ለሥራ ወደ ዱባይ የሚሄዱ ሴቶችን "ለሚያዋርድ የወሲብ ንግድ" የሚያቀርበው ግለሰብ በቢቢሲ ተጋለጠ

ማስጠንቀቂያ፡ የሚረብሽ እና ዝርዝር የወሲብ ተግባራት አገላለጾችን ይዟል

በዱባይ ቅንጡ የመኖሪያ አካባቢዎች የወሲብ ንግድ የሚያካሄዱ ሰዎችን የሚያሰማራው እና ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችን የሚመለምለው ግለሰብ በቢቢሲ የምርመራ ዘገባ ተደረሰበት።

ቻርልስ ምዌሲግዋ የቀድሞ የለንደን የአውቶቡስ ሹፌር እንደነበር የሚናገር ሲሆን፣ ለቢቢሲ ስውር ዘጋቢ ለተለያዩ የወሲብ ዝግጅቶች ከ1000 ዶላር ጀምሮ የሚከፈላቸውን ሴቶች እንደሚያቀርብ ገልጾ አብዛኞቹ ደንበኞቹ የሚጠይቋቸውን "ማንኛውንም ነገር ሊያደርጉ" ይችላሉ ብሏል።

በተባበሩት የአረብ ኢሚሬትስ ወጣ ያሉ የወሲብ ድግሶች እንደሚካሄዱ ለዓመታት በወሬ ደረጃ ሲነገር ቆይቷል።

በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ መዘባበቶችን እና የአንዳንድ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ወጣ ያሉ የወሲብ ትዕይንቶችን በማቅረብ ቅንጡ ሕይታቸውን ይደጉማሉ ከሚሉ ታሪኮች ጋር የተገናኙ ቪዲዮዎች በስፋት ተሠራጭተዋል።

በቲክቶክ ላይ በተለያዩ ሃሽታጎች የቀረቡ እነዚህ ቪዲዮዎች ከ450 ሚሊዮን ጊዜ በላይ ታይተዋል።

የቢቢሲ ወርልድ ሰርቪስ ምርመራ ግን እውነታው የበለጠ የከፋ እንደሆነ አሳይቷል።

ወጣት የኡጋንዳ ሴቶች ለምዌሲግዋ የወሲብ ንግድን በማሳለጥ ላይ እንሳተፋለን ብለው አለመጠበቃቸውን ይናገራሉ።

በአንዳንድ ሁኔታዎች፣ እንደ ሱፐርማርኬቶች ወይም ሆቴሎች ባሉ ቦታዎች ለመሥራት ወደ አረብ ኢሚሬትስ መምጣታቸውን ያምኑ ነበር።

ማንነቷን ለመደበቅ "ሚያ" ብለን የምንጠራት ሴት በሴቶቹ ላይ ለመጸዳዳት የሚጠይቁ ደንበኞች እንደሚገጥሟት ትናገራለች።

አክላም በምዌሲግዋ የወሲብ ንግድ መረብ ውስጥ መያዟን አስረድታለች።

ምዌሲግዋ የሚቀርብበትን ውንጀላ ያስተባበለ ሲሆን ሴቶች በአከራዮች በኩል ማረፊያ እንዲያገኙ እንደሚረዳቸው እና ከዱባይ ባለፀጎች ጋር ባለው ግንኙነት የተነሳ ወደ ተለያዩ ፓርቲዎች ሲሄድ እንደሚያጅቡት ይናገራል።

ከምዌሲግዋ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ሁለት ሴቶች ከሕንጻዎች ላይ ወድቀው መሞታቸውን ቢቢሲ በምርመራ ዘገባው ወቅት ማወቅ ችሏል።

ምንም እንኳን ሞታቸው ራስን ማጥፋት ተብሎ የተመዘገበ ቢሆንም ጓደኞቻቸው እና ቤተሰቦቻቸው ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራ ማድረግ እንዳለበት ያምናሉ።

