ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሺዎች የሚቆጠሩ ሩሲያውያን ነፍሰ ጡሮች ዜግነት ለማግኘት ወደ አርጀንቲና እየገቡ እንደሆነ ተገለጸ
ባለፉት ወራት ከ5 ሺህ በላይ ሩሲያውያን ነፍሰጡሮች ዜግነት ለማግኘት ወደ አርጀንቲና መግባታቸውን የአገሪቱ ባለስልጣናት አስታወቁ።
ከቀናት በፊት ሐሙስ 33 ነፍሰጡር ሩሲያውያን በአንድ በረራ ተሳፍረው ወደ ሃገሪቱ መድረሳቸው ተገልጿል።
በተለይም በቅርብ ጊዜ ወደ አገሪቱ የመጡት ነፍሰ ጡሮች በመጨረሻዎቹ የእርግዝና ሳምንታት ውስጥ እንደሆኑም የአገሪቱ የብሔራዊ ፍልሰት ኤጄንሲ አትቷል።
ነፍሰጡሮቹ የአርጀንቲና ዜግነት ለማግኘት ሲሉ ልጆቹን በአርጀንቲና ለመውለድ እንዳቀዱም ነው የታመነው።
ቁጥራቸው በተለይም በቅርቡ ያሻቀበ ሲሆን ይህም በዩክሬን ጦርነት ምክንያት እንደሆነ የኃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ጠቁሟል።
ሐሙስ ዕለት በአንድ በረራ ወደ አርጀንቲና ቦነስ አይረስ ከደረሱት 33 ሴቶች መካከል ሶስቱ የያዟቸው የጉዞ ሰነዶች ላይ ችግር በመኖሩም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የብሔራዊ የፍልሰት ኤጀንሲ ኃላፊ ፍሎሬንሺና ተናግረዋል።
ከዚያ በፊት በነበረው በረራ ሶስት ሴቶችም በተመሳሳይ ችግር በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ነው የተገለጸው።
እነዚህ ነፍሰ ጡር ሴቶች አርጀንቲና የመጡት ለጉብኝት እንደነበር መጀመሪያ ላይ ተናግረው ነበር።
ነፍሰ ጡሮቹ ቱሪስት አለመሆናቸው አመላካች ጉዳዮች አለመኖራቸውን ተከትሎም ለጉብኝት እንዳልመጡም አምነዋል።
ሐሙስ ዕለት በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩት የሶስቱ ሴቶች ጠበቃ በበኩላቸው ሃሰተኛ ቱሪስቶች በሚል ተጠርጥረው ታስረዋል፤ ይህም በአርጀንቲና ህግ ውስጥ የሌለ ነው፤ ወንጀልም እንዳልሰሩና በህገወጥ መንገድ ነጻነታቸውን እንደተነጠቁም ተናግረዋል። ሴቶቹም ከእስር ተፈትተዋል።
እነዚህ ሴቶች ልጆቻቸው የአርጀንቲና ዜግነት እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ ምክንያቱም ከሩሲያ ፓስፖርት በበለጠም ነጻነት ስለሚሰጥ ነው ሲሉም ኃላፊዋ ተናግረዋል።
የአርጀንቲና ፓስፖርትን የያዙ ዜጎች ወደ 171 አገራት ከቪዛ ነጻ በሆነ መልኩ እንዲጓዙ ያስችላቸዋል።
በአርጀንቲና ልጅ በሚወልዱበትም ወቅት ልጆቻቸው ዜግነት የሚያገኙ ሲሆን የወላጆቻቸውን የዜግነት ሂደትም ያፋጥናል። አሁን ባለው ሁኔታ ሩሲያውያን ያለ ቪዛ ወደ 87 አገራት መጓዝ ይችላሉ።