ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
“የምወልዳትን ልጅ ላለማየት ፈረምኩ” ኢትዮጵያዊቷ ስደተኛ በጣልያን
‘ምጡን እርሺው ልጁን አንሽው’ አልተባለችም። ደረቷ ላይ አስተኝታ ልጇን አላጠባችም። የምታውቃት በማህጸኗ ሳለች ነው። እዚያም ቢሆን ብዙ አላወሩም፤ ስሜት ለስሜትም አልተገናኙም። እርግጫዋን እና መገለባበጧን አላዳመጠችም።
ይህንን የምታዳምጥበት ጊዜ እና መረጋጋቱም አልነበራት።
ይባስ ብሎ የወለደቻትን ልጅ ላለማየት ፊርማዋን ለማኖር ተገደደች።
አባይ ግርማ ከዚህ የእናቶችን አንጀት ከሚያላውስ ፈተና ጋር ያጋፈጣት ታሪኳ የሚጀምረው ከአፍላ ዕድሜዋ ነው።
አባቷ ልጆቻቸው የተሳካ ሕይወት ሲኖሩ ማየት የምንጊዜም ህልማቸው ነበር። እንዳሰቡት ግን ልጆቻቸው ቦታ አልያዙላቸውም።
አባይም በትምህርቷ ውጤታማ አልነበረችም። በዚህም ያዝኑ ነበር።
ነጋ ጠባ በሐዘን የተሞላ የአባቷን ገጽታ የምታየው አባይ፣ በለጋ ዕድሜዋ ስደትን ያስመረጣት የተለየ ሌላ ምክንያት አልነበራትም። እንደ ማንኛውም ሰው ሕይወትን ማሻሻል ነው።
ከአዲስ አበባ ዳርቻ በምትገኘው ሞጆ ከተማ ተወልዳ ያደገችው አባይ፣ በአኩዮቿ አነሳሽነት ስደትን ‘ሀ’ ብላ የጀመረችው በዱባይ ነው።
ዱባይ ግን እጇን ዘርግታ አልተቀበለቻትም።
በእርሷ ልጅነት እምነት ያጡት አሰሪዎቿ 6 ወር ሙሉ ያለደመወዝ ነበር ያሠሯት። በእነዚያ ጊዜያት ከቤተሰቦቿ ጋር በስልክም ሆነ በደብዳቤ ግንኙነት አልነበራትም። ቤተሰቦቿም የት እንዳለች አያውቁም ነበር።
“ድብደባ እና የዘረኝነት ስድብ ይደርስብኝ ነበር። እረፍት አልነበረኝም። ባለ ሦስት ወለል የሆነውን ቤት ግቢ ማጽዳት፣ ምንጣፍ እና መኪና ማጠብ እንዲሁም በሌላም ሥራ ተጠምጄ ነበር የምውለው። በቀን ሁለት አሊያም ሦስት ሰዓታት ነበር የምተኛው” ስትል ታስታውሳለች።
በዚህ የተማረረችው አባይ፣ ጠፍታ ወደ ሻርጃ በማቅናት በሕገ ወጥ መንገድ በሌሎች ቦታዎች ተቀጥራ ለመሥራት ብትሞክርም ያሰበችው አልሆነም።
ይባስ ብሎ በአንድ ወቅት ከኮርኒስ ውስጥ እቃ እያወረደች ሳለ ወድቃ ከሞት ነው የተረፈችው።
ከጉዳቷ ስታገግምም ከሌሎች ሰነድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ጋር ተይዛ ለአንድ ሳምንት ያህል በእስር ቤት አሳልፋለች።
ከእስር ቤት እንደወጣችም ለአራት ዓመታት በስደት ከኖረችበት ዱባይ ታፍሳ ወደ ኢትዮጵያ ተልካለች።
ነገር ግን ስደትን በቃኝ አላለችም።
