በኢትዮጵያ በመንግሥት ኃይሎች የሚፈጸሙ ሰዎችን የመሰወር ድርጊት እየጨመረ መሆኑ ተገለጸ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአገሪቱ ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው ሰዎችን አስገድዶ የመሰወር ድርጊት በአፋጣኝ እንዲቆም ጠየቀ።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “ይህ አስከፊ የሆነ የአስገድዶ መሰወር ድርጊት በአስቸኳይ እንዲቆም መንግሥት አስፈላጊውን ጊዜያዊ እና ዘለቄታዊ እርምጃዎች እንዲወስድ” ጥሪ አቅርበዋል።

ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ ላይ በአብዛኛው የሲቪል እና የደንብ ልብስ በለበሱ የመንግሥት የፀጥታ እና የደኅንነት ሠራተኞች ያለ ፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ የሚፈጸም ነው ብሏል።

ይህ ሰዎችን አስገድዶ የመሰወር ድርጊት በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ፣ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ውስጥ ማጋጠሙን በመግለጽ፣ የዚህ ድርጊት ሰለባ የሆኑ ሰዎች ከመኖሪያ ቤታቸው፣ ከሥራ ቦታ ወይም ከመንገድ ላይ ተይዘው ከታሰሩ በኋላ ወዳልታወቀ ስፍራ ተወስደው እንደሚሰወሩ ኢሰመኮ ገልጿል።

ኮሚሽኑ ከደረሱት አቤቱታዎች እና ጥቆማዎች በመነሳት ሲያደርግ በነበረው ክትትል እንደተረዳው፣ በግድ እንዲሰወሩ ከተደረጉት መካከል ከፊሎቹ ከተወሰኑ ቀናት፣ ከሳምንታት ወይም ከወራት በኋላ የተገኙ ሲሆን፣ ሌሎቹ ደግሞ እስካሁንም የደረሱበት አለመታወቁን አመልክቷል።

በተጨማሪም የተወሰኑት ሲያዙ በወንጀል ተጠርጥረው የሚፈለጉ መሆኑ ተነግሯቸው ወደ መደበኛ ፖሊስ ጣቢያ ከተወሰዱ በኋላ የተሰወሩ እንዲሁም ሌሎቹ ደግሞ ምንም ሳይነገራቸው በፀጥታ ኃይሎች በግዳጅ ተወስደው የተሰወሩ ናቸው።

ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “የተሰወሩ ሰዎች ሁሉ በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቀቁ፣ በተሰወሩበት ጊዜ ሁሉ የተፈጸሙ ድርጊቶች ላይ የተሟላ ማጣራት ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ እንዲሁም ችግሩ የደረሰበትን አሳሳቢ ሁኔታ ከግምት በማስገባት አገር አቀፍ ገለልተኛ አጣሪ የሥራ ቡድን በማዋቀር የድርጊቱ ሰለባ የሆኑ ሰዎችን ማፈላለግ እና ፍትሕን ማረጋገጥ ይገባል” በማለት አሳስበዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች እና የማኅበራዊ ሚዲያ ተሳታፊዎች መሰወር እና የደረሱበት አለመታወቅ በስፋት እየተነገረ ሲሆን፣ ቤተሰብ እና ወዳጆችም የተሰወሩ ሰዎችን ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ መመልከት እየተለመደ መጥቷል።

የተሰወሩት ሰዎች በማን እንደተያዙ እና ወደየት እንደተወሰዱ ስለማይታወቅም ከቤተሰብ ጋር ሳይገናኙ ለቀናት፣ ለሳምንታት እንዲሁም ለወራት ቆይተው መለቀቃቸው ሲሳማ ቆይቷል።

በእንዲህ አይነት ሁኔታ የተያዙ ሰዎች እራሳቸው የት እንደነበሩ እንደማይያውቁ እና ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ መቆየታቸውን የተናገሩ ሲሆን፣ አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው በማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ ሲናገሩ በተደጋጋሚ ተሰምቷል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ላይ መንግሥት ይህንን ሰዎችን አስገድዶ የመሰወር ድርጊት እንዲያስቆም እና በፈጻሚዎቹ ላይ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።

ዋና ኮሚሽነሩ ዶ/ር ዳንኤል ጨምረውም “ይህንን ወንጀል ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመከላከል ይረዳ ዘንድ፤ ሁሉንም ሰዎች ከአስገድዶ መሰወር ለመጠበቅ የተደረገውን ዓለም አቀፍ ስምምነትን ኢትዮጵያ በአስቸኳይ ተቀብላ እንድታጸድቅ” ጥሪ አቅርበዋል።