እንደሚችሉ የቻርተርድ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አን ፍራንኬ ይናገራሉ።
በሥራ ቦታ ላይ የሚያለቅሱ ሴቶች "በጣም ስሜታዊ" ተደርገው የሚታዩ ሲሆን፤ ወንዶች ካለቀሱ ደግሞ ደካማ እና ለስላሳ ተደርገው እንዲያፍሩ ሊደረጉ ይችላሉ ይላሉ።
ጀማሪ ሠራተኞች ቢያለቅሱ ከአለቆቻቸው በበለጠ ሊታለፉ ይችላሉ፤ ነገር ግን ሁልጊዜም ላይሆን ይችላል ይላሉ።
"ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ቢያለቅሱ አስደንጋጭ አልፎ ተርፎም አግባብነት የሌለው ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ነገር ግን በትክክለኛ መንገድ ከተያዘ ኃያል መልዕክት ሊሆን ይችላል። መሪዎች ሰዎች መሆናቸውን እንዲሁም ለሥራቸውም በጥልቀት እንደሚያስቡ የሚያሳይ ይሆናል" ሲሉ ያስረዳሉ።
ሆኖም በአንዳንድ ተቋማት ላይ በሥራ ኃላፊነት ወደላይ መመንደግ ከፈለጉ ምንም ዓይነት ስሜት አለማሳየት ተመራጭ መሆኑንም ሺሪን ያስረዳሉ።
ማልቀስ በሥራ ላይ ያለን ሹመት ሊጎዳም አንደሚችል ይገልጻሉ።
"እውነት እንነጋገር ከተባለ በአንዳንድ የሥራ ቦታዎች ላይ እርጋታ እንደ ጥንካሬ፣ ስሜትን ማሳየት አለመረጋጋትን እንደሚያሳይ ምልከታዎች አሉ" ይላሉ።
ነገር ግን አንዳንድ ተቋማት ሁኔታዎችን በተለየ መንገድ እንደሚመለከቱት እና "እውነተኛ፤ ከፍተኛ የራስ ግንዛቤ ያላቸው፤ የራሳቸውን ስሜት ጨምሮ የሌሎችን ማስተናገድ ለሚችሉ የሥራ ኃላፊዎች ዋጋ እንደሚሰጡም" ያስረዳሉ።
አንድ ወቅት ላይ ስሜታዊ ቢሆኑ ይህንን ያህል "ሥራዎትን አያበላሸውም" ይላሉ።
ዋናው ነገር "በሥራ ቦታ ላይ ያለዎት ብቁነት፣ በሥራ ቦታ ላይ መገኘት እንዲሁም ተመልሰው ወደ ሥራ መመለስዎት" ነው ሲሉ ይገልጻሉ።
በሥራ ቦታዎት ላይ ሆነው ማልቀስ ቢፈልጉ ምን ማድረግ አለብዎት?
- ከሥራዎ ፈቀቅ ብለው ራስዎን ያዳምጡ
- ስሜትዎትን መደበቅ አያስፈልግዎትም፤ ለሥራዎ እንደሚያሰቡ የሚያሳይ በመሆኑ መጥፎ ነገር አይደለም።
- ድጋፍ እንዳለዎት ሊሰማዎት ይገባል፤ ስለዚህ ከሚያምኑት የሥራ ባልደረባዎ ጋር ይነጋገሩ፤ አጠር ላለ ጊዜ ዕረፍት ይውሰዱ፤ ከአለቃዎ ወይም ከአስተዳደር ድጋፍ ይጠይቁ
- የሥራ ኃላፊዎች እና ባልደረቦች ሠራተኞቻቸው ሲያለቅሱ ሶፍት በመስጠት እያለቀሱ ስለመሆናቸው ዕውቅና መስጠት አለባቸው። ማልቀሳቸውን እንዳላየ አድርገው አያስመስሉ።