የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ችግር አዙሪት እና ስጋቶቹ

የቻይና ዩዋን እና የአሜሪካ ዶላር እስሮች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአሜሪካው ፊች ሬቲንግስ የመንግሥታትን ብድር የመመለስ አቅም በመገምገም ደረጃ የሚያወጣ ተቋም ነው። በዘርፉ ስመ ገናና ከሆኑ ሦስት ተቋማት አንዱ መሆኑም ይነገርለታል።

ተቋሙ መመዘኛዎቹን ተጠቅሞ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት የኢትዮጵያን የውጭ ብድር የመክፈል አቅም ከዚህ ቀደም ከሰጠው ደረጃ ዝቅ አድርጎታል።

እንደተቋሙ ከሆነ ኢትዮጵያ ያለባትን ብድር የመመለስ አቅሟ መመናመኑን ነው በምዘናው ያመለከተው።

እንደ ፌች ግምት ከሆነ ኢትዮጵያ ሰኔ 30 በሚጠናቀቀው የዘንድሮ በጀት ዓመት አንድ ቢሊዮን ዶላር ገደማ የውጭ ዕዳ ክፍያ ይጠበቅባታል። ክፍያው በፈረንጆቹ 2025 ወደ 2 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ሊል እንደሚችልም ግምቱን አስቀምጧል፡፡

በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ በውጭ ምንዛሪ እጥረት የመፈተን ዕድሏ መጨመሩን ያሳያል።

አክሎም የአገሪቱ ዓለም አቀፍ የውጭ ምንዛሪ ክምችት በ2023 ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር መቀነሱን ጠቅሷል። ይህ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለአንድ ወር እንኳን በቅጡ የውጭ ብድሯን የሚከፍል አይደልም ብሏል።

የውጭ ምንዛሪ ክምችት ምንድነው?

የውጭ ምንዛሪ ክምችት መንግሥታት ያላቸው በዓለም አቀፍ ምንዛሪ በቀላሉ ወደ ገንዘብ ሊቀይሩት የሚችሉት የገንዘብ፣ የወርቅ፣ የቦንድ ወይንም ሌላ ዋጋ ያለው ነገር ሊሆን ይችላል።

በስፋት ተቀባይነት ያለው መገበያያ ገንዘብ የአሜሪካው ዶላር በመሆኑ የመንግሥታት የውጭ ምንዛሪ ክምችትም በዚሁ በዶላር ይለካል።

አገራትም በሚኖራቸው የውጭ ምንዛሪ ክምችትም የምጣኔ ሃብትታቸው ጥንካሬ እና ጤንነት ይለካል። ይህም ለብድር፣ ለንግድ፣ ለኢንቨስትመንትም ያላቸውን ተዓማኒነት አመላካች ነው።

ይህ የውጭ ምንዛሪ ክምችት በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት የቢዝነስ አማካሪ እና የተመሰከረላቸው የሂሳብ አዋቂው አቶ ጥላሁን ግርማ ይናገራሉ።

እንደባለሙያው ከሆነ ይህ የውጭ ምንዛሪ ክምችት የውጭ ብድርን ከነወለዱ ለመክፈል የሚያስችል ነው።

በዓለም አቀፍ ገበያ ባልተጠበቀ መልኩ የምርቶች ዋጋ ሲንር፤ ለምሳሌ የነዳጅ ዋጋ ሳይታሰብ ቢጨምር ወይም በአገራት መካከል በተፈጠረ ግጭት የዕቃዎች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ቢያሻቅብ የሚፈጠር ችግርን ለመቋቋምም ይውላል።

ከዚህ በተጨማሪም ለኢንቨስተሮችም መተማመኛ ነው።

ኢንቨስተሮች መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ሲያስቡ የሚያዩት የመጀመሪያ ነገር የአገሪቱ መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬ ክምችት ምን ያህል ነው? የሚለውን ነው። እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ አያያዙ ምን እንደሚመስልም ይመለከታሉ።

ይህ የአገራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት አስፈላጊ የሆኑ ምርቶች እና አገልግሎቶችን እንዲሁም ማሽኖችን ከውጭ አገር ተገዝተው ለማስገባት ጥቅም ላይ ይውላል።

“ይህ ክምችት በተለይም ብድር መክፈል አቅምን የሚገዳደር ከሆነ እና አገሪቱ የሚያስፈልጋትን ዕቃ ከውጭ ለማስገባት የማትችለበት ደረጃ ላይ ስትደርስ አስጊ ደረጃ ላይ ደረሰች ተብሎ ይወሰናል ማለት ነው” ብለዋል ጥላሁን።

