ዩኬ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ለማዘዋወር 370 ሚሊዮን ፓውንድ ትከፍላታለች

ዩናይትድ ኪንግደም ጥገኝነት ጠያቂዎችን ከግዛቷ ወደ ሩዋንዳ ለሚሰፍሩት ካላት እቅድ ለተወሰነው 370 ሚሊዮን ፓውንድ እንደምትከፍል የመንግሥት ወጪዎችን የሚከታተለው ተቋም ይፋ አደረገ።

ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) በአምስት ዓመታት ውስጥ ወደ ምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር ለሚዘዋወሩ ለእያንዳንዳቸው ጥገኝነት ጠያቂዎች 150,000 ፓውንድ ለሩዋንዳ መንግሥት ይከፍላል።

ሌበር ፓርቲ የኦሪት ጽህፈት ቤቱ ያወጣውን የገንዘቡን መጠን በተመለከተ “ብሔራዊ ቅሌት” ሲል የተቃወመው ሲሆን፣ የአገር ውስጥ ሚኒስቴር ግን “አንድ ነገር ለመሥራት ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል” ብሏል።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ “አሁን አንድ እርምጃ ካልወሰድን በ2026 ለጥገኝነት ጠያቂዎች መኖሪያ የሚወጣው ገንዘብ በየዓመቱ 11 ቢሊዮን ፓውንድ ይደርሳል” ሲሉ የውሳኔውን መነሻ አብራርተዋል።

የኦዲት ሪፖርቱ ይፋ የተደረገው የዩኬ ምክር ቤት አባላት ስደተኞችን ወደ ሌላ አገር የማዘዋወሩ ዕቅድን በተመለተ ከፍተኛ ግልጽነት እንዲኖር መጠየቃቸውን ተከትሎ ነው።

ለአምስት ዓመታት በተደረሰው ስምምነት መሠረት፣ ዩናይትድ ኪንግደም በሕገወጥ መንገድ ወደ ግዛቷ የሚገቡ ሰዎችን ወደ ሩዋንዳ በመላክ እዚያ ጥገኝነት እንዲጠይቁ ይደረጋል።

የዚህ ፖሊሲ ዓላማም በእንግሊዝ ቦይ በኩል በባሕር የሚገቡ ሰዎችን ለማስቆም ሲሆን፣ ይህ ዕቅድም ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ከቀዳሚ ዓላማዎቻቸው መካከል አንዱ ነው።

ቢሆንም ግን ዕቅዱ የሕጋዊነት እንቅፋት ስለገጠመው በእንጥልጥል ላይ ያለ ሲሆን፣ አስካሁን አንድም ሰው ወደ ሩዋንዳ አልተዘዋወረም።

ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ የተዘጋጀው ሕግ በፓርላማ አባላት የጸደቀ ሲሆን፣ በሚቀጥለው ሳምንት ክርክር ይደረግበታል። ነገር ግን አሁን ይፋ የሆነው የገንዘብ መጠን ጉዳይ እንቅፋት ሊሆን ይችላል ተብሏል።

በዚህ መርሃ ግብር አማካይነት የዩኬ የአገር ውስጥ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ለሩዋንዳ የምጣኔ ሃብት ድጋፍ እና ወደ አገሩ ለሚገቡት ሰዎች ሰዎች የሚውል ገንዘብ ይሰጣል።

ከአውሮፓውያኑ 2022 ጀምሮ አስካሁን ዩኬ 220 ሚሊዮን ፓውንድ ለሩዋንዳ የሰጠች ሲሆን በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታትም በየዓመቱ 50 ሚሊዮን ፓውንድ በመስጠት አጠቃላዩ 370 ሚሊዮን ፓውንድ ይሆናል።

ከ300 በላይ ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደ ሩዋንዳ የሚላኩ ከሆነ፣ በአንድ ጊዜ 120 ሚሊዮን ፓውንድ እና ተጨማሪ በእያንዳንዳቸው ሰዎች 20 ሺህ ፓውንድ ተክፍላለች።

በተጨማሪም ወደ ሩዋንዳ ለሚዘዋወሩት ጥገኝነት ጠያቂዎች ለእያንዳንዳቸው የመኖሪያ፣ የምግብ እና የትምህርት ወጪ የሚሆን 150,874 ፓውንድ መድቧል።

ነገር ግን ግለሰቦቹ ከሩዋንዳ ውጪ የሚሄዱ ከሆነ ገንዘቡ የሚቆም ሲሆን ለጉዟቸው የሚሆን 10 ሺህ ፓውንድ ብቻ ይሰጣቸዋል።

የኦዲት ተቋሙ ባወጣው መረጃ መሠረት ይህ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ ለማዘዋወር የወጣው ዕቅድ በ370 ሚሊዮን ፓውንድ ላይ የሚቆም ሳይሆን ተጨማሪ ወጪዎች እንደሚኖሩት አሳውቋል።

ተቃዋሚው ሌበር ፓርቲ በሚቀጥለው ምርጫ የሚያሸንፍ ከሆነ ወደ ሩዋንዳ ስደተኞችን ለማዘዋወር የተያዘውን እቅድ እንደሚሰርዘው አስታውቋል።