ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምን ያህል ሐብት አላት? ከየት የመጣ ነው?
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ንብረቶች ዋጋ ከእምነቱ ምሥጢራት መካከል አንዱ ነው የሚል የቆየ አባባል አለ። ቤተክርስቲያኒቱ ለዘመናት ስትጠብቀው የቆየችው ምሥጢር ነው ለማለት ያህል።
ቤተክርስቲያኒቱ በበርካታ አገረ ስብከቶች ተከፋፍላለች። እያንዳንዳቸው የየራሳቸውን ሒሳብ ያንቀሳቅሳሉ።
የዓለምን 1.4 ቢሊዮን ካቶሊኮች የሚወክለውን የቤተ ክርስቲያንን አጠቃላይ ሐብት ማወቁ ከባድ ብቻ ሳይሆን የማይቻል ሥራ ነው።
ነገር ግን መቀመጫውን በቫቲካን ባደረገው በሃይማኖቱ መንፈሳዊ እና አስተዳደራዊ ሥልጣን ውስጥ እምብርት ከሆነው ከቫቲካን እንጀምር።
የመንበሩ መቀመጫ
ቤተክርስቲያኗ ባላት ምሥጢዊነት ምክንያት፣ ስለ ቫቲካን ሐብት መጠን የሚነገሩ መላምቶች ባለፉት ዓመታት ጨምረዋል።
ነገር ግን ሚያዝያ 21 የሞቱት ርዕሳነ ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ከሥልጣን ዘመናቸው መጀመሪያ አንስቶ፣ ለውጥ እና የበለጠ የፋይናንስ ግልፅነት እንዲኖር የተለያየ እርምጃ ወስደዋል።
ለአብነትም በአውሮፓውያኑ 2021 የሐዋርያዊ መንበረ ፓትርያርክ አስተዳደር (ኤፒኤስኤ) የሒሳብ መግለጫ ካሳተመ በኋላ አሁን በየዓመቱ ተግባራዊ የሚሆን አሠራር ሆኗል።
የፓትርያርክ አስተዳደሩ ከተቋቋመ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ እነዚህ ወጪ እና ገቢን የሚያሳዩ መግለጫዎች ይፋ መሆን ጀምረዋል።
እንደ አስተዳደሩ የቅርብ ጊዜ ሪፖርት ከሆነ፣ በ2023 በቫቲካን የሚተዳደሩ የቤተክርስቲያኒቱ አገረ ስብከቶች ከ52 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ያስመዘገቡ ሲሆን፣ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ወደ 8 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ሐብት ጨምሯል።
የተጣራ ሐብቱ ያልተገለፀ ቢሆንም በሮም የሚገኘው ገበያዎች፣ ባሕል እና ሥነ ምግባር ጥናት እና ምርምር ማዕከል መረጃ የቤተክርስቲያኒቱ የሐብት መጠን ወደ 1 ቢሊዮን ዶላር እንደሚጠጋ ገምቷል።
ይህ ዝርዝር በርካታ ሕንፃዎችን እና መሬቶችን አያካትትም።
ኤፒኤስኤ እንዳለው ቤተክርስቲያኑ ገቢ የምታገኘው ከ5,000 በላይ ንብረቶችን በማስተዳደር ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ አንድ አምስተኛው ተከራይተዋል።
ይህ የ84 ሚሊዮን ዶላር የሥራ ማስኬጃ ገቢ እና የተጣራ ዓመታዊ ገቢ ወደ 40 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ትርፍ ያስገኛል ይላል ኤፒኤስኤ።
እነዚህ ሁሉ አሃዞች ከቫቲካን የፋይናንስ ሥርዓት ጋር የተያያዙ እና በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሌሎች የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አገረ ስብከቶችን አያካትቱም።