በአራት ዓመታት የዱባይ ቆይታዋ እዚህ ግባ የሚባል ነገር ባታተርፍም፣ በሌላኛው መንገድ ደግሞ መሞከርን አሰበች። በአጋጣሚ ያገኘችውን ዕድል ተጠቅማ ወደ ሱዳን ተጓዘች።
በእርግጥ በሱዳን ያን ያህል የከፋ ነገር አልገጠማትም። በሰው ቤት ተቀጥሮ ከመሥራት የራሷን ምግብ ቤት እስከመክፈት ደርሳ ነበር።
በዚህ መሃል ግን ከአንድ ወጣት ጋር በፍቅር ወደቀች። እርሱም ስደተኛ ነው።
አባይ እንደምትለው የፍቅር አጋሯ ወደ ሱዳን ያቀናው በማንነት ጥያቄ ምክንያት ነበር።
አባቱ ጀርመን ነበር የሚኖሩት። እርሱ ግን አያውቃቸውም። ‘አባቴ ማን ነው? የት ነው ያለው?’ በሚል ጥያቄ የናወዘው ወጣት ወደ ጀርመን ተጉዞ አባቱን ለማግኘት ነበር ህልሙ።
የሕይወት መስመር ከዚያ እና ከዚህ ብሎ ያገናኛቸው ሁለቱ ጥንዶች ምንም እንኳን በሱዳን ያለው ሕይወታቸው እየተደላደለ ቢመጣም የእርሱ አባቱን የማግኘት ህልም ስላየለ በዚያ ኑሯቸውን ለማድረግ አልቻሉም።
በረሃ እና ባሕሩን አቆራርጦ አውሮፓ መግባት የግድ ነበር።
ያላቸውን ንብረት ሻሽጠው ለሌላ ስደት እግራቸውን አነሱ። እርሷ በአውሮፕላን እንድትከተለው ተስማምተው እርሱ ቀድሞ ከሱዳን ወጣ።
ከአንድ ወር በላይ በሰሃራ በረሃ
አባይ ሱዳን በነበረችበት ወቅት ተገቢው ሰነድ ስለነበራት በአውሮፕላን ለመከተል ነበር ዕቅዳቸው።
ነገር ግን ያሰቡት ባለመሳካቱ ከአንድ ወር በኋላ በዚያው በረሃ ተከተለችው።
“ቀላል መስሎኝ ነበር” የምትለው አባይ፣ በሕይወቷ እንደዚያ ዓይነት ፈተና ገጥሟት እንደማያውቅ ትናገራለች።
ሊቢያ ለመግባት ረጅሙን እና የማያልቀውን በረሃ ያቆራረጡት በሦስት ፒክ አፕ መኪና ከ300 በላይ የሚሆኑ ስደተኞች በተጨናነቀ ሁኔታ ተጭነው ነበር።
“ሁለቱ ትከሻዬ ላይ ሰዎች ተቀምጠዋል፤ ጉልበቶቼም ላይ ሰዎች ተቀምጠዋል። በዚህ ሁኔታ ነበር የተጓዝነው” ትላለች።
በመኪናዎች መበላሸት እንዲሁም መንገዱ አስተማማኝ ሳይሆን ሲቀር እየተደበቁ ከአንድ ወር በላይ በሰሃራ በረሃ ላይ አሳለፉ።
የሚጠጣም ሆነ የሚቀመስ የለም። ውሃ ሲጠማቸው በቤንዚን ጀሪካን የተሞላ ውሃ ነበር የሚጎነጩት።
አባይ እንደምትለው በባዶ ሆዳቸው የጠጡት ንጹህ ያልሆነ ውሃ የሚፈጥረው ግሳት የቤንዚን ነበር።
በጉዞው ላይ በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት እና በደል ቢኖርም በውሃ ቀጠነ ወንዶቹ ላይ የሚበረታው የደላሎቹ ክንድም ያሳቅቅ ነበር።
ይህንን መቋቋም አቅቷቸው እየተንጠባጠቡ በበረሃው ወድቀው የቀሩ እንዳሉም አባይ ታስታውሳለች።