አገራት እንደ አቅማቸው እና እንደ ምጣኔ ሃብታቸው ጥንካሬ ለሳምንታት፣ ለወራት እንዲሁም ለዓመታት የሚያገልግል የውጭ ምንዛሪ ክምችት ሊኖራቸው ይችላል።

ኢትዮጵያ በመደበኛ ሁኔታ ባለፉት ዓመታት ከጥቂት ወራት የሚበልጥ መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬ ክምችት ኖሯት አያውቅም።

ለአንድ ወር የሚበቃ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ነው ያለው ሲባል ግን ከ30 ቀናት በኋላ የውጭ ምንዛሪው ያልቃል ማለት አይደለም።

ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ በሚላክ ገንዘብ (ሬሚታንስ)፣ በእርዳታ፣ በብድር እና በወጪ ንግድም ይገኛል።

ለዚህም ነው ባለሙያዎች የውጭ ምንዛሪ ክምችት ተመናመነ ማለት ሁሉ ነገር አበቃ ማለት አይደለም የሚሉት።

ክምችቱ ካልጨመረ ስጋት ያሳድራል። ነገር ግን አበቃ ማለት አይደለም።

በቂ የሚባለው የውጭ ምንዛሪ ክምችት ስንት ነው?

በዚህ ጉዳይ ቁርጥ ያለ መልስ የለም። የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) አገራት ከሦስት እስከ ስድስት ወር መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬ ክምችት እንዲኖራቸው ይመክራል።

ለሦስት ወር የተባለውም መሻሻል ያለበት እንጂ ሁልጊዜም የሦስት ወር ብቻ ሆኖ መዝለቅ የለበትም።

እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገራት የሦስት ወር ክምችት መያዝ ጥሩ እንደሆነ ይመከራል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ከሦስት ወር ያነሰ የውጭ ምንዛሬ ክምችት አዲስ አይደለም።

የውጭ ምንዛሪ ክምችቱ በጣት ለሚቆጠሩ ቀናት ብቻ የሚበቃበት ደረጃ ላይ ደርሶም ያውቅ እንደነበረም ይነገራል።

የውጭ ምንዛሪ ክምችት እንዴት ይቀንሳል?

መንግሥት ያለው የውጭ ምንዛሪ ክምችት ይታወቃል።

ኢትዮጵያ ወደ አገር ውስጥ ምታስገባቸው ምርቶች መረጃም አለ። ዓመታዊውን ወጪ በማስላት በወር እና በቀን ስንት እንደሚወጣ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪው ለስንት ጊዜ እንደሚበቃ ይበቃል ይታወቃል።

በኢትዮጵያ “በየዓመቱ የገቢ ምርት እያደገ ነው የመጣው። የወጪ ንግዱ ደግሞ እንዘጭ እንዘጭ እያለ የመጣበት ሁኔታ ነው” ይላሉ ጥላሁን።

የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው ከውጭ የሚገባው ነው። ይህ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ይፈልጋል። ስለዚህ አገሪቱ ከምታገኘው የውጭ ምንዛሪ ይልቅ ምታወጣው ስለሚበልጥ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ይሳሳል።

ይህ ክፍተት ደግሞ ከተለያዩ ምንጮች በሚገኝ ብድር፣ በእርዳታ፣ ከውጭ በሚላክ የውጭ ምንዛሪ (ሬሚታንስ) በመሳሰሉት ነው የሚሸፈነው።

“ይህ ካልሆነ እና የሚጎድለው የውጭ ምንዛሪ ቋት ካልተሟላ አገሪቱ ዕዳ ውስጥ ትገባለች” በማለት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ያለውን ተጽእኖ ያስረዳሉ።

የአገራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ምንጭ አና ክምችቱ መጠን አና በበቂ ሁኔታ የሚያገለገለበተ ጊዜ የመጣኔ ሃበታቸውን ጥንካሬ ያሳያል።

ባለሙያው አቶ ጥላሁንም “በዚህ መሠረት ነው እንግዲህ የአገራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ጤናማ ነው አይደለም የሚለው የሚለካው” ይላሉ።

አገራት የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙላቸው ምርቶች እና አገልግሎቶች ስፋት እንዲሁም አስተማማኝነት በክምችታው ላይ ይነጸባረቃል።