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ፋይናንስ ያልተማከለ ሲሆን፣ እያንዳንዱ አገረ ስብከት የራሱን በጀት ስለሚያስተዳድር፣ በዓለም ዙሪያ ያለው አጠቃላይ ሐብቱ እና ገቢው በጣም ግዙፍ እና ምናልባትም ሊቆጠር የማይችል ይሆናል።
በሳኦ ፓውሎ በሚገኘው የካቶሊክ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ፈርናንዶ አልቴሜየር ጁኒየር "የመላውን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ንብረት ለመገምገም በተግባር የማይቻል ነው" ብለዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ የቤተክርስቲያኑ በርካታ አገረ ስብከቶች ከ71 እስከ 81 ሚሊዮን ሄክታር የሚሸፍን መሬት እንደያዙ መቀመጫውን በፓሪስ ያደረገው የሃይማኖቶች እና ሴኩላሪዝም ጥናት ተቋም (IREL) ገልጿል።
ስለዚህም ቤተክርስቲያኒቷ ከዓለም ታላላቅ የመሬት ባለይዞታዎች አንዷ ነች።
ንብረቶቹ አብያተ ክርስቲያናትን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ ሆስፒታሎችን እና ገዳማትን ያካትታሉ።
እውነተኛውን ዋጋ ለመለካት ባይቻልም በታሪክ ተመራማሪዎች ግምት የተዘገቡ አሃዞችን በመጨመር በዓለም ዙሪያ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ሀብት እንዳላት መገመት ይቻላል።
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሐብት መነሻ
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሐብት መሰብሰብ ወይም ትርፍ ማጋበስ እንደሌለባት የሚከለክል የራሷ ሕግ አላት።
ይህ የቀኖና ሕግ (code of canon Law) በመባል የሚታወቀውን ሕግ የምትከተለው ቤተክርስቲያኒቱ እንዴት ይህንን ሁሉ ሐብት ልታከማች ቻለች?
የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው ንብረቶችን እና ሐብትን መሰብሰብ የጀመረችው።
የሮማ ስርወ መንግሥት ይፋዊ ሃይማኖት ካቶሊክ እንዲሆን ካደረገው ንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ (272-337) ጀምሮ ቤተክርስቲያኒቷ ሐብትን መሰብሰብ መጀመሯን ኔይ ደ ሱዛ የተባለው የታሪክ ምሁር ጽፏል።
የታሪክ ምሁራን እንደሚሉት በዚያን ጊዜ ክርስቲያኖች በትህትና ዝቅ ያለ ሕይት ይኖሩ እና በራሳቸው ቤት ወይም ዋሻ ውስጥ እየኖሩ ያገለግሉ ነበር።
"እነዚህ ክስተቶች ክርስትናን እና የሮማን ስርወ መንግሥት ታሪክን በእጅጉ ቀይረዋል" ሲል ደ ሱዛ አክሏል።
"ቤተክርስቲያኒቷ ከመሳደድ ጀምሮ የብዙ ንብረቶች ባለቤት እና ተጠቃሚ ሆናለች።"
ነገር ግን ይህ ከሮማን ስርወ መንግሥት መኳንንት ጋር የሚወዳደር ሐብት እንዲኖራት አስችሏል።
ግዙፍ ሐብት
ቆስጠንጢኖስ እና ሌሎች በርካታ የሮማ ስርወ መንግሥት መሪዎች ከወርቅ እና ከብር በተጨማሪ ቤተ መንግሥቶቻቸውን፣ ርስቶቻቸውን፣ መሬትን እና የፍል ውሃ መታጠቢያዎቻቸውን ለቤተክርስቲያኒቱ ለግሰዋል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ስጦታ የሚሰጥበት ሥርዓት ተቋቋመ።
ዛሬ፣ ቤተክርስቲያኒቱ በዋጋ የማይተመኑ ሥራዎችን ታከናውናለች።
በየዓመቱ በሚሊዮን የሚገመት ገቢ የሚገኝባቸውን የሚጎበኙ ሙዚየሞች ታስተዳድራለች።