በዚህ ሁኔታ ወደ ሊቢያ የድንበር መቆጣጠሪያ ኬላ አቅራቢያ ሲደርሱ ከፒክ አፑ መኪና ወደ ረዥም ተጎታች መኪና አዘዋወራቸው።
“ከላያችን ላይ እንጨት ተረብርቦ ‘በጎች ናቸው’ ብለው አሳለፉን” ትላለች አባይ።
አባይ ኬላውን ካለፈች በኋላ በሊቢያ ከሚቀልቧቸውና ከስደተኞች ገዥ እና ሻጮች ለማምለጥ ከመኪናው እንደወረደች ታክሲ ይዛ የፍቅር ጓደኛዋ ወዳለበት ቦታ ከነፈች።
ብዙዎች የሚገጥማቸውን ስቃይና ፈተናም እንደ ዕድል አለፈች።
ቀድሞ ሊቢያ የገባው የፍቅር ጓደኛዋ አገሩን በመጠኑም ቢሆን ለምዶት ስለነበር ለዕለት ጉርስ የሚሆኑ የተወሰኑ ሥራዎችን እየሠሩ የባሕር ጉዞ የሚያደርጉበት ቀን እስከሚደርስ መጠባበቅ ያዙ።
ወደ ባሕር የመውረጃ ቀን (ዜሮ ሰዓት)
ይህ ቀን ደላሎቹ ሁኔታዎችን ፈትሸው እና ገምግመው ስደተኞችን ለባሕር ጉዞ የሚያመቻቹበት ነው።
እነአባይ ማቄን ጨርቄን ሳይሉ ወደተባሉበት ቦታ ወረዱ።
ደላሎቹ ባሕሩ ዳርቻ ከመድረሳቸው በፊት ባዘጋጁት ማጎሪያ ስደተኞቹን እየወሰዱ ይሰበስባሉ። ሕጻናት፣ ሴቶች፣ ወጣቶች በዚያ ቦታ ታጭቀዋል። እነርሱን ተቀላቀሉ።
አባይ በተጓዘችበት ወቅት እርሷን ጨምሮ በርካታ ነፍሰ ጡር ሴቶች ነበሩ። አብዛኞቹ ቀናቸው የደረሰ ነው።
የሚበላም ሆነ የሚጠጣ ነገር የለም። አልፎ አልፎ እንዳይሞቱ እንዳይሽሩ የሚያደርገውን ጁስ እያመጡ ይወረውሩላቸዋል።
በረሃብ መቀጣት ያዙ። በበረሃው የተዳከመው አቅማቸው እየተሟጠጠ መጣ።
በዚህ ሁኔታ ሁለት ሳምንታትን ካሳለፉ በኋላ ከታጎሩበት እንዲወጡ ታዘዙ። የሚጠብቃቸው መኪና የቆመው ካሉበት ራቅ ብሎ ነበር። በእርግጥ መኪናው እነርሱ የሚሳፈሩበት አይደለም።
እንደ እንስሳ ከኋላ ሆነው እየገረፉ ስደተኞችን የሚያሯሩጡ ደላሎች የሚጠቀሙበት ነው።
“ነፍሰ ጡር የለ ሕጻን እያሯሯጡ ነበር የሚወስዱን። እነርሱ በመኪና እየተከተሉን ዘግየት ያለውን. . . ከኋላ እየደበደቡ ያስሮጡናል። በዚህ መሃል የሚወድቀው በርካታ ነው” ትላለች አባይ የነበረውን ሁኔታ ስታስታውስ።
ከዚያም ኮንቴይነር አምጥተው በቁማቸው ጫኗቸው። ጉዟቸው በዚህ የሚጠናቀቅ አልነበረም።
ከተሽከርካሪው ወርደው ወደ ባሕሩ ዳርቻ እንደገና በሩጫ መጓዝ ይጠበቅባቸዋል። እንደምንም ወደ ኋላ የሚቀረው እየቀረ የበረቱት ባሕሩ ጋር ደረሱ።
አነስተኛ መናኛ ጀልባ ተዘጋጅታለች። ይህች ጀልባ ወደ ተዘጋጀች እና መልህቅ ወደሌላት አነስተኛ መርከብ የምታደርሳቸው ናት። በጀልባዋ ትንሽ ከተጓዙ በኋላ ስትጠብቃቸው በነበረችው አነስተኛ መርከብ ላይ ተሳፍረው አደገኛውን ጉዞ ጀመሩ። አባይ እንደምትለው በቁጥር 360 አካባቢ ይሆናሉ።
