ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ባሕር ሲያቋርጥ የሞተው ኢትዮጵያዊ ሚስት እና ልጆቹ የፈረንሳይ መንግሥትን ከሰሱ
ከፈረንሳይ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም በባሕር በኩል ሲያቋርጥ የሞተ አንድ የኢትዮጵያዊ ቤተሰብ በፈረንሳይ መንግሥት ላይ ክስ መሠረተ።
ከሁለት ዓመት በፊት ባሕር ላይ ጀልባቸው ተገልብጣ ከሰመጡ 27 ስደተኞች መካከል አንዱ ለሆነው ለኢትዮጵያዊው ፍቅሩ ሽፈራው ሞት በፈረንሳይ መንግሥት ላይ የቀረበው ክስ ከአደጋው ጋር በተያያዘ የቀረበ የመጀመሪያው አቤቱታ ነው ተብሏል።
በዩናይትድ ኪንግደም ጥገኝነትን ለማግኘት ባሕር ሲያቋርጥ ሕይወቱ ያለፈው የፍቅሩ ሽፈራው ባለቤት እና ሁለት ልጆቹ በሰሜን ፈረንሳይ ሊል ውስጥ ለሚገኝ ፍርድ ቤት ለደረሰባቸው ጉዳት በመንግሥት ላይ ክስ መክፈታቸውን የፈረንሳይ ዜና ወኪል - ኤኤፍፒ ዘግቧል።
በዚህ የክስ ሂደት ላይ የስደተኞች መብት የሚሟገተው ዩቶፒያ 56 የተባለው ቡድን እና የፈረንሳይ የሰብአዊ መብቶች ሊግ የተባለው ተቋም ከፍቅሩ ቤተሰቦች ጋር በመሆን የፈረንሳይን መንግሥት መክሰሳቸውን የኤኤፍፒ ዘገባ ጨምሮ አመልከቷል።
ይህም ኅዳር 12/2014 ዓ.ም. ደርሶ በርካታ ስደተኞች ላይ የሞት አደጋን ያስከተለውን የጀልባ መስመጥ በተመለከተ በፈረንሳይ ባለሥልጣናት ላይ የቀረበ የመጀመሪያው ክስ መሆኑን የመብት ተከራካሪዎቹ ገልጸዋል።
አደጋው በፈረንሳይ እና በዩናይትድ ኪንግደም መካከል ያለው የባሕር መተላላፊያ ከአፍሪካ፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ እና ከእስያ ተነስተው በፈረንሳይ በኩል ወደ ዩኬ ለመግባት ለሚሞክሩ ስደተኞች ዋነኛ መስመር ከሆነ ወዲህ ያጋጠመ አሰቃቂ አደጋ ነው ተብሏል።
ፍቅሩ እና ሌሎቹ ሰዎች ጉዟቸውን የጀመሩት በአየር በምትሞላ አነስተኛ ጀልባ ላይ ተሳፍረው የነበረች ሲሆን፣ በጉዞ ላይ ሳሉ ውሃ ወደ ጀልባዋ በመግባቱ ነበር የመስመጥ አደጋው ያጋጠመው።
በአደጋው ሕይወታቸውን ካጡት 27 ሰዎች መካከል አንዲት ነፍሰጡር ሴት እና ሦስት ልጆች የነበሩበት ሲሆን፣ ሁለት ሰዎች ሲተርፉ ሌሎች አራት ግን የደረሱበት ሳይታወቅ ቀርቷል።
በአደጋው ጊዜ ከጀልባዋ የተላለፈን 16 የድረሱልን ጥሪዎችን ተቀብለው ምላሽ ባለመስጠታቸው የፈረንሳይ ባለሥልጣናት ሲወቀሱ ቆይተዋል።
ባለፈው ዓመት የአገሪቱ ዓቃብያነ ህግ አደጋ ላይ ያሉ ሰዎችን ባለመርዳት በሚል ሰባት የፈረንሳይ ሠራዊት አባላትን ከሰዋል።
ጀልባዋ አደጋው ሲደርስባት የነበረችበት የባሕሩ ክፍል በእንግሊዝ ወይም በፈረንሳይ የውሃ ክልል ውስጥ ነው አይደለም የሚል ውዝግብ የተነሳ ሲሆን፣ በዋናነት ሁለቱም ወገኖች ከጀልባዋ ለተሰሙት የድረሱልን ተማጽኖዎች ምላሽ ባለመስጠት ሲወቀሱ ቆይተዋል።
የኢትዮጵያዊው ባለቤት እና ልጆች በፈረንሳይ መንግሥት ላይ የከፈቱትን ክስ ደግፎ ተባባሪ የሆነው የመብት ተሟጋች ተቋም ፕሬዝዳንት ፓትሪክ ቦድዊን በሂደቱ የሚሳተፉት ለውጥ ለማምጣት መሆኑን ገልጸዋል።
“እንዲህ ዓይነቶቹ አሰቃቂ አደጋዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ጉዳትን የሚያስከትሉ መሆናቸውን በማሳየት፣ ባሕር ላይ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን ያለመተባባር አደገኛ ፖሊዎች እንዲወገዱ” የማድረግ ዓላማ እንዳላቸውም ገልጸዋል።
የዩቶፒያ 56 ተወካይ ኒኮላይ ፖስነር ደግሞ በዚህ የክስ ሂደት ውስጥ የአደጋው ሰለባ የሆኑ የሌሎቹም ሰዎች ቤተሰቦች ይሳታፋሉ ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
ከሁለት ዓመታት በፊት ባጋጠመው እና 27 ሰዎች የሞቱባት የዓሳ ማስገሪያ ጀልባ በእንግሊዝ ቻናል በኩል ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ለመግባት የተነሱ ስደተኞችን ይዛ የተነሳችው ከሰሜን የፈረንሳይ የባሕር ጠረፍ ነበረ።
ነገር ግን ጀልባዋ ከባሕሩ መካከል ላይ ከደረሰች በኋላ ውሃ ወደ ውሰጧ በመስረጉ ተገልብጣ ከዚያ በፊት በስፍራው ካገጠሙት ሁሉ የከፋ የተባለው አደጋ ደርሷል።
በዚህም 27 ሰዎች የሞቱ ሲሆን ከመካከላቸውም 17ቱ ወንዶች፣ አንደኛዋ ነፍሰጡር የሆነች 7 ሴቶች፣ ሦስት ልጆች መሆናቸውን በወቅቱ የፈረንሳይ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቆ ነበር።