የቀድሞው የቴስላ ሠራተኛ አሽከርካሪ አልባ መኪናዎቹ ደኅንነት ይጎድላቸዋል ሲል መረጃ አሾለከ

የቀድሞው የቴስላ ሠራተኛ የድርጅቱ አሽከርካሪ አልባ መኪናዎች አውራ ጎዳና መውጣት የሚያስችል ቴክኖሎጂ የላቸውም ሲል ለቢቢሲ ተናገረ።
መረጃ አሾላኪው ሉካስ ክሩፕስኪ ደንበኞች የቴስላ መኪናዎችን ገዝተው የፍሬን እና የአሽከርካሪ አልባ ቴክኖሎጂ ችግር እንዳጋጠማቸው የሚጠቁም መረጃ ባለፈው ግንቦት ለአንድ የጀርመን ጋዜጣ ሰጥቶ ነበር።
ግለሰቡ እንደሚለው ይህን ስጋት ለድርጅቱ ቢያነሳም የሚሰማው አካል አላገኘም።
ቴስላ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ቢጠየቀም ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል።
የቴስላ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢላን መስክ የመኪናዎቹ አሽከርካሪ አልባ ቴክኖሎጂ እጅግ የበለፀገ እንደሆነ ይናገራል።
“ቴስላ ማለት እጅግ ረቂቅ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ያለው መኪና ነው” ሲል ባለፈው ቅዳሜ ኤክስ የተሰኘው ማሕበራዊ ሚድያው ላይ ፅፏል።
ነገር ግን ክሩፕስኪ ለቢቢሲ በሰጠው ቃለ-መጠይቅ ሰው ሰራሽ አስተውሎት የቴስላን አሽከርካሪ አልባ ቴክኖሎጂ ለማዳበር ጥቅም ላይ የዋለበት መንገድ ያሰጋኛል ብሏል።
የቴስላ አውቶፓይለት የተሰኘው ቴክኖሎጂ የመኪናው መሪ በራሱ ጊዜ እንዲንቀሳቀስና ‘ፓርክ’ ማድረግ እንዲችል ቢያግዝም ሰዎች መሪውን ጨብጠው እንዲቀመጡ ይመከራል።
“እኔ ቴክኖሎጂው ብቁ ነው ብዬ አላስብም” ይላል መረጃ አሾላኪው።
“ይህ ሁላችንንም የሚነካ ነው። ምክንያቱም አውሮ ጎዳና ላይ መሞከሪያ እየሆንን ነው። ምንም እንኳ ቴስላ ባይኖርዎትም ልጆችዎ መንገድ እያቋረጡ ሊሆን ይችላል።”
ክሩፕስኪ እንደሚለው የኩባንያው ቋት ውስጥ አሽከርካሪ አልባው ቴክኖሎጂ የተወሰነ ክፍተት እንዳለው የሚጠቁም መረጃ ተመልክቷል።
አልፎም የሥራ አጋሮቹ “ፋንተም ብሬኪንግ” የተሰኘው አንዳች ነገር ሲመለከት ፍሬን የሚይዘው ቴክኖሎጂ ምንም አደጋ ሳያጋጥመው ፍሬን እንደሚይዝ እንደነገሩት ያወሳል።አክሎ ደንበኞች በሚልኩት የቅሬታ ደብዳቤ ላይ ይህ የፍሬን መያዝ ጉዳይ ተደጋግሞ እንደተነሳ ይጠቁማል።
የዩናይትድ ስቴትስ ፍትሕ ሚኒስቴር ካለፈው ጥር ጀምሮ የቴስላን አሽከርካሪ አልባ ቴክኖሎጂን በተመለከተ ምርመራ መጀመሩ ይታወቃል።
የጀርመኑ ሃንድልስብላት ጋዜጣ ከክሩፕስኪ 100 ጂቢ የሚሆን መረጃ ካገኘ በኋላ “ቴስላ ፋይልስ” የተሰኘ ዘገባ መሥራቱ ይታወሳል።
የቴስላ የአውሮፓ ዋና ቅርንጫፍ መቀመጫ በሆነችው ኔዘርላንድስ የሚገኘው የቴስላ መረጃ ጥበቃ ክፍል መረጃ ሾልኮ መውጣቱን ተከትሎ ምርመራ መክፈቱን ለቢቢሲ ጠቁሟል።
ክሩፕስኪ መረጃ አሾልኮ ማውጣቱን ተከትሎ ባለፉት ስድስት ወራት “ከባድ ጊዜ” እንዳሳለፈ ይናገራል።
“አንዳንዴ ማታ ማታ ምንም እንቅልፍ ሳይወስደኝ አድራለሁ” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
ነገር ግን ደፍሮ መረጃውን በማሾለኩ ብሉፕሪንት ከተሰኘው ተቋም የፍሪ ስፒች ዊስልብሎዊንግ ሽልማት አግኝቷል።
የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት አሽከርካሪ አልባ መከናዎችን በተመለከተ አዲስ ሕግ ለማርቀቅ ዕቅድ ላይ መሆኑ ተሰምቷል።