“ቀና ስንል ሰማይ፣ ዝቅ ስንል ባሕር ነው። ምንም የሚታይ ነገር የለም። የሞት እና የሽረት ጉዳይ ነው። ከፈጣሪ በስተቀር ሌላ የምናስበው ነገር አልነበረም።”
ባሕሩን ካጋመሱ በኋላ የሚሄዱበትን አቅጣጫ የሚያመለክታቸው ካርታ [አቅጣጫ ጠቋሚ] ጠፋ።
ከ36 ሰዓታት ፈታኝ የባሕር ጉዞ በኋላም በጣልያኗ የባሕር ዳርቻ ላምፔዱሳ ደረሱ።
በዚህ ጊዜ አባይ አምስተኛ ወሯ እየገባ ነበር።
“ነፍሰ ጡር ብሆንም ሆዴ አይጨምርም ነበር” የምትለው አባይ፣ ላምፔዱሳ ሰነድ ለሌላቸው ስደተኞች በሚሰጥ ነጻ ሕክምና ምርመራ ካደረገች በኋላ ዶክተሯ ስትደናገጥ እንደተመለከተቻች ትናገራለች።
ጣልያንኛ ስለማትችል የተፈጠረው አልገባትም ነበር። የሰጠቻትን የሕክምና ማስረጃ ይዛ ወደ ቀይ መስቀል ይዘዋት ሄዱ። እዚያም ባዩት የሕክምና ማስረጃዋ ተደናገጡ።
ለ15 ቀናትም ሆስፒታል ተኛች። ይህ ለእርሷም እንቆቅልሽ ነበር የሆነባት።
“ከመጨነቅ ባለፈ የሆነው ነገር አልገባኝም ነበር። ከማልቀስ ውጪ ምርጫ አልነበረኝም” ትላለች አባይ።
በሆድሽ የያዝሽው ፅንስ ጤናማ አይደለም የሚል መርዶ የተነገራት ከብዙ የሕክምና ምልልስ በኋላ ነበር።
ፅንሱን ለማቋረጥ ጊዜው አልፏል። የተሻለ ሕክምና የምታገኝበትም ቤሳ ቤስቲን አልነበራትም።
በመሆኑም ልጇን ባታቅፋትም ዘጠኝ ወራትን ጠብቃ ለመገላገል ወሰነች።
“የምወልዳትን ልጅ ላለማየት ፈረምኩ”
በቀዶ ሕክምና የመጀመሪያ ልጇን ተገላገለች። ነገር ግን እንደ እናት አላየቻትም። እርሷን ላለማየትም ፈርማለች።
ሐኪሞች ገለጻ እንዳደረጉላት ከሆነ ልጇ ጤናማ አልነበረችም። የሰው ቅርፅ እና መልክ አልያዘችም። ይህም በአእምሮዋ ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድርባት እና ሥነ ልቦናዋ እንዳይጎዳ በሚል ነበር ልጇን ላለማየት የወሰነችው።
“እስካሁን ያ ክስተት ለምን እንዳጋጠመ አልገባኝም” የምትለው አባይ፣ የሰሃራ በረሃን ሲያቋርጡ በጭናቸው ሥር ሲገባ የነበረው ነዳጅ እና ግራሶ፣ የሚጠጡት የቤንዚን ውሃ፣ በቂ ምግብ እና ውሃ አለማግኘት የፈጠረባት ችግር እንደሆነ ትገምታለች።
“ለፅንሱ እጅግ እሰጋ ነበር፤ ነገር ግን ምንም ምርጫ ስላልነበረኝ ያገኘሁትን ነበር የምበላው እና የምጠጣውም” ትላለች አባይ።
አባይ ከዚህ ሁሉ ፈተና በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ብትፀንስም ተመሳሳይ ችግር ነበር የገጠማት።