ስለዚህም የኢትዮጵያ የወጪ ንግዱ መንገዳገድ “አገሪቱ ጥሩ ነገር ላይ እንዳልሆነች ስለሚያሳይ ነው ደረጃዋ ሊበላሽ ወደሚችል ወይንም ደግሞ ከፍተኛ ስጋት ወዳለበት ደረጃ የወረደው” ብለዋል።

የዩሮ እና የዶላር ኖቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እንደ ማሳያ ያነሱት ደግሞ ብድር መክፈያን በተመለከተ አዲስ የመክፈያ ሂደት ሽግሽግ (ሪስትራክቸር) እንዲኖር መጠየቋ ነው። ከዓለም አቀፍ የብድር የተቋማት ብድር ለማግኘት የምታደርገው ጥረትም ይጠቀሳል።

የውጭ ምንዛሪ ክምችቱ ካነሰ ሌተር ኦፍ ክሬዲት (የባንክ መተማመኛ ሰነድ) ከፍቶ ዕቃ ከውጭ ማስገባት አይቻለም።

“በጣም አስፈላጊ የሆኑ እንደ መድኃኒት እና እንደ ምግብ ያሉ ነገሮችን መግዛት አትችልም። ብድር መክፈልም አዳጋች ይሆናል ማለት ነው።”

ይህንን ሁሉ ከግምት ካስገባት በኋላ ነው ፊች ኢትዮጵያ የብድር መክፈል አቀሟ እየተመናመነ ነው በማለት፣ ስጋት ክልል ውስጥ እንዳለች የሚያመለክት ደረጃ ውስጥ ያስገባት።

የውጭ ምንዛሪ ክምችት እጥረት በምን ይገለጻል?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በኢትዮጵያ ያለው የውጭ ምንዛሪ ክምችት ላለፉት ዓመታት እያሽቆለቆለ ይገኛል። ከጊዜ ወደ ጊዜም እየተባባሰ ነው።

ለዚህ ደግሞ አስመጪዎች የሚፈልጉትን ያህል የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት አለመቻላቸው እና ጠይቀው መከልከላቸው አንዱ ማሳያ ነው።

በውጤቱም ወረፋ ጠብቀው ባገኙት የውጭ ምንዛሪ የሚያመጧቸውን ዕቃዎች በሁለት እና በሦስት እጥፍ ለገበያ ይቀርባሉ።

“የውጭ ምንዛሪ ክምችት መመናመኑ የሚታየው ለባንክ የጥያቄ ማመልከቻ ሲቀርብ ነው። ውጭ አገር ለመሄድ፣ ለህክምና፣ ለጉብኘት እና ለትምህርት ዶላር ጠይቆ ማግኘት ካልተቻለ የውጭ ምንዛሪ ክምችት አለመኖሩን አመላካች ነው። ምክንያቱም ካዝናቸው ተሟጣል” ይላሉ ጥላሁን።

የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከሌለ ከውጭ ተቋማት የተወሰደን ብድር መክፈል አይቻልም። በዚህ ምክንያትም አንዳንድ አገሮች እዳቸውን መክፈል ሰለሚያዳገታቸው እንደ አይኤምኤፍ እና ዓለም ባንክ ካሉ ተቋማት ተጨማሪ የብድር እና የመክፈያ የእፎይታ ጊዜ ይጠይቃሉ።

ነገሮች እሰኪስተካከሉ ከአበዳሪዎች ጋር መነጋገር እና ከውጭ የሚመጡ ዕቃዎችን ማስቀረትንም ይመርጣሉ።

የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ችግር ስለመባባሱ አንዱ ማሳያው ከዚህ ቀደም 38 ምርቶች ወደ አገር ቤት እንዳይገቡ መከለከላቸው ነው።

በዚህ ወሳኔም አንገብጋቢ ላልሆኑ ምርቶች የአገሪቱ ውስን የወጭ ምንዛሪ እንዳይውል በማድረግ “በዚህ ዘዴ ያላቸውን የውጭ ምንዛሪ በጣም ለሚያስፈልጉ ምርቶች ብቻ መጠቀም ማለት ነው” ብለዋል ጥላሁን።

ቢሆንም ግን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በሚያጋጥምበት ጊዜ ለኢንዱስትሪዎች የሚሆኑ ግብዓትን ማስመጣትም ከባድ ይሆናል።

በርካታ የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ለምርታቸው የሚውሉ ግባቶችን በበቂ መጠን ማግኘት ስላልቻሉ ከአቅም በታች እያመረቱ ሲሆን፣ አንዳንዶች ደግሞ ሥራ ወደ ማቆሙ ተቃርበዋል።

በአገሪቱ ያለው የውጭ ምንዛሪ ችግር በፍጥነት ፈር ካልያዘ ብድር ያለመክፈል የስጋት ደረጃን ይጨምራል። አበዳሪዎቸው ገንዘብ ለመስጠት መተማመን ያጣሉ። ይህ ደግሞ ለትልልቅ ፕሮጀክቶች ገንዘብ ማግኘትን አዳጋች ያደርገዋል።

መፍትሔውስ ምን ይሆን?

