ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢራን የሐማሱ መሪ ሃኒያ የተገደሉት ከቅርብ ርቀት ነው አለች
ኢራን የሐማስ የፖለቲካ ኃላፊ እስማኤል ሃኒያ የተገደሉት በእንግዳ ማረፊያው ከቅርብ ርቀት በተተኮሰ “አጭር ርቀት የሚመዘገዘግ ተተኳሽ” ነው አለች።
ምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን ግን ሃኒያ የተገደሉት የሞሳድ አባላት በማረፊያ ክፍላቸው የጠመዱት ቦምብ ከፈነዳ በኋላ ነው እያሉ ነው።
የኢራን አብዮታዊ ጥበቃ ኃይል እንዳለው ከሆነ 7 ኪሎ ግራም የሚመዝነው ተተኳሽ “ከፍተኛ ፍንዳታ” ፈጥሮ እስማኤል ሃኒያ እና ጠባቂዎቻቸውን ገድሏል።
የሐማሱ መሪ ባለፈው ረቡዕ ኢራን ውስጥ የተገደሉት ለአዲሱ የኢራን ፕሬዝዳንት በዓለ ሲመት ቴህራን በተገኙ ወቅት ነበር።
የኢራን አብዮታዊ ጥበቃ ኃይል ይህ ግድያ በአሜሪካ ድጋፍ በእስራኤል የተቀነባበር ነው ብሏል።
ይህ አብዮታዊ ኃይል ግድያውን በተመለከተ ያወጣው ሪፖርት ምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን ካወጡት ዘገባ ጋር ይቃረናል።
የእንግሊዙ ዴይሊ ቴሌግራፍ ሃኒያ የተገደሉት የሞሳድ አባላት በእንግዳ ማረፊያ ውስጥ የጠመዱት ቦምብ ከፈነዳ በኋላ ነው ብሏል።
ጋዜጣው የኢራን ባለስልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ሁለት የሞሳድ አባላት በእንግዳ ማረፊያው ሦስት ክፍሎች ውስጥ ቦምብ አጥምደው ነበር።
የሲሲቲቪ ምስሎችን የተመለከቱ የኢራን ባለስልጣናት ቦምቡን አጥምደዋል የተባሉ ሦስት የሞሳድ አባላት ቦምቡን ከአገር ውጪ ሆነው ከማፈንዳታቸው በፊት ከኢራን ወጥተዋል ሲሉ ለዴይሊ ቴሌግራፍ ተናግረዋል።
ኒው ዮርክ ታይምስም እንዲሁ ሃኒያ የተገደሉት በክፍላቸው ውስጥ ተጠምዶ የነበረው ቦምብ ከፈነዳ በኋላ ነው ብሏል።
እንደ ኒው ዮርክ ታይምስ ዘገባ ከሆነ የፈነዳው ቦምብ ክፍሉ ውስጥ ከተጠመደ ከሦስት ወራት በላይ ሊሆነው ይችላል።
የሐማስ ኃላፊዎች ለቢቢሲ ሃኒያ በዚህ የእንግዳ ማረፊያ ከዚህ ቀደም አርፈው እንደነበረ ተናግረዋል።
የሃኒያ ግድያ ተከትሎ በርካታ ቁጥር ያላቸው የኢራን አብዮታዊ ጥበቃ ኃይል አባላት ከሥራ ተባረዋል ወይም በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ኒው ዮርክ ታይምስ በዘገባው የአገሪቱ የደኅንነት ተቋም ግድያውን በተመለከተ ሰፊ ምርመራ እያደረገ ሲሆን በእንግዳ ማረፊያው የሚሰሩ ምርመራ እንደተደረገባቸው እና የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያቸው እንደተወሰደባቸው ጽፏል።
የሃኒያ በኢራን መገደል የአገሪቱን ደኅንነት በበላይነት በሚቆጣጠረው የአብዮታዊ ጥበቃ ኃይል ላይ ትችትን አስከትሏል።
እንደ ተባለው ሃኒያ የተገደሉት ክፍላቸው ውስጥ በተጠመደ ቦምብ ከሆነ የሞሳድ ሰላዮች በኢራን እንዳሻቸው እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ማሳያ ነው ይላሉ ባለሙያዎች።