“ከእግዜር ጋር ሁሉ ተጣላሁ። በድጋሚ ልጄን እንደማላቅፍ ሳስብ ሕይወት ቀፈፈኝ። ራሴን ለማጥፋት ሞከርኩ” የምትለው አባይ ከዚያ በኋላ ያሉትን ዓመታት በለቅሶ እንዳሳለፈች ትናገራለች።
አብራው የተሰደደችው የባለቤቷ ፍቅርም እየቀዘቀዘ መጣ። በዚህ ሁኔታ በአውሮፓዊቷ ከተማ ሕይወትን መግፋት ይከብዳት ጀመር።
ፅንሱን እስከምትገላገል እንዲቆዩበት በእርዳታ ድርጅቶች የተሰጣቸውን ቤትም ለቀው እንዲወጡ ተነገራቸው።
የተዘጋ ቤት ሰበራ
ስደተኞች አስከፊውን ጉዞ አልፈው እንደ ዕድል አውሮፓ ቢገቡም ማረፍያ አያገኙም። በየባቡር ጣቢያው እና በየአውቶብስ መናኽሪያ ውለው የሚያድሩ ጥቂት አይደሉም።
አንዳንዶች የተዘጋ ቤት ሰብረው በመግባት ኑሯቸውን መምራት ይጀምራሉ።
ይህም ግን ቀላል አይደለም። የመንግሥት ተቃዋሚዎችን መደገፍ የግድ ይላል። ተቃዋሚዎቹ በሚጠሩት የተቃውሞ ሰልፍ ላይ መፈክር ይዘው መሰለፍ፣ ቋንቋው ባይገባቸውም በተቃውሞዎች ላይ መሳተፍ ይጠበቅባቸዋል።
አባይ ይህንን የተረዳችው አንድ የመንግሥት ተቃዋሚ በሮም አደባባይ ሲጮህ ከተመለከተች በኋላ ነበር።
እነዚህ ተቃዋሚዎች ዝግ የሆኑ ቤቶችን በመስበር ስደተኞችን እንደሚያስገቡ ጭምጭምታ ሰማች።
ቤት ለማግኘት ስትል ከተቃዋሚዎቹ ጋር ሰልፍ ማድረግ፣ ጥሪ በሚያደርጉበት ቦታ መገኘት ጀመረች። የማታውቀውን መንግሥት ስትቃወም፣ ያልገባትን መፈክር ስታንጠለጥል አንድ ዓመት አሳለፈች።
ከዚያም በሮም ከተማ ‘አናኒና’ በሚባል እና በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን በሚኖሩበት አካባቢ የተዘጋ ቤት ሰብረው ገቡ።
ቤቱ የሊቢያው ፕሬዚደንት የነበሩት ሙአመር ጋዳፊ ሆቴል እንደሆነ ይነገራል።
አባይ በዚህ ቤት ውስጥ ለ11 ዓመታት ኖራለች። ሁለት ጤናማ ልጆችንም አፍርታበታለች።
15 ዓመታትን በጣልያን ብታሳልፍም አሁንም የቤት ኪራይ መክፈል ያዳግታታል። አንድ ቀን የጣልያን መንግሥት ፊቱን ቢያዞር የምትወድቅበት ቦታ የላትም።
አባይ ከኢትዮጵያ - ዱባይ - ሱዳን - ሊቢያ - ጣልያን ያደረገችው የስደት ጉዞ በጣሊያን ቢገታም፣ የተነሳችበት ዓላማ፣ ለስደት የገፋትን አባቷን የማኩራት ዓላማዋ አልሰመረም።
አባቷ መከራዋን እንጂ መዳረሻዋን ሳያዩ ይህችን ዓለም ተሰናብተዋል።
አብራው ከተሰደደችው የፍቅር አጋሯ እና ከሁለት ልጆቿ አባት ጋርም ተለያይተዋል።
የልጆቿ አባትም የማንነት ጥያቄውን ለመመለስ ለተነሳበት ጉዞ መልስ ሳያገኝ አባቱን አጥቷል።
ከተሰደድሽበት ዓላማ የቱን አሳካሽ ሲል ቢቢሲ ላቀረበላት ጥያቄም መልሷ አጭር ነበር ።
“ምንም!”