እንዲሁም የፋይናንስ ገበያ ላይ ኢንቨስት ማድረጓን ቀጥላለች።
የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የኃይል ማዕከል ቫቲካን ከተማ ነች።
መንግሥቱ በጳጳሱ የሚተገበር ፍፁም ንጉሣዊ ሥርዓት ነው - ለሮም ጳጳስ የተሰጠ ስም።
ቱሪዝም ሌላው የገቢ ምንጭ ነው።
- ሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ ሕንፃዎች፡ ሐዋሪያዊ ቤተ መንግሥት፣ የቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን፣ ከቤተክርስቲያኑ አጠገብ ያሉ ሕንፃዎች፣ ዶሙስ ቫቲካን (የቀድሞው የሳንታ ማርታ መኖርያ)
- ሙዚየሞች እና ጋለሪዎች፡15ሙዚየሞችን ጨምሮ የሲስቲን ቤተ መቅደስ፣ ራፋኤል ቤተክርስቲያን፣ ፒናኮቴካ ቫቲካን፣ የሚሽነሪ ኢትኖሎጂካል ሙዚየም እና ታሪካዊ ሙዚየም
- ቤተ መጻሕፍት እና ወመዘክሮች፡ የቫቲካን ሐዋሪያዊ ቤተ መጻሕፍት፣ ሐዋሪያዊ መዘክሮች፣ ሊብሬርያ ኤዲትሪሲ ቫቲካን
- የመገናኛ ብዙኃን እና ኮሚዩኒኬሽን፡ የቫቲካን ሬዲዮ፣ ሎሴቫቶሬ ሮማኖ ጋዜጣ፣ የቫቲካን መገናኛ ብዙኃን፣ የቫቲካን ቴሌቪዥን ማዕከል
- ሌሎች ተቋማት፡ የቫቲካን ባንክ፣ የቫቲካን ኦብዘርቫቶሪ
የቫቲካን ዋና ሐብቶች
ቫቲካን ከግዛቷ ውጪ 12 ግዙፍ ንብረቶችን ታስተዳድራለች።
የፒተር ፔንስ (Peter's Pence) በተሰኘ ሥርዓት በኩል ማኅበራዊ ሥራዎችን ለመደገፍ፣ የቫቲካን እንቅስቃሴዎችን፣ ቱሪዝም እና ሙዚየሞችን ለማንቀሳቀስ የሚውል ዓለም አቀፍ የበጎ ፈቃድ ልገሳዎችን ትቀበላለች።
ከቫቲካን ሙዚየም፣ ከሲስቲን ቤተክርስቲያን፣ ለመታሰቢያነት ከሚሠሩ ሳንቲሞች እና ቴምብሮች፣ ከቫቲካን ባንክ እንዲሁም ሐብቶቿን ከሚያስተዳድረው ሐዋሪያዊ መንበረ ፓትሪያርክ አስተዳደር (APSA) ገቢዎችን ታገኛለች።
ቤኒቶ ሙሶሎኒ
ቤተክርስቲያኗ አብዛኛዋ ሐብቷ የተገኘው ከጣልያኑ አምባገነን መሪ ቤኒቶ ሙሶሎኒ ነው።
ጣልያናዊው የታሪክ ተመራማሪ አንድሪያ ሪካርዲ እንዳለው እአአ በ1929 ሙሶሎኒ 1.75 ቢሊዮን የጣሊያን ሊሬ (በወቅቱ 91.3 ሚሊዮን ዶላር የተገመተ) ገንዘብ ለቅድስቲቱ መንበር አስቀምጧል።
ይህ የላተራን ስምምነት ወይንም የእርቅ ስምምነት ተብሎም ይታወቃል።
ገንዘቡ የታሰበው ጣሊያን አንድ አገር ሆና በተዋሃደችበት ወቅት በተለይም በ1860 እና 1870 ባለው ጊዜ ውስጥ ተይዞ ለነበረው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ንብረት ካሳ እንዲውል በሚል የተሰጠ ነው።
ከተሰጠው ገንዘብ ውስጥ ሩብ ያህሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒየስ 11ኛ ዘመናዊውን የቫቲካን ግዛት ለመመሥረት፣ የቅድስት መንበር ሕንፃዎችን ለመገንባት እና ለቫቲካን ሠራተኞች መኖሪያ ቤት ግንባታ ተጠቅመውበታል።
የተቀረው አደጋን ለመቀነስ በልዩ ልዩ ስትራቴጂዎች ላይ ኢንቨስት ተደርጓል።
ዛሬ ኤፒኤስኤ በጣሊያን፣ በእንግሊዝ፣ በፈረንሳይ እና በስዊትዘርላንድ ውስጥ ንብረቶች አሉት።
ሕንጻዎች እና መሬት
በአሁኑ ጊዜ ቤተክርስቲያኒቷ ያሏት መሬቶች 1.9 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያስገኛሉ።
