በአልጄሪያዊቷ ቦክሰኛ ኢማኔ ኸሊፍ ላይ የተነሳው ውዝግብ ምክንያቱ ምንድን ነው?

በዘንድሮው የፓሪስ ኦሊምፒክ ውድድር ላይ አልጀሪያዊቷ ቦክሰኛ ኢማኔ ኸሊፍ አወዛጋቢ ሆናለች።

ለዚህም መነሻ የሆነው ኢማኔ እና የታይዋኗ ቦክሰኛ ሊን ዩ ቲን ባለፈው ዓመት በተካሄደ የሴቶች የዓለም ቦክስ ሻምፒዮና ላይ የጾታ ብቃት መመዘኛ ፈተናዎችን አላለፉም በሚል ከውድድሩ እንዲታገዱ መደረጋቸው ነበር።

በዘንድሮው የፓሪስ ኦሊምፒክስ ላይ ግን ከዚህ እግድ ነጻ ተደርገው በሴቶች የቦክስ ውድድር ተሳታፊ ሆነዋል።

የ25 ዓመቷ ኢማኔ በሴቶች የ66 ኪሎግራም የቦክስ ፍልሚያ ጣሊያናዊቷን አንጄላ ካሪኒን በመርታት ወደ ሩብ ፍጻሜ ገብታለች።

ሊን በበኩሏ በ57 ኪሎግራም የሴቶች ውድድር ምድብ የኡዝቤኪስታን ተፋላሚዋን ሲቶራ ቱርዲቤኮፋን በማሸነፍ የመጨረሻ ስምንቱ ውስጥ ገብታለች።

ባለፈው ዓመት ከነበረው የዓለም ሻምፒዮና ውድድር እንዲገለሉ ተደርገው የነበሩት እነዚህ ቦክሰኞች በዘንድሮው ኦሊምፒክ መሳተፋቸው አወዛጋቢ ሆኗል።

ከኢማኔ ጋር የኦሊምፒክስ የቦክስ ፍልሚያ በ46 ሰኮንዶች ውስጥ ግጥሚያውን አቋርጣ የወጣችው ጣሊያናዊቷ ካሪኒ ጉዳይ ለአንዳንድ ተቺዎች በር ከፍቷል።

ከዚህ ቀደም የፆታ መመዘኛዎችን ባለሟሟላት እንዳትሳተፍ ተደርጋ የነበረችን ቦክሰኛ በኦሊምፒክ እንድትወዳደር የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መፍቀዱ በአንዳንዶች ተተችቷል።

ጣሊያናዊቷ ካሪኒ ግጥሚያውን ያቋረጠችው “ሕይወቴን ለማትረፍ ነበር” ካለች በኋላ አልጀሪያዊቷ ተፋላሚዋን ይቅርታ ጠይቃለች።

ኢማኔ በበኩሏ ካሪኒን ካሸነፈች በኋላ ባደረገችው ንግግር “እዚህ የመጣሁት ወርቅ ለማግኘት ነው። ሁሉንም እፋለማለሁ” ስትል ተደምጣለች።

ቀደም ሲል የኦሊምፒክስ ቦክስ ውድድሮችን ያዘጋጅ የነበረው የዓለም አቀፉ የቦክስ ኤጀንሲ ሁለቱ ቦክሰኞች እንዲሳተፉ የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ያሳለፈውን ውሳኔ በጽኑ ተቃውሟል።

ኢማኔ በተፈጥሮ የትኛውን ፆታ ይዛ ተወለደች?

የቦክስ ሕይወቷ ከተጀመረ አንስቶ በሴቶች የቦክስ ውድድር ተሳታፊ የሆነችው ኢማኔ ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ በሴት አትሌትነት እውቅና ሰጥቷታል።

“አልጀሪያዊቷ ቦክሰኛ ሴት ሆና ነው የተወለደችው፣ በሴትነት ተመዘግባለች፣ ሙሉ ሕይወቷን የኖረችው በሴትነት ነው፣ ሴት ቦክሰኛ ናት፣ ሴት ሆና የተመዘገበችበት ፓስፖርት አላት” ሲሉ የዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ቃል አቀባይ ማርክ አዳምስ ተናግረዋል።

