ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"ቆዳዬ እየተላጠ ነበር"- ተጭበርብረው በሩሲያ የድሮን ፋብሪካዎች እንዲሠሩ የተገደዱ አፍሪካውያን ሴቶች
አዳው ሥራዋን በጀመረችበት ቀን ስህተት መሥራቷን ተገነዘበች።
"ዩኒፎርም ተሰጠን። ምን እንደምሠራ አላወቅንም ነበር። በጀመሪያው ቀን የድሮን ፋብሪካ ተወሰድን። ሰዎች ተሰባስበው ድሮን ሲሠሩ ተመለከትን። ከዚያ ወደሌላ የሥራ ቦታ ወሰዱን።"
'አላቡጋ ስታርት ፕሮግራም' ለተባለ ተቋም አመልክታ ነበር የተቀጠረችው። ከ18 እስከ 22 ዓመት ያሉ ሴቶች ላይ ያተኮረ የሥራ መስክ እንደሆነ ተገልጾላታል።
ዋነኛ ትኩረቱ የአፍሪካ ሴት ወጣቶች ላይ ነው። ከላቲን አሜሪካ እና ደቡብ እስያ የሚቀጠሩ ሴቶች ቁጥርም ጨምሯል።
ቀጣሪው ድርጅት የሎጅስቲክስ እንዲሁም የመስተንግዶ ሥልጠና እንደሚሰጥ ገልጿል።
ሆኖም ግን ሥልጠና በመስጠት ሽፋን ወጣቶች በአነስተኛ ገንዘብ እንደሚቀጠሩ እና አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገቡ ክሶች እየቀረቡ ይገኛሉ።
አንድ ደቡብ አፍሪካዊ ተጽዕኖ ፈጣሪ፤ ወጣቶች በ 'አላቡጋ ስታርት ፕሮግራም' እንዲቀጠሩ ማስታወቂያ መሥራቱን ተከትሎ፤ 'ሕገ ወጥ የሰው ዝውውርን' እያስተዋወቀ ነው በሚል ተተችቷል።
ተጽዕኖ ፈጣሪው ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።
'አላቡጋ ስታርት ፕሮግራም' ከመላው አፍሪካ ከ1,000 በላይ ሴቶችን በጦር መሣሪያ ፋብሪካ መቅጠሩ ይታመናል።
ነሐሴ ላይ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ተቋሙ ላይ ምርመራ እንደከፈተ አስታውቋል። ወጣቶች በተቋሙ እንዳይቀጠሩም አሳስቧል።
ለደኅንነቷ ሲባል ስሟ የተለወጠው አዳው ስለ ቅጥሩ የሰማቸው እአአ በ2023 ነበር።
"ጓደኛዬ ሩሲያ ነጻ የትምህርት ዕድል አለ የሚል መረጃ የፌስቡክ 'ስታተስ' አደረገች። በደቡብ ሱዳን የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር በኩል የወጣ ማስታወቂያ ነበር።"
በዋትስአፕ ለተቋሙ መልዕክት ላከች። ከዚያም ስሟን፣ ዕድሜዋን እና ለምን ተቋሙን መቀላቀል እንደፈለገች የሚጠይቅ ፎርም ሞላች።
"መሥራት የምፈልግበትን የሙያ መስክ አስመረጡኝ። ሴቶች በብዛት የማይገቡበትን ሙያ ነበር የፈለግኩት። በተለይ በእኛ አገር ሴቶች ግዙፍ የግንባታ ማሽኖች ላይ አይሠሩም።"
የቪዛ ሒደቱ አንድ ዓመት ወስዶባታል። አምና መጋቢት ላይ ወደ ሩሲያ አቀናች።
"ሩሲያ ስደርስ በጣም ይቀዘቅዛል፤ ጠላሁት። ገና ከአውሮፕላን ማረፊያው ስንወጣ ውርጭ ተቀበለን።"
ብርዱ እንዳለ ሆኖ፤ 'አላቡጋ ስታርት ፕሮግራም' ስትደርስ ባየችው ነገር ደስተኛ ነበረች።
"በጣም ነበር ያስደነቀኝ። ይሆናል ብዬ የጠበቅኩትን ነበር ያገኘሁት። ብዙ ፋብሪካዎች፣ መኪናዎች እና የእርሻ ተቋማት አይቻለሁ።"
አዳው ለሦስት ወራት ቋንቋ ተማረች። ከዚያ በኋላ ግን ሕይወቷ ባልጠበቀችው መንገድ ተመሰቃቀለ።
በሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ፋብሪካ ውስጥ መሥራት ይፈልጉ እንደሆነ ፈቃዳቸውን እንዳልተጠየቁ ትናገራለች።
ስለ ሥራቸው ለማንም መረጃ እንዳይሰጡ አሳሪ ስምምነት (non-disclosure agreements ወይም NDA) ስለፈረሙ ለቤተሰቦቿ መናገር አልቻለችም።
"ሁላችንም ብዙ ጥያቄ ነበረን። ሎጅስቲክስ እና ከፍተኛ የግንባታ ማሽነሪን ጨምሮ በቴክኒክ ዘርፍ ለመሥራት ነበር የተስማማነው።"
'አላቡጋ ስታርት ፕሮግራም' ሠራተኞቹን ማጭበርበሩን ያስተባብላል።
"ሠራተኞቻችን የሚሠሩባቸው ዘርፎች ባጠቃላይ በድረ ገጻችን ተዘርዝረዋል" ሲል ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥቷል።
ሠራተኞቹ ፋብሪካውን ፎቶ ማንሳት ባይፈቀድላቸውም፤ ቢቢሲ አዳው የቀረጸችውን እና በሩሲያ ብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያ አርቲ ላይ የተላለፈ ተንቀሳቃሽ ምሥል ማግኘት ችሏል።
በተቋሙ ውስጥ ኢራን ሠራሽ ድሮኖች (Iranian Shahed 136) ሲመረቱ በቪድዮው ይታያል።
ቪዲዮው ላይ የታየው ፋብሪካ አዳው ትሠራበት የነበረ መሆኑን ለቢቢሲ አረጋግጣለች።
"አላቡጋ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የጦር መሣሪያ ማምረቻ ነው" ሲሉ በኢንስቲትዮት ፎር ሳይንስ ኤንድ ኢንተርናሽናል ሰኪውሪቲ የሚሠሩት ስፔንሰር ፋርጋሶ ይናገራሉ።
"ሩሲያ፤ ሻሐድ 136 ድሮኖችን እያመረተች እንደሆነ አምናለች። በይፋ የለቀቁት ተንቀሳቃሽ ምሥልም ይሄንን ያረጋግጣሉ። ስለ ፋብሪካው እና ስኬቱ በኩራት ይናገራሉ" ይላሉ ባለሙያው።
እንደ አዳው ላሉ ብዙ ሴቶች ቃለ መጠይቅ ያደረጉት ስፔንሰር፤ ሠራተኞቹ የጦር መሣሪያ እያመረቱ መሆኑን እንደማያውቁ ገልጸዋል።
"ከላይ ከላይ ሲታይ እነዚህ ሴቶች አገራትን እንዲያዩ፣ ልምድ እንዲያካብቱ እና ገቢ እንዲያገኙ የሚያስችል ጥሩ ዕድል ይመስላል። ወደ ተቋሙ ሲመጡ ግን ቃል የተገባላቸው እውነት እንዳልሆነ ያውቃሉ። የሥራ ሁኔታውም እንደተነገራቸው አይደለም።"
አዳው በሥራው መቀጠል እንደማትችል አውቃለች።
"ሁሉም ነገር ይገለጥልኝ ጀመር። ማመልከቻ ካስገባሁበት ጊዜ ጀምሮ የተነገሩኝ ውሸቶች በግልጽ ታዩኝ። ከሚዋሹኝ ሰዎች ጋር መሥራት አልችልም። ሕይወቴን የድሮን ፋብሪካ ውስጥ ማሳለፍ አልፈልግም።"
የሥራ መልቀቂያ ስታስገባ በሁለት ሳምንት ውስጥ ጉዳዩዋ እንደሚታይ ተነገራት። ሁለቱን ሳምንታት በሥራ መቀጠል ነበረባት።
በሁለት ሳምንት ውስጥ ድሮን ቀለም እየቀባች ነበር። የቀለሙ ኬሚካል እጇን አቃጥሎታል።
"ቤት ስገባ ቆዳዬን አየሁት፤ እየተላላጠ ነበር። ጓንት እና ጉዳት መከላከያ ልብስ ብናደርግም ኬሚካሉ ሰርጎ መግባት ይችላል።"
'አላቡጋ ስታርት ፕሮግራም' ለሠራተኞቹ አስፈላጊውን የጥንቃቄ አልባሳት እንደሚያሟላ ይገልጻል።
አዳው ሩሲያ በደረሰች በሁለት ሳምንታት ውስጥ እአአ በ2024 በሚያዝያ ወር ፋብሪካው ላይ ዩክሬን የድሮን ጥቃት ፈጽማለች።