የውጭ ምንዛሪ ክምችት ሲቀንስ የተለያዩ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይችላሉ።

በአጭር ጊዜ የወጪ ንግድን መጨመር ከባድ ሊሆን ይችላል። በአጭር ጊዜ ውስጥ አገሪቱ መክፈል ያሉባት ብድሮች እንዲራዘሙ ማድረግ ግን ይቻላል። ተጨማሪ ብድር ለማግኘት መሞከርም እንደዚያው።

ይህ ደግሞ “ተበድሮ ዕዳን መክፈል ማለት ነው . . . አንዱ አበድሮን እንድንከፍለው ወጥሮ ሲይዘን ከሌላ ተበድረን እንደመክፈል ማለት ነው” ሲሉ ጥላሁን ያስረዳሉ።

ይህ ደግሞ የብድር አዙሪት ይፈጥራል።

ስለዚህ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ክምችት በረዥም ጊዜ ሂደት ለማሳደግ ደግሞ ቀዳሚ መፍትሄው ገቢ ምርቶችን ቀንሶ የወጪ ንግድን መጨመር ነው።

አገር ውስጥ ሊመረቱ የሚችሉትን በአገር ውስጥ ማምረት እንዲሁም ኢንዱስትሪዎችን መደገፍም ተገቢ ይሆናል።

እንደ ምሳሌም “ኢትዮጵያ ምርጥ ምርጥ የቅባት እህሎችን ወደ ውጭ ልካ ጥራት የሌለው ዘይት ወደ አገር ውስጥ እያስገባች” በመሆኑ ዘይቱን እዚሁ ማምረት ያስፈልጋል።

ዕሴት በመጨመር ወደ ውጭ የሚላኩ የምርት ዓይነቶችን መጨመርም ሌላው አማራጭ ነው።

“. . . ኢትዮጵያ ከአባጅፋር ጀምሮ እስከ ዐቢይ አሕመድ ድረስ የጅማን ጥሬ ቡና ስትልክ ነው የኖረችው። ያ መቀጠል የለበትም፤ እሴት በመጨመር ገቢን ማሳደግ ያስፈልጋል” ይላሉ ጥላሁን።

ሌላው የሚነሳው ፖሊሲ ጉዳይ ነው።

ብር ከዶላር ጋር ሲነጻጸር ያለውን ዋጋ የሚተምነው ብሔራዊ ባንክ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በየቀኑ ዶላር በብር ሲመነዘር ምን ያህል ሊሆን እንደሚገባ ተምኖ ለባንኮች ይፋ ያደርጋል።

ይህ ዶላር በባንኮች የሚሸጥበት ዋጋ ትክክለኛውን የዶላር ዋጋ አይወክልም፤ ባይሆን በትይዩ ገበያ (በጥቁር ገበያ) ያለው የዶላር ገበያ ዋጋ እውነታውን ያሳያል የሚሉ ተንታኞች አሉ።

“የብር መግዛት አቅም ቢቀንስ ወጪ ንግዱ ይሻሻላል የሚሉ ብዙ ናቸው። መንግሥት ደግሞ ያንን ካደረግኩ የዋጋ ንረት ያመጣብኛል የሚል ስጋት አለው። ይህ የመንግሥት የፖሊሲ ውሳኔ ነው። ብዙ የተያያዝ ነገር አለው” ብለዋል።

አውዳሚ የሆኑ ጦርነቶችን ማስቆምንም ባለሙያወ ከመፍትሄዎቹ ጋር አንስተዋል። ጦርነቶቹ ለዋጋ መናር ምክንያት በመሆናቸው ለሰላም ማስፈን ትልቅ ቦታ መስጠት ያስፈልጋል።

“እያንዳንዱ ጥይት እና ድሮን በውጭ ምንዛሪ ነው የሚገዛው። ከትራክትር ይልቅ ለጥይት የሚከፈለ ከሆነ ችግር ነው። . . . ስለዚህ ሰላምን ማስፈን ትልቅ ነገር ነው” ብለዋል።