“ይህ ጉዳይ ፆታን የቀየሩ (የትራንስጀንደር) ጉዳይ አይደለም። በሆነ መንገድ ወንድ ከሴት ጋር እየተፋለመ ነው የሚሉ አንዳንድ ውዥንብሮች ተነስተዋል። ይህ ፍጹም ትክክል አይደለም። በዚህ ጉዳይ ላይ መግባባት ያለ ሲሆን፣ ወንድ ከሴት ጋር እየተፋለመ ላለመሆኑ ሳይንሳዊ መረጃዎች አሉ” ብለዋል ቃል አቀባዩ።

ኢማኔ በታዳጊነቷ ስለገጠሟት ነገሮች እንዲሁም ሴት ሆና ከወንዶች ጋር እግር ኳስ በመጫወቷ ስለደረሰባት መድልዎ እና መገለልም ታስረዳለች።

“መንገዶችሽ ላይ እንቅፋቶች እንዲያጋጥሙሽ አትፍቀጂ። ማንኛውንም ዓይነት እንቅፋቶች እና መሰናክሎች ተቋቁመሽ አሸንፊያቸው። ህልሜ የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘት ነው” ስትል በዘንድሮው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ተናግራ ነበር።

“እኔ ካሸነፍኩ ወላጆች ልጆቻቸው ምን ያህል ርቀት መጓዝ እንደሚችሉ ይገነዘባሉ። በተለይም በአልጄሪያ የተቸገሩ ሴት ታዳጊዎች እንዲሁም ልጆችን ማነሳሳት እፈልጋለሁ” ብላለች።

ኢማኔ ማንነቷን ከሴት ውጪ በሌላ መንገድ እንደማትመለከትም ታይቷል።

የኢማኔ የቦክስ ውድድር ጉዞ ምን ይመስላል?

የ25 ዓመቷ ኢማኔ ለስምንት ዓመታት ያህል በቦክስ ውድድር ስትሳተፍ ቆይታለች።

በዓለም መድረክ ላይ ብቅ ያለችው በአውሮፓውያኑ 2018 የዓለም ሻምፒዮና ላይ በአማተር የቦክስ ውድድር ስትሳተፍ ነበር። በወቅቱ የ19 ዕድሜ የነበራት ኢማኔ 17ኛ ደረጃን ነበር ያገኘችው።

በዓመቱ በተደረገው የሴቶች የዓለም ሻምፒዮና የቦክስ ውድድር ላይ ተሳትፋ 19ኛ ወጥታለች።

ለመጀመሪያ ጊዜም ከአራት ዓመታት በፊት በተደረገው የቶኪዮ ኦሎምፒክ ተሳታፊ ነበረች።

በወቅቱም በ60 ኪሎግራም ቀላል ክብደት የውድድር መደብ የተፋለመችው ኢማኔ በሩብ ፍጻሜው በአየርላንዷ ኬሊ ሃሪንግተን አምስት ለ ዜሮ ተሸንፋ ከውድድሩ ውጪ ሆናለች።

ኬሊ ሃሪንግተን በዚህ ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ሆናለች።

ከሁለት ዓመታት በፊት በነበረው የዓለም ሻምፒዮና የብር ሜዳሊያ በማግኘት የመጀሪያዋ አልጄሪያዊት ቦክሰኛ በመሆን ኢማኔ ታሪክ አስመዝግባለች።

በወቅቱም በአየርላንዳዊቷ ኤሚ ብሮድኸርስት ተሸንፋ የነበረችው ኢማኔ በዚያው ዓመት በነበሩት የአፍሪካ ሻምፒዮና እና የሜድትራንያን ውድድሮች የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ሆነች።

ባለፈው ዓመት በ66 ኪሎግራም ምድብ በአረብ ጨዋታዎች ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት የአሸናፊነቱን ስፍራ ወስዳለች።

ይህም አሸናፊነቷ በአፍሪካ የኦሊምፒክ ማጣሪያ ውድድር ተሳታፊነቷን ያረጋገጠ ሲሆን፣ በዘንድሮው ዓመት በሴኔጋል በተካሄደው የማጣሪያ ውድድር ሞዛምቢካዊቷ ተፋላሚዋን አልሲንጋ ፓንጉዋናን በማሸነፍ ውድድሩን አጠናቃለች።

በስምንት ዓመት የቦክስ ውድድር ቆይታዋ ኢማኔ 51 ጊዜ ተፋልማ 42 ጊዜ ስታሸንፍ በዘጠኙ ተረታለች። ከእነዚህ ድሎች ውስጥ ስድስቱ የተመዘገቡት በዝረራ ነው።

ጣሊያናዊቷን ቦክሰኛ መርታቷ ለምን አወዛጋቢ ሆነ?

