ኔታንያሁ ወደ ዩኬ ከመጡ ሊታሰሩ እንደሚችሉ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ጠቆመ

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) የእስር ትዕዛዝ ያወጣባቸው የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ቢጓዙ እስር እንደሚጠብቃቸው የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ጠቆመ።

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ቃል አቀባይ ስለ ኔታንያሁ ጉዳይ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ ባይሆኑም ነገር ግን መንግሥት “ሕጋዊ ግዴታዎቹን” እንደሚወጣ ተናግረዋል።

በያዝነው ሳምንት ሐሙስ ህዳር 12/ 2017 ዓ.ም ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) በጋዛ የጦር ወንጀሎችን በመፈጸም በከሰሳቸው ቤንያሚን ኔታንያሁ ላይ እና የእስራኤል የቀድሞ መከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት ላይ የእስር ማዘዣ አውጥቷል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚያን ኔታኒያሁ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ረሀብን እንደ ጦር መሣሪያ መጠቀም እንዲሁም ሆን ብሎ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በመፈጸም የጦር ወንጀሎች እና ሰብዓዊነት ላይ በተፈጸመ ወንጀል ነው የተከሰሱት።

ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ የፍርድ ቤቱ ፈራሚ አባል አገራት የእስር ትዕዛዙን ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚያስገድዱ ስምምነት ፈርመዋል።

ኔታንያሁ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ከገቡ ይታሰራሉ ወይ ተብለው የተጠየቁት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ “በመላምት” ላይ ተመስርተው አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።

ነገር ግን “መንግሥት ሕጋዊ ግዴታዎቹን እንደሚወጣ” አጽንኦት በመስጠት መልሰዋል።

በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ሕግ መሰረት “ፍርድ ቤቱ የእስር ማዘዣ ካወጣ በኋላ የተሾመው ሚኒስትር ትዕዛዙን ለሚመለከተው የዳኝነት ቢሮ ያስተላልፋል። ይህም ቢሮ በዩናይትድ ኪንግደም የእስር ትዕዛዙን ተፈጻሚነትን ያጸድቃል” ይላል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ መንግሥት በፍርድ ቤቱ ህግ የተገለጸውን ሂደት እንደሚከተል እና “ሁልጊዜም በአገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ የተደነገጉ ሕጋዊ ግዴታዎችን እንደሚያከብር” አረጋግጠዋል።

በዚህ የእስር ሂደት ውስጥ የትኛው የመንግሥት መስሪያ ቤት እንደሚሳተፍ ማረጋገጥ ያልቻሉ ሲሆን መንግሥት ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ የአገሪቱን ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሎርድ ሄርመር የሕግ ምክር ስለመጠየቁ ምላሽ አልሰጡም።

በአጠቃላይ ከመላው ዓለም የሚመጡ የእስር ማዘዣዎች እና ተላልፎ የመስጠት ጥያቄዎች ወደ እርምጃ ከመገባቱ በፊት ሆም ኦፊስ በተሰኘው መንግሥታዊ መስሪያ ቤት ላለው ልዩ ቡድን መላክ አለባቸው።

የዩናይትድ ኪንግደም ህግ የአይሲሲስን ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል ወይም ማስረከብ በሚለው ላይ ፍርድ ቤቶች የመጨረሻው ውሳኔ እንዳላቸው አስፍሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ መሆን አለመሆናቸውን የተጠየቁት ቃል አቀባዩ “በሁሉም ደረጃ ከእስራኤል ጋር መወያየታችን መሰረታዊ ነው” ካሉ በኋላ እስራኤልን “በተለያዩ ዘርፎች ቁልፍ አጋር ናት” ሲሉ ገልጸዋታል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ሎርድ ሄርመር አይሲሲ የእስር ማዘዣ ቢያወጣ በውሳኔያቸው ላይ ፖለቲካዊ ተጽዕኖዎች ጣልቃ ገብነት እንደማይፈቅዱ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

“ለኔታንያሁ የእስር ማዘዣ የእኔ ምክር የሚሆነው በህጋዊ ትንተና ላይ የተመሰረተ የህግ ምክር ይሆናል” ብለዋል።

ሐሙስ እለት የእስር ማዘዣ መውጣቱን ተከትሎ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት የአይሲሲን ነጻነት እንደሚያከብር እና በጋዛ አፋጣኝ የተኩስ አቁም እንዲደረስ ጫና በማድረግ ላይ እንዳተኮረ ተናግሯል።