ምዌሲግዋ ክስተቱ በዱባይ ፖሊስ ምርመራ እንደተደረገበት ገልጾ ለተጨማሪ መረጃ ልናናግራቸው እንደምንችል ተናግሯል።

ፖሊስ ግን ለጥያቄያችን ምላሽ አልሰጠንም።

ሕይወታቸውን ካጡ ሴቶች መካከል አንዷ የሆነችው ሞኒክ ካሪንጊ ወደ ዱባይ የሄደችው ከምዕራብ ኡጋንዳ ነው።

ዱባይ ውስጥ ትኖር የነበረው ለምዌሲግዋ ከሚሠሩ በርካታ ሴቶች ጋር በጋራ ነው።

ከሞኒክ ጋር ከ2022 ጀምሮ መኖሯን የምትናገረው ኬይራ "ቦታው ልክ እንደ ገበያ ነው. . . 50 የምንሆን ሴቶች ነበርን። የጠበቀችውን ስላላገኘች ደስተኛ አልነበረችም" ብላለች።

እህቷ ሪታ እንደምትለው ከሆነ ሞኒክ በዱባይ የሚጠብቃት ሥራ በሱፐር ማርኬት ውስጥ እንደሆነ ነበር የምታውቀው።

በዱባይ ሞኒክን ታውቃት እንደነበር የምትነገረው ሚያ "ወደ ቤቴ መሄድ እንደምፈልግ ስነግረው በጣም ይቆጣ ነበር" ትላለች።

መጀመሪያ ዱባይ እንደደረሰች 2,711 ዶላር አካባቢ ዕዳ እንዳለባት እንደነገራት እና በሁለት ሳምንት ውስጥ ይህ ዕዳዋ በእጥፍ ማደጉን ትናገራለች።

ዕዳዋን ዘርዝራ ስታስረዳም "ለአውሮፕላን ቲኬት፣ ለቪዛ፣ ለማደሪያ እና ለምግብ የወጣ ወጪ ነው" ትላለች ሚያ።

"ያ ማለት ጠንክሬ መሥራት አለብኝ ማለት ነው፣ በጣም ጠንክሬ፣ እጅግ ጠንክሬ ወንዶች መጥተው አብረውኝ እንዲተኙ እየለመንኩ" ትላለች ሁኔታውን ስታስረዳ።

ስሙን ማይክል ብለን የምንጠራው የሞኒክ ዘመድ ደግሞ ዱባይ በደረሰች በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የምዌሲግዋ 27 ሺህ ዶላር ዕዳ ነበረባት ሲል ይናገራል።

በወቅቱ እያለቀሰች የድምጽ መልዕክት እንደላከችለት ያስታውሳል።

ሚያ አብዛኛውን ጊዜ ደንበኞቿ አውሮፓውያን እንዲሁም ወጣ ላለ ወሲብ ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው ወንዶች መሆናቸውን ትናገራለች።

"ሴቶች ላይ መጸዳዳት የሚወድ ደንበኛ ነበረ። ተጸዳድቶ እንዲበሉት ይነግራቸዋል" ስትል ትገልጻለች።

ሌክሲ ስንል የምንጠራት ሌላ ሴት ደግሞ በሌላ ግለሰብ መመልመሏን ትናገረለች።

ሚያ ስለደንበኞቿ ከገለፀችው ሃሳብ ጋር በሚስማማ መልኩ "ክብርን ዝቅ የሚያደርጉ ጥያቄዎች በተደጋጋሚ እንደሚቀርቡ ገልጻለች።

"በቡድን ወሲብ የምንፈጽም ከሆነ ፊትሽ ላይ የምንሸና፣ የምንመታሽ ከሆነ 15,000 የአረብ ኢሚሬትስ ድርሃም እንከፍልሻለን፤ ሰገራችንን ስትበይ የምንቀርጽሽ ከሆነ ደግሞ 5,000 እንጨምራለን' የሚሉ ደበንበኞች አሉ።"

