ትራምፕ ያሳኩትን የምርጫ ድል ተከትሎ 'ደፋር' ተብለው በፑቲን ተሞካሹ

ለዶናልድ ትራምፕ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት ያስተላለፉት ቭላድሚር ፑቲን ተመራጩን ፕሬዝዳንት "ደፋር" ሲሉ አሞካሽተዋል።

የሩሲያው ፕሬዝዳንት በሶቺ ከተማ በተካሄደ ዝግጅት ላይ እንደተናገሩት ትራምፕ በዋይት ሃውስ ባሳለፉበት የመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው ከየአቅጣጫው ጫና በዝቶባቸው ነበር።

ትራምፕ የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም እሠራለሁ ማለታቸው "ቢያንስ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል" ሲሉ ፑቲን አክለዋል።

በምርጫ ዘመቻ ወቅት ዶናልድ ትራምፕ ጦርነቱን “በአንድ ቀን” ማቆም እንደሚችሉ ደጋግመው ቢናገሩም ይህ እንዴት ሊያሳኩ እንደሚችሉ በዝርዝር አልገለጹም።

የፑቲን ንግግር በርካታ ሰዓታትን የፈጀ እና የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን የዳሰሰ ነበር። በሐምሌ ወር በዶናልድ ትራምፕ ላይ የተካሄደውን የግድያ ሙከራ በተመለከተም ባደረጉት ንግግር ድርጊቱ “ተጽዕኖ እንደፈጠረ” ተናግረዋል።

ትራምፕ ጆሯቸው ተመትቶ ጠባቂዎቻቸው ከመድረሳቸው በፊት ቡጢ ጨብጠው እጃቸውን ከፍ በማድረግ “ተዋጉ ተዋጉ፣ ተዋጉ” ሲሉ ደጋፊዎቻቸው ትግላቸውን እንዲቀጥሉ አሳስበው ነበር።

ፑቲን "በእኔ አስተያየት በጣም ትክክለኛ በሆነ መንገድ እንደ ደፋር ሰው ማድረግ ያለበት አድርጓል" ብለዋል ።

ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ለመወያየት ዝግጁ እንደሆኑ የተጠየቁት ፑቲን “ዝግጁ ነን፣ ዝግጁ ነን" ሲሉ መልሰዋል።

ትራምፕ ከፑቲን ጋር ለመነጋገር መዘጋጀታቸውን ሐሙስ ዕለት ለኤንቢሲ ኒውስ ሲናገሩ "የምንነጋገር ይመስለኛል" ብለዋል።

በ2016ቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዶናልድ ትራምፕ በሂላሪ ክሊንተን ላይ የበላይ እንዲሆኑ ሞስኮ ጣልቃ ገብታለች በሚል ቢከሰሱም ክሬምሊን ግን ክሱን አስተባብሏል።

የአሜሪካ ልዩ አማካሪ ሮበርት ሙለር እአአ በ2016 በትራምፕ የምርጫ ዘመቻ እና በሩሲያ መካከል ስምምነት አለ ስለተባለው ውንጀላ ዙሪያ ማጣራት ቢያደርጉም ከሦስት ዓመት በኋላ ባወጡት ዘገባ ግን ምንም አይነት ማስረጃ አልተገኘም ተብሏል።

በሌላ መረጃ ደግሞ የአውሮፓ መሪዎች የትራምፕን ወደ ዋይት ሃውስ መመለስ ዙሪያ ሐሙስ ዕለት በቡዳፔስት ተወያይተዋል።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ ከተመራጩ ፕሬዝዳንት ጋር "በጣም ሞቅ ያለ" እና "አመርቂ ውይይት" ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

“በዩክሬን እና በአሜሪካ፣ በመላው አውሮፓ እና በአሜሪካ መካከል ያሉ ግንኙነቶች ውጤታማ እና አወንታዊ እንዲሆኑ ሁሉንም ነገር ማድረግ አለብን” ብለዋል።

በዩክሬን እና በአውሮፓ የሚገኙ በርካታ ሰዎች ትራምፕ ወደ ኪዬቭ የሚላከው የአሜሪካ ወታደራዊ እርዳታ ሊገታ ወይም ሊዘገይ ይችላል የሚል ጭንቀት ገብቷቸዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኬር ስታርመር በጉባኤው ላይ እንደገለጹት ዩክሬን ከሩሲያ ጋር በምታደርገው ጦርነት ለኪዬቭ የምትሰጠው ድጋፍ አሁንም “ጠንካራ” መሆኑን ለዘለንስኪ አረጋግጠዋል።

ቀደም ሲል የትራምፕን ድል “በቮድካ" እንዳከበሩ የገለጹት የሃንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን በበኩላቸው አሁን አሜሪካ እና አውሮፓ የንግድ መስመር ላይ ከባድ ንግግሮች ይገጥማቸዋል ብለዋል።

የትራምፕ የቅርብ አጋር የሆኑት ኦርባን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫው "ከአሜሪካ ጋር የሚኖረው የንግድ ጉዳይ ከመነሳቱም በላይ ቀላል አይሆንም" ብለዋል።

ትራምፕ ምርጫውን ከማሸነፉ በፊት በሁሉም የገቢ ምርቶች ላይ 10 በመቶ ቀረጥ እንደሚጥሉ ተናግረው ነበር።

"ወደፊት አውሮፓ ለራሷ ሠላም እና ደህንነት የበለጠ ኃላፊነት እንድትወስድ ስምምነት ነበር። የበለጠ ግልጽ በሆነ መንገድ ለማስቀመጥ አሜሪካውያን ብቻ እንዲንከባከቡን መጠበቅ አንችልም” ብለዋል ኦርባን።