"የፋብሪካው የድንገተኛ ጊዜ ደውል ሲጮህ ነቃሁ። ከሌላ ጊዜው የተለየ ነበር። የመኖሪያችን ላይኛው ፎቅ ላይ ያለው መስታወት ተሰባበረ። ፍንዳታውን ሲሰሙ የተወሰኑት ሴቶች ከእንቅልፋቸው ነቁ። ወደ ውጪ ወጣን።"
በቀዝቃዛው ማለዳ ከክፍሏ ስትወጣ አካባቢውን ጥለው የሚሮጡ ሰዎች ተመለከተች።
"ሰዎች ወደላይ ሲጠቁሙ ቀና አልኩ። ድሮን በሰማይ ላይ ሲመጣ ተመለከትኩ። እኔም መሮጥ ጀመርኩ። በፍጥነት ስሮጥ ከፊቴ የነበሩትን ሰዎች ቀደምኳቸው።"
ቢቢሲ፤ ጥቃቱ በተፈጸመበት ቀን አዳው የቀረጸችውን ተንቀሳቃሽ ምሥል ትክክለኛነት ማረጋገጥ ችሏል።
አዳው ሥራውን ከመጀመሯ በፊት ፋብሪካው የድሮን ማምረቻ መሆኑን ጭምጭምታ ሰምታለች። ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ ስትጠይቅ ከምትፈልገው የሥራ ዘርፍ ውጭ እንደማትመደብ ተገለጸላት።
ሆኖም ግን በድሮን ፋብሪካው እንድትሠራ ተገድዳለች።
"የድሮን ፋብሪካ ነው ሲባል ፀረ ሩሲያ ፕሮፓጋንዳ መስሎኝ ነበር። የሩሲያን ስም ለማጠልሸት ብዙ ሐሰተኛ ዜና ይሰማል። በልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ ውስጥ አውሮፓውያን እና አሜሪካውያንም ይሠሩ ነበር። ጦርነቱ ሲጀመር ሩሲያ ላይ ማዕቀብ በመጣሉ ፋብሪካውን ጥለው ወጡ። ሩሲያ አፍሪካውያን ሠራተኞችን መመልመል የጀመረችውም ለዚህ ነው።"
አዳው ሥራ መልቀቂያ ካስገባች በኋላ ቤተሰቦቿ የአውሮፕላን ትኬት ቆረጡላት።
ብዙ ሴቶች ወደ አገራቸው መመለስ የሚችሉበት የገንዘብ አቅም እንደሌላቸው ትናገራለች።
የሚከፈላቸው ገንዘብ በማስታወቂያ ከሚነገረው ያነሰ ነው። አዳው 600 ዶላር እንደምታገኝ ቢገለጽላትም እጇ ላይ የደረሰው 100 ዶላር ገደማ ብቻ ነው።
"የቤት ኪራይ፣ የቋንቋ መማሪያ፣ የዋይ-ፋይ እና የትራንስፖርት እንዲሁም ታክስ ተቀንሶብናል። አንድ ቀን ሥራ ከቀረን 50 ዶላር ይቀነሳል። ምግብ ስናበስል የድንገተኛ ጊዜ ደውል ድምጽ ከተሰማ 60 ዶላር ይቀነሳል። ሩስኪ [የሩሲያ ቋንቋ] ስንማር የቤት ሥራ ካልሠራን ወይም ክፍል ካልገባን ከደመወዛችን ይቀነሳል።"
'አላቡጋ ስታርት ፕሮግራም' ለቢቢሲ እንደገለጸው፤ የሠራተኞችን ደመወዝ የሚወሰነው በውጤታማነታቸው እና በባሕሪያቸው ነው።
ስሟ እንዳይጠቀስ የጠየቀች ቢቢሲ ያነጋገራት ሌላ የፋብሪካው ሠራተኛ በበኩሏ የሥራ ቆይታዋ ጥሩ እንደሆነ ገልጻለች።
"እውነቱን ለመናገር ሁሉም ተቋም ሕግ አለው። ሥራ የቀረ ወይም ውጤታማ ያልሆነ ሰው እንዴት ሙሉ ደመወዝ ያገኛል? ሁሉም ነገር ምክንያታዊ ነው። ማንም የማይፈልገውን እንዲሠራ አይገደድም። አብዛኞቹ ሴቶች ከሥራ ይቀራሉ፤ ደንብ አያከብሩም። ድርጅቱ ማንንም በግዳጅ አልያዘም። በፈለግነው ሰዓት መልቀቅ እንችላለን።"
አዳው ግን ይሄንን አትቀበልም።
"በጣም ነው የተከፋሁት። ወደ ክፍሌ ስመለስ ሁሌም አለቅስ ነበር። እንዴት ራሴን እዚህ አገኘሁት? ብዬ እጠይቃለሁ። የብዙ ሰዎችን ሕይወት የሚቀጥፍ መሣሪያ ሲገነባ እጄ እንዳለበት ማወቄ ያሳዝነኛል።"