ጣሊያናዊቷ ቦክሰኛ ካሪኒ የቦክስ ፍልሚያ ውድድሩ በተጀመረ በ46 ሰኮንዶችው ውስጥ ግጥሚያዋን አቋርጣ መውጣቷ ለውዝግቦች በር ከፍቷል። በዚህ ውድድር ኢማኔ ተፋላሚዋን ረትታታለች።

ጣሊያናዊቷ ቦክሰኛ ካሪኒ ግጥሚያውን ያቋረጠችው “ሕይወቴን ለማትረፍ ነበር” ብትልም በኋላ ላይ አልጀሪያዊቷ ተፋላሚዋን ይቅርታ ጠይቃለች።

ለውዝግቡ መነሻ የሆነው ባለፈው ዓመት በሕንድ መዲና ኒውደልሂ በተካሄደው የዓለም ሻምፒዮና ላይ ኢማኔ እንዳትሳተፍ ተደርጋ ውድቅ የመሆኗ ጉዳይ ነው።

ከቻይናዊቷ ያንግ ሊዩ ጋር ለወርቅ ሜዳሊያ ለመፋለም ሰዓታት ሲቀራቸው ነበር የዓለም አቀፉ የቦክስ ማኅበር ኢማኔን የፆታ ብቁነት ፈተናን አላለፈችም በሚል እንዳትሳተፍ ያደረጋት።

አልጄሪያዊቷ ቦክሰኛ መጀመሪያ ላይ ውሳኔውን ለስፖርት የግልግል ፍርድ ቤት ይግባኝ ብታቀርብም ሂደቱ ከተጀመረ በኋላ ግን ትታው ነበር።

በማኅበሩ ደንቦች መሠረት “ቦክሰኞች ተመሳሳይ ፆታ ካላቸው፣ ሴቶች ከሴቶች እንዲሁም ወንዶች ከወንዶች ጋር እንዲፋለሙ ይደረጋል” ይላል።

ማኅበሩ የሴት ፆታ ሲል እውቅና የሚሠጠው ፆታን ይወክላል የሚባለው ክሮሞዞም “ኤክስ ኤክስ” ሲሆን ወንድ ብሎ ዕውቅና የሚሰጠው ደግሞ “ኤክስ ዋይ” ክሮሞዞም ያላቸውን ነው።

ማኅበሩ የኢማኔን የቴስትሮን [የወንዶች የሚባለው ሆርሞን] መጠንን መመርመሩን ውድቅ አድርጎ ነበር።

ሆኖም የማኅበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክሪስ ሮበርትስ የኢማኔ የቴስትሮን መጠን እንደተመረመረ አምነው በተደረጉት ሁለት ምርመራዎች “የኤክስዋይ ክሮሞዞሞች” መገኘታቸውን ለቢቢሲ ስፖርት ተናግረዋል።

ሆኖም ሮበርት በተደረጉት ምርመራዎች የኢማኔን አካላዊ ሁኔታ “በተፈጥሯዊ ወንድ” የሚለውን የማያሳይ እንደሆነም ገልጸዋል።

የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በበኩሉ በእነዚህ ፈተናዎች ትክክለኛነት ላይ ጥርጣሬዎቹን አንስቷል።

“አሠራሩ ምን እንደሆነ አናውቅም። ፈተናው ትክክል ይሁን እንዲሁም ፈተናውን ማመን ይኖርብን እንደሆነ አናውቅም” ሲሉ የኮሚቴው ቃል አቀባይ ገልጸዋል።

“ፈተና ተካሂዷል መባል እና የፈተናውን ትክክለኛነት እንዲሁም አፈጻጸሙን በመቀበል መካከል ልዩነት አለ” ብለዋል።

ቢቢሲ ይህ ማኅበሩ አካሂዷል የተባለውን የፆታ ብቃት ፈተና ምን እንደያዘ ማወቅ አልቻለም።

ከማኅበሩ ውሳኔ በኋላ በኦሊምፒክ ደንብ ላይ ምን ተቀየረ?

