ቫግነር ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ማሊ ከዩክሬን ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋረጠች

ማሊ የሠራዊት አባላቷ እና የሩሲያ ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ቫግነር ላይ ድንገተኛ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ከዩክሬን ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋረጠች።

በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ላይ የወጣው የማሊ ወታደራዊ መንግሥት በድንገተኛ ጥቃቱ የዩክሬን ባለሥልጣናት ሚና ነበራቸው ብሏል።

ባለፈው ወር ማሊ ከአልጄሪያ ከሚያዋስናት ድንበር አቅራቢያ የአገሪቱ ጦር አባላት እና የቫግነር ተዋጊዎች፤ ቱአሬግ በሚባሉ ተገንጣይ ኃይሎች ድንገተኛ ጥቃት ተከፍቶባቸው ነበር።

ለቀናት በዘለቀው ውጊያ ከአል-ቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለው እስላማዊው ተገንጣይ ቡድን በማሊ ጦር እና በቫግነር ተዋጊዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።

ከዚህ ጥቃት በኋላ የዩክሬን ጦር ደኅንነት ቃል አቀባይ አንድሪይ ዩሶቭ፤ ተገንጣይ አማጺ ቡድኑ ጥቃቱን እንዲፈጽም “አስፈላጊው መረጃ ተሰጥቶታል” ብለዋል።

የማሊ ጦር ከፍተኛ አዛዥ የሆኑት ኮሎኔል አብዱላዬ ማኢጋ በዚህ ጥቃት የዩክሬን ተሳትፎ ማሊን በእጅጉ ማስቆጣቱን ተናግረው፤ ኪዬቭ የባማኮን ሉዓላዊነት ጥሳለች ብለዋል።

ኮሎኔሉ ባወጡት መግለጫ የዩክሬን መንግሥት “ከአሸባሪ ኃይሎች ጎን በመሆን በዚህ አሳፋሪ፣ መሰሪ እና ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት ተባባሪ መሆኑን አምኗል” ብለዋል።

ይህን ተከትሎ ማሊ ከዩክሬን ጋር ያላትን ግንኙነት “በአስቸኳይ ለማቋረጥ” ወስናለች ብለዋል።

የማሊ ሠራዊት እና የቫግነር ተዋጊዎች ወታደራዊ ዘመቻ ለማድረግ ተጨማሪ ኃይል እየተጠባበቁ ሳለ ነበር ሐምሌ 18/2016 ዓ.ም. በተገንጣይ ቡድን ድንገተኛ ጥቃት የተከፈተባቸው።

ባለፈው ሳምንት የማሊ ጦር በዚህ ድንገተኛ ጥቃት ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰበት ይግለጽ እንጂ ምን ያክል አባላቱ እንደተገደሉ ያለው ነገር የለም።

በተመሳሳይ መጠሪያ ስሙን ከቫግነር ወደ ‘አፍሪካ ኮርፕስ’ የቀየረው የሩሲያው ተዋጊ ቡድን እንዲሁ በ1ሺህ ታጣቂዎች ድንገተኛ ጥቃት ተከፍቶበት ሄሊኮፍተሩ ተመትቶ መውደቁን እና አንድ አዛዡ መገደሉን ከመግለጽ ወጪ የደረሰበትን ዝርዝር የጉዳት መጠን አልገለጸም።

ይሁን እንጂ እስከ 80 የሚደርሱ ተዋጊዎቹ በዚህ ጥቃት ሳይገደሉ እንደማይቀር ይገመታል።

ተገንጣይ ኃይሎቹ በበኩላቸው 84 የቫግነር ተዋጊዎችን እና ወደ 50 የሚጠጉ የማሊ ወታደሮችን መግደላቸውን ገልጸዋል።

ይህ ቫግነር የደረሰበት ጉዳት አማጺ ኃይሎችን ለመዋጋት የማሊን መንግሥት መደገፍ ከጀመረ ከሁለት ዓመታት ወዲህ ትልቁ ሳይሆን እንደማይቀር ይገመታል።

ከአስር ዓመት በፊት የማሊ ማዕከላዊ መንግሥት በቱአሬግ አማጺ ቡድን እንቅስቃሴ ምክንያት አብዛኛውን የአገሪቱ ሰሜናዊ አካባቢ መቆጣጠር ተስኖታል።

አሁን ስልጣን ላይ ያለው የማሊ ወታደራዊ መንግሥት በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን ላይ የወጣው መንግሥት ሰሜናዊ የአገሪቱን ክፍል መቆጣጠር ተስኖታል በሚል ምክንያት ነበር።

ወታደራዊው መንግሥት ከፈረንሳይ ጋር የነበረውን ወዳጅነት በመተው ፊቱን ወደ ሩሲያ ካዞረ ሰነባብቷል።