ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"አሜሪካ በኢራን ላይ በፈጸመችው ጥቃት ምንም አላተረፈችም" አያቶላህ ኻሜኒ
የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ አሜሪካ በኢራን የኒውክሌር ይዞታዎች ላይ በፈጸመችው ጥቃት "ምንም አላተረፈችም" ሲሉ ተናገሩ።
ኻሜኒ ከእስራኤል ጋር ግጭት ከቆመ በኋላ በሰጡት የመጀመሪያ መግለጫቸው "የአሜሪካ ጥቃት የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር ለማደናቀፍ ያቀደውን ስኬት አላገኘም" በማለት ገልጸዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው የፈጸመችው ጥቃት የኢራንን የኒውክሌር ይዞታዎች "ሙሉ በሙሉ ያወደመ ነው" ቢሉም፤ አያቶላህ ይህንን "ማጋነን" ሲሉ አጣጥለውታል።
ጠቅላይ መሪው ጨምረውም አገራቸው በኳታር የአሜሪካ ጦር ሰፈር ላይ የፈጸመችውን አጸፋ "ከፍተኛ ምት" ሲሉ ነው የጠሩት።
አሜሪካ በበኩሏ ጥቃቱ የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር ያንኮታኮተ ነው በሚለው አቋሟ እንደጸናች ነው።
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት በአገራቸው እና በእስራኤል የተሰበሰቡ የደህንነት መረጃዎች እንደሚያሳዩት "የኒውክሌር መርሃ ግብሩ በእጅጉ መጎዳቱን እና ለዓመታት ወደ ኋላ እንዲመለስ ያደረገው" ነው ብለዋል።
አሜሪካ በኢራን ላይ የፈጸመችው ጥቃት የኒውክሌር ማብላያ ይዞታዎችን እንዳላወደመ ሾልኮ የወጣ የአሜሪካ መከላከያ ማዕከል (ፔንታጎን) የደህንነት ግምገማ ከሰሞኑ አሳይቷል።
ቅድመ ግምገማው ጥቃቱ የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር ምናልባትም በወራት ወደኋላ ሊመልሰው እንደሚችል ነው ያሳየው።
ትራምፕ የኢራን ሶስቱ የኒውክሌር ይዞታዎች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን በተደጋጋሚ ከመናገር በተጨማሪ ሚዲያዎች ሆን ብለው ጥቃቱን ለማሳነስ "አጀንዳ ቀርጸው እየሰሩ ነው" ሲሉ ወቅሰዋል።
መከላከያ ሚኒስትሩ ከአገሪቱ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ዳን ኬይን በመሆን ሐሙስ ዕለት በፔንታጎን በሰጡት መግለጫ ጥቃቱን "ታሪካዊ ስኬት" በማለት አሞካሽተውታል።
በዚህ መግለጫ በተጋጋለ ሁኔታ ከጋዜጠኞች ጋር የተመላለሱት ሚኒስትሩ ኢራን ከአሜሪካ ጥቃት በፊት የበለጸገ የዩራኒየም ክምችቷን ከመሬት በታች ከሚገኘው የፎርዶ የኒውክሌር ጣቢያ ወደ ሌላ ስፍራ አዛውራለች የሚለውን ሪፖርት አጣጥለዋል።
ለሳምንት ያህል ከሕዝብ ዕይታ ርቀው የነበሩት ኻሜኒ ትናንት የሰጡት መግለጫ ጠቅላይ መሪው የት ናቸው የሚለውን መላ ምት ማክተሚያ አድርጎታል።
ኻሜኒ በመጠለያ ውስጥ እንደቆዩ እና ግንኙነታቸውን ገድበው ነበር የተባለ ሲሆን የትናንትናውን መግለጫ ከየት ሆነው እንደሰጡ የተገለጸ ነገር የለም።
ሆኖም ከፍተኛ የአገሪቱ ባለስልጣን ጠቅላይ መሪው ደህንነቱ የተጠበቀ ቦታ ላይ መሆናቸውን ከዚህ ቀደም ተናግረው ነበር።
ኻሜኒ በአገራቸው ላይ ድጋሚ ጥቃት ከተሰነዘረ በመካከለኛው ምስራቅ በሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይ ጥቃት ከመፈጸም ወደ ኋላ እንደማይሉ ተናግረዋል።
ጠቅላይ መሪው አገራቸው በእስራኤል እና በአሜሪካ ላይ ድል ተቀዳጅተናል በማለት "ለህዝባቸው እንኳን ደስ አላችሁ" ብለዋል።
ኻሜኒ፣ ትራምፕ ጥቃቱን "ባልተለመደ መልኩ አጋንነው"አቅርበውታል "ነገር ግን ያከናወኑት ምንም ነገር የለም። አላማቸውንም አላሳኩም" በማለት አጣጥለውታል።
ዋይት ሃውስ ኢራንን ወደ ድርድር ጠረጴዛው ለመመለስ ለሰላማዊ አገልግሎት የሚውል ያልበለጸገ የኒውክሌር ፕሮግራም የገንዘብ ድጋፍ ማመቻቸትን ጨምሮ የተለያዩ አማራጮችን እያጤነ መሆኑን የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ዘግቧል።
ነገር ግን የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከአሜሪካ ጋር የተቃደ ምንም አይነት ውይይት እንደሌለ ሐሙስ ዕለት ለኢራን መንግሥታዊ ቴሌቪዥን ተናግረዋል።