እንደዚህ ያሉ ወጣ ያሉ የወሲብ ፍላጎቶች እና ጥያቄዎችን ስትመለከት አብሮት የዘር ጉዳይ ሊኖረው እንደሚችል ትጠረጥራለች።

"እንዲህ ዓይነት ነገር ማድረግ አልፈልግም ባልኩ ጊዜ ሁሉ የበለጠ የመፈጸም ፍላጎት ያድርባቸዋል።የሆነ የሚያለቅስ እና የሚጮህ እንዲሁም የሚሮጥ ሰው ይፈልጋሉ። ያ ሰው ደግሞ (በእነርሱ ዓይን) ጥቁር መሆን አለበት።"

ሌክሲ በዚህ ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ ሊያስጥላት ይችላል ብላ ላመነችው ብቸኛ አካል፣ ፖሊስ፣ አቤት ብላለች።

ነገር ግን "እናንተ አፍሪካውያን አንዳችሁ ሌላኛችሁ ላይ ችግር ትፈጥራለችሁ። እዚህ ውስጥ መሳተፍ አንፈልግም። ካሉ በኋላ ዘጉብኝ" ስትል ጉዳዩን ባሳወቀችበት ወቅት የተፈጠረውን ታስታውሳለች።

ቢቢሲ ይህንን ጥያቄ ለፖሊስ ቢያቀርብም ምላሽ አላገኘም።

ሌክሲ ወደ ኡጋንዳ አምልጣ መሄድ የቻለች ሲሆን አሁን በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሴቶችን ለመርዳት እና ለማስወጣት ትንቀሳቀሳለች።

ቻርለስ ምዌሲግዋን ፈልጎ ማግኘት ቀላል አልነበረም። በድረገጾች ላይ የነበረው አንድ ፎቶ ብቻ ሲሆን እርሱም ቢሆን የተወሰደው ከጀርባ ነው።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይም የተለያዩ ስሞችን ይጠቀማል።

ነገር ግን ኦፕን ሶርስ ኢንተለጀንስ፣ ስውር ምርመራ እና የእርሱ የወንጀል መረብ የቀድሞ ባልደረባ ከሆኑ የተገኘን መረጃ በመጠቀም በዱባይ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች በሚኖሩበት ጁሜራህ ቪሌጅ ሰርክል አገኘነው።

ስለሚያካሄዳቸው ንግዶች፣ ክብረ ነክ ለሆኑ የወሲብ ተግባራት ሴቶች ያቀርባል የሚለውን የመረጃ ምንጮቻችንን የነገሩንን ለማጠናከር፣ ራሱን የተለያዩ ፓርቲዎችን የሚያዘጋጅ ግለሰብ አድርጎ ያቀረበ እና የናየጡ ሐብታሞች ለሚገኙበት ፓርቲ ሴቶችን እንደሚፈልግ የገለፀ ስውር ዘጋቢ ላክን።

ምዌሲግዋ ስለ ንግዱ ሲያወራ ተረጋግቶ እና በራስ መተማመን ነው።

"25 ያህል ሴቶች አሉን" ብሏል።

"አብዛኞቹ የተጠየቁት ለመፈጸም ፈቃደኞች ናቸው. . . ሁሉንም ነገር ያከናውናሉ።"

ክፍያቸውም ለአንድ ሌሊት ለአንዲት ሴት 1,000 ዶላር መሆኑን እና "ወጣ ላሉ ነገሮች" ግን ተጨማሪ እንደሚያስከፍል ተናግሯል።

ዘጋቢያችንንም "አንድ ምሽት ላይ ተገኝቶ" የሚሆነውን ለቅምሻ ማየት እንደሚችል በመግለጽ ጋብዞታል።

በንግግራቸው መካከልም በለንደን የአውቶቡስ ሹፌር እንደነበር ተናግሯል።

በአውሮፓውያኑ 2006 በምሥራቅ ለንደን የአውቶቡስ ሹፌር ሆኖ መሥራቱን የሚያሳይ ይፋዊ ሰነድ ተመልክተናል።

ለዘጋቢያችን በተጨማሪ ሥራውን እንደሚወደው ጨምሮ ተናግሯል።

"በሎተሪ ሚሊዮን ፓውንድ ላሸንፍ እችላለሁ። ነገር ግን ያ ቢሆን አንኳ እሠራዋለሁ. . . የሕይወቴ አካል ሆኗል።"