በዓለም አቀፉ የቦክስ ማኅበር ይዘጋጁ የነበሩ የቦክስ ውድድሮችን የቶኪዮ ኦሊምፒክን ጨምሮ የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በአዘጋጅነት ተረክቦታል።

ኮሚቴው ከገንዘብ፣ ከአስተዳደር፣ ሥነ ምግባር፣ ከዳኝነት ጋር በተያያዙ ስጋቶች ምክንያት ማኅበሩን በአውሮፓውያኑ 2019 አግዶታል።

በኮሚቴው የተቀመጡለትን መሠረታዊ ማሻሻያዎች ማሟላት ያልቻለው ማኅበሩ ይህንንም ተከትሎ የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ባለፈው ዓመት ሥልጣኑን ነጥቆታል።

ውሳኔው በዘንድሮው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ በስፖርት የግልግል ፍርድ ቤት ይግባኝ ቢቀርብበትም እንዲጸና ብይን ተላልፏል።

የዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ የዓለም አቀፉን የቦክስ ማኅበር ሥልጣን የሰረዘው ማኅበሩ ኢማኔን እና የታይዋኗን ሊ ካለፈው ዓመት የዓለም ሻምፒዮና የቦክስ ውድድር ካገለለ ከአራት ወራት በኋላ ነው።

ኮሚቴው ከሦስት ዓመታት በፊት “በፍትሃዊነት፣ በአካታችነት እና በፆታ ማንነት እና በፆታ ልዩነቶች እና መድልዎ እንዳይኖር” የሚያደርግ ማዕቀፍ አውጥቷል።

ኮሚቴው ያወጣው ሰነድ የአገራት ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ለውድደሮች አትሌቶችን በሚመርጡበት ወቅት ሊከተሏቸው የሚገቡ አስር መርኆዎችን አስቀምጧል።

የዓለም አቀፍ ኮሚቴው “ዓለም አቀፉ ፌዴሬሽን ያስቀመጣቸውን የብቃት መመዘኛዎችን ያሟሉ አትሌቶች እንዲሳተፉ ድጋፍ ያደርጋል። ኮሚቴው በዓለም አቀፍ ፌዴሬሽኑ ብቁ የሆኑ አትሌቶችን በፆታ ማንነታቸው እና ወይም በፆታ ባህሪያቸው ላይ በመመሥረት አያገልም” ብሏል።

ለቦክስ ውድድሮች ምን ዓይነት ምርመራዎች ይደረጋሉ?

ኮሚቴው በኦሊምፒክ ውድድሮች ላይ አበረታች ንጥረ ነገሮችን ቁጥጥር በተመከከተ ኃላፊነቱን ለዓለም አቀፉ የምርመራ ኤጀንሲ (አይቲኤ) የሰጠው በአውሮፓውያኑ 2019 ነበር።

የዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ አበረታች ንጥረ ነገሮችን ሲጠቀም ወይም ሲያቀርብ የተገኘ ማንኛውንም አካልን እንደማይታገስ አስታውቋል።

ምርመራዎቹ የአንድን አትሌት የቴስቶስትሮን መጠንን ጨምሮ ሌሎች ምርመራዎችን ያካተተ ነው።

“ከወንዶች በበለጠ የቴስቶስትሮን መጠናቸው ከፍ ያለ በርካታ ሴቶች አሉ” የሚሉት የማኅበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሮበርትስ “ስለዚህ የቴስቶስትሮን ምርመራ ወሳኝ ነው የሚለው ሃሳብ እውነት አይደለም” ይላሉ።

የኢማኔ ጉዳይ ፆታ የመቀየር (የትራንስጀንደር) ክርክር ነው?

የኢማኔ ጉዳይ ፆታ የመቀየር (የትራንስጀንደር) ክርክክር ነው ወይ? ለሚለው ጥያቄ መልሱ በጭራሽ አይደለም የሚል ነው።

ኢማኔ ፆታዋን ስለመቀየሯ ወይም ራሷን (ትራንስጀንደር) በሚል ማንነት አትገልጽም እንዲሁም ፍናንፍንት (ኢንተርሴክስ) ስለመሆኗ የሚጠቁም ምንም አመልካች ነገር የለም።