የስደተኞች ቡድንን ወክላ በፈረንሳዩ ኦሊምፒክ ብስክሌት የምትወዳደረው እየሩ ገብሩ

“ጦርነቱ ተጀመረ እናም ሁሉ ነገር የከፋ ሆነ። በዚህ ሁሉ መካከል ጠንካራ ለመሆን እና በህልሜ ላይ ለማተኮር መረጥኩ” ይህንን ያለችው በትግራይ ጦርነት ምክንያት በፈረንሳይ ስደት ላይ ያለችው እየሩ ገብሩ ናት።

እየሩ ገብሩ በዘንድሮው የፓሪስ ኦሊምፒክ የስደተኞች ቡድንን ወክለው ከሚወዳደሩት አንዷ ናት።

የብስክሌት ተወዳዳሪ የሆነችው እየሩ በህልሟ ላይ ማተኮሯ “ያንን የመከራ ወቅት እንዳሳልፍ ረድቶኛል” ትላለች።

ለብስክሌት ጥቅል ፍቅር ያላት እየሩ የተወለደችው በ1990ዎቹ አጋማሽ በትግራይ ነው።

በፓሪስ ኦሊምፒክ የስደተኞችን ቡድን እንዲወክሉ ከተመረጡት 36 አትሌቶች መካከል አንዷ ናት።

በኦሊምፒክ በውድድር መሳተፍ ከትንሽነቷ ጀምሮ ስታልመው የነበረ እድል ነው።

“ስድስት ወይም ሰባት ዓመቴ እያለሁ ብስክሌት ሲወዳደሩ አያለሁ። አሸናፊዎቹን አይቼ በፍቅር ወደቅኩ” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

“ብስክሌት መንዳት እፈልጋለሁ” ብዬ ወሰንኩኝ የምትለው እየሩ ለመማርም አስር ዓመታት ያህል ፈጅቶብኛል ትላለች።

“ጠንክሬ መስራት እና በህልሜ ማመን እንዳለብኝ ወሰንኩኝ” ትላለች።

እየሩ ስታድግ ከነበረው የገንዘብ ውስንነት ጋር ተያይዞ የብስክሌት ውድድሯን የጀመረችው ዘግይታ ነው። በኢኮኖሚም ይሁን በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በርካታ ስፖርቶችን የሚጎዳ የዘመናት የተደራሽነት ችግር ነው።

“ብስክሌት መንዳት ለሃብታሞች ነበር። የራስሽ ብስክሌት ሊኖርሽ አይችልም” ስትል የ27 ዓመቷ እየሩ ትናገራለች።

እየሩ በ16 ዓመቷ ነው ብስክሌት ተከራይታ መንዳት የተማረችው። ከዚያም የአክሱም ከተማ ብስክሌትን ክለብ ተቀላቅላ የበለጠ ስለ ስፖርቱ ማወቅ ጀመረች።

አስቸጋሪ ምርጫ

በዚህም መካከል አስቸጋሪ ምርጫ ውስጥ ገባች። ትምህርቷን መቀጠል ወይም ጊዜዋን በሙሉ በብስክሌት ማሳለፍ።

“በጣም ከባድ ነበር ምክንያቱም በትምህርቴ ጎበዝ ስለነበርኩ ነው። እናም የብስክሌት ውድድር ስጀምር አንዱን መምረጥ ነበረብኝ” ስትል ተናግራለች።

“እናቴ ምንም ችግር እንደሌለውና እንደምትደግፈኝ ነገረችኝ። ሌሎች ዘመዶቼ በምርጫዬ ደስተኛ አልነበርኩም። ምክንያቱም በኛ አገር ለወደፊቱ ጥሩ ህይወት ሰው እንዲኖረው ዩኒቨርስቲ ገብቶ መማር አለባቸው የሚል እምነት ስላለ ነው” ትላለች።

“ነገር ግን በብስክሌት ላይ ማተኮር እፈልጋለሁ አልኩኝ። ቀላል ውሳኔ አልነበረም ነገር ግን እኮራበታለሁ” ትላለች።

የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ብስክሌተኞች በዓለም አቀፉ የስፖርት መድረክ ሲያንጸባርቁ ከተመለከተች በኋላ እየሩ ውሳኔዋ ቀላል እንደሆነ አሰበች።

ሶስት ጊዜ የኦሊምፒክ ወድድር ያሸነፈችው እንዲሁም በዓለም ሻምፒዮና እና በኮመንዌልዝ ጨዋታዎች የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊዋ ደቡብ አፍሪካዊቷ አሽሌይ ሙልማን ፓሲዮ አርዓያ ከሆኑላት መካከል አንዷ ነበረች።

“በጣም ጠንካራ እና ሁልጊዜም በአሸናፊነት ነው የምታጠናቀቅቀው” ስትል እየሩ ስለ አሽሌይ ትናገራለች።

“በዚያን ጊዜ ኢትዮጵያ አንድ ታዋቂና ‘ወርልድ ቱር’ ብስክሌተኛ ጽጋቡ ግርማይ ነበራት። እሱ ይህንን ማድረግ ችሏል። እኔም ይህንን ማሳካት እንደምችል አመንኩ” ትላለች።