ለምዌሲግዋ የኦፕሬሽን ማናጀር ሆኖ ይሠራ እንደነበር የተናገረው ትሮይ ሥራውን እንዴት እንደሚያከናውን ተጨማሪ መረጃ ሰጥቶናል።

ምዌሲግዋ በተለያዩ የምሽት ክበቦች ለሚገኙ የደኅንነት ሰዎች ገንዘብ በመክፈል ሴቶቹ ገብተው ደንበኞችን እንዲፈልጉ ያደርጋል ብሏል።

"በሕይወቴ አይቼ ስለማላውቀው የወሲብ ዓይነቶች እሰማለሁ። እርሱ ሀብታም ሰዎች ደስተኛ እስከሆኑ ድረስ በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ብናልፍ ግድ አይሰጠውም። . . .[ሴቶቹ] ማምለጫ የላቸውም. . . ድምጻውያንን፣ እግር ኳስ ተጫዋቾችን፣ ፕሬዝዳንቶችን ያገኛሉ።"

ምዌሲግዋ ይህንን ሥራ እየሠራ ከሕግ አምልጦ እንደሚኖር ትሮይ ያምናል።

ምክንያቱም ትሮይ እና ሌሎች ሹፌሮቹ ብቻ አልነበሩም።

ምዌሲግዋ በስማቸው መኪኖችን እና አፓርትመንቶችን ለመከራየት ስለሚጠቀም የእርሱ ስም በውሎች ላይ ሰፍሮ እንደማይገኝ ይገልጻል።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ሚያዝያ 27/2022 ሞኒክ በዱባይ የውጭ ዜጎች መኖሪያ በሆነው አል ባርሻ መሆኗን የሚያሳይ ሰልፊ ተነስታ ለጥፋለች።

ከአራት ቀን በኋላ ሞተች። በኤሜሬትስ የቆየችው ለአራት ወር ብቻ ነበር።

ሚያ እንደምትለው ከሆነ ሞኒክ እና ምዌሲግዋ በእርሱ ስር በቆየችባቸው ወቅት በተደጋጋሚ ይጨቃጨቁ ነበር።

ሚያ እንደምታስረዳው ሞኒክ ምዌሲግዋ የሚላትን ለመፈጸም ዳተኛ ስትሆን ከእርሱ መረብ ለመውጣትም ችላ ነበር።

"የሆነ ሥራ አግኝታ ነበር። በጣም ደስተኛ ሆና ነበር። ነጻ የምትሆን መስሏት ትክክለኛ ሥራ ስላገኘች ከወንዶች ጋር መተኛት ስለቀረ የራሷን ሕይወት ራሷ እንደምትመራው አስባ ነበር" ትላለች።

ሞኒክ ጥቂት ሜትሮች ራቅ ብሎ የሚገኝ ሌላ አፓርታማ ውስጥ ቤት አገኘች።

ከዚህ የአፓርታማ በረንዳ ላይ ነው ግንቦት 1/2022 ወድቃ ሕይወቷ ያለፈው።

ሞኒክ በሞተችበት ወቅት በዱባይ የነበረው ዘመዷ ማይክል መልስ ለማግኘት መሞከሩን ይናገራል።

ፖሊስ ሞኒክ ትኖርበት በነበረው አፓርትመንት ውስጥ መጠጥ እና አደንዛዥ ዕጽ በማግኘቱ እንዲሁም በበረንዳው ላይ የእርሷ የጣት አሻራ ብቻ ስለተገኘ የሚያደርገውን ምርመራ ማቋረጡን ነግሮታል።

