ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የንግሥቲቷ የቀብር ሥነ ሥርዓት የሚፈጸምበት ዕለት ብሔራዊ በዓል እንዲሆን ጸደቀ
የንግሥት ኤልዛቤጥ የቀብር ሥነ ሥርዓት ዕለት በመላው ዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ በዓል እንዲሆን በልጃቸው ንጉሥ ቻርለስ ሳልሳዊ ጸደቀ።
አዲሱ ንጉሥ በለንደን በተካሄደው የንግሥና ሥነ ሥርዓት ላይም ነው ይህንን ያጸደቁት።
የንግሥቲቱ የቀብር ሥነ ሥርዓት በቀጣይ ሰኞ መስከረም 09/2015 ዓ.ም. ይፈጸማል።
ብሪታንያን ለረጅም ዓመታት በንግሥና የገዙት ንግሥት ኤልዛቤጥ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ከሰዓት በኋላ በባልሞራል በሚገኘው የስኮትላንድ ግዛት ውስጥ ይህችን ዓለም ተሰናብተዋል።
የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው የሚካሄደው የብሪታንያ ነገሥታት እና ንግሥቶች ዘውድ በተቀዳጁበት በዌስት ሚኒስትር አቤ በሚገኘው ታሪካዊ ቤተ ክርስቲያን ነው።
ይህ ቤተ ክርስቲያን ንግሥት ኤልሳቤጥ ሁለተኛ በአውሮፓውያኑ 1947 ልዑል ፊሊፕ ጋር ጋብቻቸውን የፈጸሙበት ነው።
በአውሮፓውያኑ 2002 የንግሥቲቱ እናት የቀብር ሥነ ሥርዓት ቢደረግም ከ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በአቤ ውስጥ የንጉሣዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት አልተደረገም።
ዌስት ሚኒስትር አቢ በአውሮፓውያኑ 1953 የንግሥት ኤልዛቤጥ የንግሥና ሲመትን ጨምሮ የብሪታንያ ነገሥታት በዓለ ሲመትም የሚከናወንበት ነው።
ከተለያዩ አገራት የሚመጡ የዓለም መሪዎች የንግሥቲቱን ሕይወት እና አገልግሎት ለማስታወስ የንጉሣዊ ቤተሰብ አባላትን እንዲቀላቀሉ ይጋበዛሉ።
የዩናይትድ ኪንግደም ከፍተኛ ፖለቲከኞች እና የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሮች በቴሌቭዥን በሚተላለፈው አገልግሎት ላይ ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አንዳንድ የንግድ ድርጅቶች እና ተቋማቶች በዚህች ዕለት ለመዝጋት በመወሰናቸው ምክንያት የዕለት ተዕለት ኑሮ በቀደመው መልኩ አይሆንም ተብሎ ይጠበቃል።
ሮያል ሜይል በዕለቱ የፖስታ አገልግሎቶቹ እንደሚታገዱ አስታውቋል እንዲሁም እንደ ሃሮድስ ያሉ መደብሮችም ለመዝጋት ማቀዳቸውን ተናግረዋል።
የታወጀው ብሔራዊው የሐዘን ጊዜ እስከ መንግሥታዊው የቀብር ሥነ ሥርዓት ድረስ እንደሚቆይ መንግሥት አስታውቋል።
ድርጅቶችና ተቋማት የታቀዱ ዝግጅቶችን የመሰረዝ ግዴታ ባይኖርባቸውም ነገር ግን የንግሥቲን ህልፈተ ሕይወት ተከትሎ በርካታዎቹ ቀድሞውኑ ተሰርዘዋል ወይም ለተወሰኑ ቀናት ለሌላ ጊዜ ተላልፈዋል ።
በፕሪምየር ሊግ፣ በእንግሊዝ እግር ኳስ ሊግ፣ በስኮትላንድ፣ በሰሜን አየርላንድ የሚደረጉ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች እስከ ማክሰኞ የተራዘሙ ሲሆን፣ በሴቶች ሱፐር ሊግ፣ የሴቶች ሻምፒዮና እና የሴቶች ኤፍኤ ዋንጫ ሁሉም ጨዋታዎች እንዲራዘሙ ተደርገዋል። በርከት ያሉ የፈረስ እሽቅድምድም፣ ጎልፍ እና የቦክስ ፍልሚያዎችም ተቋርጠዋል።
ለሚቀጥለው ሳምንት የታቀዱ መጠነ ሰፊ የሥራ ማቆም አድማዎች የንግሥቲቱ ሞት ተከትሎ ወዲያውኑ የተሰረዙ ሲሆን፣ የሠራተኛ ማኅበር ኮንግረስ በብሪታኒያ በሳምንቱ መጨረሻ የሚያካሂደውን ዓመታዊ ጉባኤ ለንግሥቲቱ ክብር ሲባል ለሌላ ጊዜ አስተላልፌያለሁ ብሏል።