“እነርሱም አነሳሱኝ” ስትል ተናግራለች።

የትግራይ ጦርነት መከሰት

እየሩ በትግራይ ክልል መዲና መቀለ ነዋሪነቷን አድርጋ ኢትዮጵያን በአህጉሪቷ እና በአለም መድረክ ውድድሮች መወከል ጀመረች።

በአውሮፓውያኑ 2017 በስዊዘርላንድ የዓለም ብስክሌት ማዕከል እንድትሰለጥን ተጋበዘች።

በስዊዘርላንድ ሶስት ዓመታትን ቆይታ ወደ መቀለ ስትመለስ ህይወቷን የሚገለባብጡ ጉዳዮች ተፈጠሩ።

ጥቅምት መገባደጃ 2013 ዓ.ም የተከሰተውን የትግራይ ጦርነት ተከተሎ የእየሩን የብስክሌት ውድድር ገታው።

የፌደራሉ መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች ባደረጉት ደም አፋሳሽ ጦርነት እስከ 600 ሺህ የሚደርሱ ነዋሪዎች አልቀዋል።

ከክልሉ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የተፈናቀሉ ሲሆን እንዲሁም ወደ 900 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ተሰደዋል።

ጦርነቱ ከተጀመረ ከስምንት ወራት በኋላ በቤልጂየም 2021 የዓለም ሻምፒዮና ላይ ለመወዳደር ስትል እየሩ ለስደት ተዳረገች።

ሆኖም በምትኩ በፈረንሳይ፣ ኒስ ከተማ ጥገኝነት ጠየቀች። ይህም ውሳኔዋ ለሁለት ዓመታት ያህል በፕሮፌሽናልነት መወዳደር እንዳትችል ገደባት።

“ህይወቴን ለማዳን ከአገሬ መውጣት ነበረብኝ” ሲል እየሩ ተናግራለች።

“ውድድር ወይም ስልጠና ላይ አልነበርኩም፤ ነገር ግን በራሴ ማመኔን አላቋረጥኩም። ከባድ ቢሆንም በቀላሉ ተስፋ መቁረጥ አልፈለግኩም” ትላለች

በፈረንሳይ የጥገኝነት ጥያቄዋ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ብስክሌትን የሚያስተዳድረው አለም አቀፉ አካል ዩሲአይ የቀድሞ አሰልጣኝ በፈረንሳይ ክለብ እንዲድታገኝ ረዷት።

“ከዚያም አህጉራዊ ቡድንን ተቀላቀልኩ እንዲሁም ለኦሎምፒክ የስደተኞች ስኮላርሺፕ አገኘሁ” ስትል አክላለች።

በዚያም “የብስክሌት ህይወቴ እንደገና ተወለደ” ብላለች።

100 ሚሊዮን ስደተኞችን የምትወክለው እየሩ

በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ 53 ስፖርተኞችን የሚደግፈው የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አማካኝነት የስደተኛ አትሌት ስኮላርሺፕ ተጨማሪ ድጋፍ ያገኘችው እየሩ በኒስ ከሚገኘው አዲሱ ቤቷ ሆኗ በብስክሌት ውድድር ላይ እንደገና ማተኮር ችላለች።

እናም በተለይም አንዷን ህልሟን ልታሳካ ጫፍ ደርሳለች።

“በኦሊምፒክ መሳተፍ የሁልጊዜም ህልሜ ነው። የኦሊምፒክ አሸናፊ የመሆን ህልሜ ነው” ትላለች እየሩ

“ኢትዮጵያ በሩጫ ውድድሮች ጎበዝ የሆኑ አትሌቶች ስላሉ በርካታ ኦሊምፒክን ተመልክቻለሁ። ለዚያም ነው ኦሊምፒክ ሁሉም ነገር ነው እንድል ያደረገች” ትላለች

“እናም አሁን ህልሜን ለማሳካት እድሉን አግኝቻለሁ። ህልሜም በመሳካቱ ምስጋናየ ከፍ ያለ ነው” ስትል ገልጻለች።

እየሩ በመጪው እሁድ፣ ሐምሌ 28/ 2016 ዓ.ም በትሮካዴሮ ላይ በሚደረገው የሴቶች የመንገድ ላይ የብስክሌት ውድድር በመሳተፍ የህይወት ህልሟን ታሳካለች።

“በጣም ትልቅ ነገር ነው” ትላለች እየሩ “በዓለም ዙሪያ ያሉ ከ100 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን እወክላለሁ። እነሱን በመወከሌ ደስተኛ ነኝ እንዲሁም ኩራት ይሰማኛል” ብላለች።

ኢየሩን በዜግነት በተቀበለቻት አገር የኦሎምፒክ ችቦ እንዲያበሩ ከተመረጡም አንዷ ሆናለች።

እየሩ ከፈረንሳይ መዲና በስተምዕራብ ባለው ገጠራማ አካባቢ በሚካሄደው የ158 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ የብስክሌት ውድድር ትሳተፋለች።

“ፈታኝ እንደሚሆን አውቃለሁ” ትላለች እየሩ።

“ይህ የጎዳና ውድድር ለታላላቅ ብስክሌተኞች ነው። ነገር ግን የምችለውን ያህል ተዘጋጅቻለሁ። በመጀመሪያዬ ኦሎምፒክ ተሳትፎየ መደሰት እናም በውድድሩ የምችለውን ያህል አደርጋለሁ” ብላለች።

“ለትንሽ ነገር ማቀድ አልፈልግም። ስደተኞችን ለመወከል የተቻለኝን ሁሉ አደርጋለሁ” ስትል ገልጻለች።