እአአ በ 2019 ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ መዋዕለ ነዋይን በተለያዩ ተግባራት ላይ ፈሰስ ማድረግን ካፒታል እንዳይቀንስ የመከላከል ዘዴ መሆኑን ተናግረው ነበር።
"ያለው ተጠብቆ እንዲቆይ ወይንም ትንሽ እንዲያተርፍ ያደርጋል" ነበር ያሉት።
ሪካርዲ ይህ ጠቃሚ ነው ምክንያቱም ቅድስት ቤተክርስቲያኗ ምንም እንኳን በቫቲካን መንግሥት ድጋፍ ቢደረግላትም ራሷም አገር አይደለችም ብለዋል።
በሃይማኖታዊ ፋይናንስ ላይ ጥናቶች የሚያደርገው ተቋም (IHEFR) ምንም ግብር አትከፍልም እንዲሁም የሕዝብ ዕዳ የለባትም ሲል አስታውቋል።
ከንብረቶቹ በሚገኘው ገቢ እና ከሁሉም በላይ በአማኞች በሚሰጡ ልገሳዎች ይደገፋል።
ተቋሙ ይኹን እንጂ፣ የቫቲካን ዓመታዊ ገቢ እና ወጪ በጣም ዝቅ ብሎ ሪፖርት የተደረገ ሲሆን፣ አጠቃላይ ንብረቷ ቀደም ሲል ከተገለጸው (4 ቢሊዮን ዶላር ገደማ) እጥፍ ነው ብሏል።
ሐብታሞቹ አገረ ስብከቶች
በጀርመን የሚገኘው የኮሎኝ አገረ ስብከት በዓለም ላይ ካሉት የበለጸጉ አገረ ስብከቶች መካከል አንዱ ነው።
ገቢው በአብዛኛው የካቶሊክ ቤተክርስቲያንን ጨምሮ በመንግሥት እውቅና ካላቸው የሃይማኖት ማኅበረሰቦች አባላት በቀጥታ የሚሰበሰበው ግብር ነው።
እአአ በ2023፣ ቤተክርስቲያኗ ከዚህ ግብር በግምት 7.4 ቢሊዮን ዶላር ሰብስባለች።
ከመገናኛ ብዙኃን በቀረበ ተደጋጋሚ ጥያቄ መሠረት በጀርመን ከሚገኙት 27 አህጉረ ስብከቶች ግማሾቹ ንብረታቸውን ያሳወቁ ሲሆን፣ እነዚህም አሥር ባንኮች፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ 70 ሆቴሎች፣ የንብረት ድርጅቶች እና የመገናኛ ብዙኃን ይገኙበታል።
በአሜሪካ የሚገኝ ቤተክርስቲያን
በዩናይትድ ስቴትስ የምትገኘው ቤተክርስቲያን ለቫቲካን ትልቅ አስተዋፅዖ ታደርጋለች።
እንደ ኢንዲያና ኖትርዳም ያሉ ታዋቂ ዩኒቨርሲቲዎች (1.76 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንዳለው ሪፖርት ተደርጓል) እና በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው ጆርጅታውን (በ1.92 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አለው) እንዲሁም ሆስፒታሎች እና ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ሰፊ ንብረቶችን ያስተዳድራል።
የግዴታ ሃይማኖታዊ ግብር ባይኖርም፤ ነገር ግን ቤተክርስቲያኗ ከግለሰቦች ትልቅ ልገሳዎችን ትቀበላለች።
ብራዚል፡ የዓለም ትልቁ የካቶሊክ ማኅበረሰብ
ብራዚል በዓለም ትልቁ የካቶሊክ ማኅበረሰብ መኖሪያ ነች።
አገሪቷ በዓለም ላይ ትልቁ እና ሁለተኛው በጣም የሚጎበኝ የማሪያን ቤተ መቅደስ አላት።
የአፓሬሲዳ አገረ ስብከት በዓመት 10 ሚሊዮን ሃይማኖታዊ ተጓዦች ቤተ መቅደሱን ይጎበኛሉ።
በዚህም ምክንያት 35,000 ነዋሪዎች ባሉበት ከተማ ወደ 240 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ዓመታዊ ገቢ ታገኛለች።
የብራዚል አገረ ስብከት ከአማኞች ልገሳ የሚቀበሉ ሲሆን ግብርም አይከፍሉም።
ምንም እንኳን የተጠናከረ የፋይናንስ መረጃ ባይኖርም፣ ሰፊ የሆኑ ደብሮች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች እና ዩኒቨርሲቲዎችን ታስተዳድራለች።