ሆስፒታል የሞኒክን ሞት የሚያረጋግጥ ምስክር ወረቀት የሰጠው ቢሆንም እንዴት እንደ ሞተች አይገልጽም።

በዚያ አፓርታማ ውስጥ የሚኖር ጋናዊ ግን የሞኒክ አለቃ ነው የተባለ እና በሌላ ሕንጻ የሚኖርን ሰው በማገናኘት አግዞታል።

ማይክል የሴቶቹ መኖሪያ ነው ወደ ተባለው ክፍል ሲደርስ ክፍሉ በሺሻ ጭስ ታፍኖ እንደነበር ያስታውሳል።

በጠረጴዛ ላይም ኮኬይን የሚመስል ነገር መመልከቱን እና ሴቶች ከደንበኞቻቸው ጋር ወንበር ላይ ወሲብ ሲፈጽሙ እንደነበር ይናገራል።

ቻርልስ ምዌሲግዋን ከሁለት ሴቶች ጋር አልጋ ላይ እንዳገኘው ገልጾ ወደ ፖሊስ ለመውሰድ ሲጎትተው "በዱባይ 25 ዓመት ኖሪያለሁ። ዱባይ የእኔ ናት. . . ልትከሰኝ የምትችልበት መንገድ የለም. . . ኢምባሲው ነኝ፤ ኢምባሲው እኔ ነኝ" እንዳለው ይናገራል።

"[ሞኒክ] የመጀመሪያዋ አይደለችም ስትሞት። የመጨረሻዋም አትሆንም" ሲል መናገሩን ማይክል ለቢቢሲ ገልጿል።

ሚያ እና ኬይራ ይህንን የሁለቱን ግለሰቦች ምልልስ መስማታቸውን በተለያየ ጊዜ ተናግረዋል።

ምዌሲግዋን ምን ማለቱ እንደሆነ ስንጠይቀው እንደዚያ ማለቱን ክዷል።

የሞኒክ ሞት ካያላ ቢሩንጊ ከምትባል ሌላ ኡጋንዳዊት አሟሟት ጋር በጣም ተመሳሳይነት አለው።

በ2021 በተመሳሳይ አካባቢ ከሚገኝ ሕንጻ ላይ ወድቃ የሞተችው ቢሩንጊ ትኖርበት የነበረው ሕንጻ በቻርለስ ምዌሲግዋ የተያዘ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ።

የካይላ ቤተሰብ የአከራይዋን ስልክ የሰጡን ሲሆን፣ ይህም የምዌሲግዋ ቁጥር ሆኖ ተገኝቷል።

ትሮይ እንዲሁም አራት ሌሎች ለዚህ የምርመራ ዘገባ ያነጋገርናቸው ሴቶች እርሷ ትኖርበት የነበረውን ሕንጻ ምዌሲግዋ ያስተዳድረው እንደነበር አረጋግጠዋል።

የካይላ ቤተሰቦች ልክ እንደ ሞኒክ ቤተሰቦች ሁሉ ሞቷ ከአልኮል እና አደንዛዥ ዕጽ ጋር የተያያዘ መሆኑን መስማታቸውን ተናግረዋል።

ነገር ግን ቢቢሲ የተመለከተው የአስከሬን ምርመራ ሪፖርት በሞተችበት ወቅት ምንም ዓይነት መጠጥም ሆነ ዕጽ በደሟ ውስጥ መገኘቱን አይሳይም።

የካይላ ቤተሰቦች አስከሬኗን አስመጥተው የቀበሩ ሲሆን፣ የሞኒክ ቤተሰብ ግን ይህንን ማድረግ አልቻለም።

የቢቢሲ ምርመራ ሞኒክ በዱባይ አል ቁዋሳኢስ የመቃብር ስፍራ "የማይታወቁ" የሚለው አካባቢ ተቀብራ ሊሆን እንደሚችል ሰምቷል።

ቦታው ምልክት ያልተደረገባቸው በርካታ የመቃብር ስፍራዎችን ያዘ ሲሆን፣ ቤተሰቦቻቸው አስከሬናቸውን መውሰድ ያልቻሉ ስደተኞች መቀበሪያ ቦታ ነው።

ሞኒክ እና ካይላ ኡጋንዳን ከባሕረ ሰላጤዋ አገር ጋር የሚያገናኝ ስውር የሆነ ሰፊ የወንጀል መረብ ማሳያዎች ናቸው።

ኡጋንዳ እየጨመረ ካለ ሥራ አጥነት ጋር ስትታገል ወደ ባሕረ ሰላጤው አገራት ሄዶ መሥራት ለአገሪቱ ምጣኔ ሃብት በየዓመቱ 1.2 ቢሊዮን ዶላር የገቢ ግብር ያስገኛል።

ይህ ግን አደጋን አዝሎ ይዟል።

ኡጋንዳዊቷ አክቲቪስት ማሪያም ምዊዛ ከባሕረ ሰላጤው አገራት በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የነበሩ 700 ሰዎችን ማትረፏን ትናገራለች።

"በሱፐርማርኬት ውስጥ እና ሌሎች ቦታዎች ሥራ እንደሚያገኙ ቃል ተገብቶላቸው ከሄዱ በኋላ ለወሲብ ንግድ ይሸጣሉ" ስትል ነግራናለች።

ለሞኒክ ቤተሰቦች ሐዘናቸው ከፍርሃት ጋር ተሳስሮባቸዋል። እርምጃ የማይወሰድ ከሆነ ሌሎች ቤተሰቦችም ተመሳሳይ ስቃይ ውስጥ ይገባሉ የሚል ፍርሃት አላቸው።

"ስለ ሞኒክ ህልፈት እያሰብን ነው" የሚለው ዘመዷ ማይክል "ነገር ግን በሕይወት ለተረፉት ሴቶች ማን አላቸው? እስካሁን እዚያው ናቸው፤ አሁንም በስቃይ ውስጥ" ይላል።

ቢቢሲ በምርመራው የቀረበበትን ክሶች በሚመለከት ምላሽ እንዲሰጥ ቻርለስ "አቢ" ምዌሲጋዋን ጠይቋል። ሕገ ወጥ የወሲብ ንግድ ውስጥ መሠማራቱን ክዷል።

"እነዚህ የውሸት ክሶች ናቸው" ብሏል።

"ነግሬሃለሁ እኔ የምሽት መዝናኛ ላይ ገንዘብ ያላቸውን ሰዎች የምጋብዝ ሰው ነኝ። በመሆኑም ብዙ ሴቶች ወደ እኔ ይጎርፋሉ። ይህም ብዙ ሴቶችን እንዳውቅ አድርጎኛል፤ ይኸው ነው።"

አክሎም "[ሞኒክ] እስከ ፓስፖርቷ ነው የሞተችው። ማለትም ማንም ሰው እርሷን ወስዶ ገንዘብ አልጠየቀም። ከመሞቷ በፊት ከአራት እስከ አምስት ሳምንት ለሚሆን ጊዜ አላገኘኋትም" ብሏል።

"[ሞኒክ እና ካይላ]ን አውቃቸዋለሁ። ከተለያዩ አከራዮች ቤት ተከራይተው ነበር። በእነዚህ ሁለት ቤቶች ማንም ካልታሰረ ምክንያቱ ይህ ነው። ሁለቱም ክስተቶች በዱባይ ፖሊስ ምርመራ ተደርጎባቸዋል። ምናልባት እነሱ ሊረዷችሁ ይችላሉ"።

ቢቢሲ የሞኒክ ካሩነጊ እና ካይላ ቢሩነጊን መዝገብ ለማየት አል ባርሻ ፖሊስ ጣቢያን ጠይቋል።

ለዚህ ጥያቄም ሆነ የሞኒክ እና ካይላ ሞት በሚገባ አለመመርመሩን በሚመለከት ለቀረበው ክስ ምላሽ አልሰጠም።

ቢቢሲ የሞኒክ ካሩነጊ አስከሬን ምርመራ ሪፖርት ማግኘት ያልቻለ ሲሆን፤ ከመሞቷ በፊት ትኖርበት የነበረውን ቤት ያከራያትን ግለሰብም ማነጋገር አልቻለም።