ፕሬዝዳንት ሩቶ ከፍተኛ አመጽ የታየበት ተቃውሞ ከገጠማቸው በኋላ የአገሪቱን ጦር አሰማሩ

የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ማክሰኞ በመዲናዋ ናይሮቢ እና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ተቃዋሚዎች ከፖሊስ ጋር ተጋጭተው በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ከደረሰ በኋላ መሰል አመጽ እንዳይደገም ሁሉንም ሕግ አስከባሪ አሰማራለሁ አሉ።

ማክሰኞ ሰኔ 18/2016 ዓ.ም. የኬንያ ፓርላማ ያጸደቀውን አዲስ የታክስ ሕግ ለመቃወም አደባባይ የወጡ ተቃዋሚዎች የአገሪቱን ፓርላማ ወረው በእሳት ያቃጠሉ ሲሆን፣ ፖሊስ በወሰደው እርምጃ ቢያንስ አምስት ሰዎች ተገድለዋል።

ፖሊስ በከፍተኛ ቁጥር የወጡ ወጣቶችን ለመበተን ጥይት ተኩሶ በርካታ ሰዎችን ማቁሰሉ ተገልጿል።

ቀኑን ሙሉ ከዋለው ተቃውሞ በኋላ ማክሰኞ ምሽት የአገሪቱ ፀጥታ ኃይሎች በመዲናዋ በሚገኙ የተለያዩ ስፍራዎች እየተንቀሳቀሱ የሰልፉ መሪ እና አስተባባሪ ናቸው የተባሉ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ስለማዋለቸው ተሰምቷል።

ፕሬዝዳንት ሩቶ ማክሰኞ ምሽት 3 ሰዓት ላይ ከቤተ-መንግሥታቸው በሰጡት መግለጫ “የተደራጁ ሕገ-ወጥ ቡድኖች በሕግ አክባሪ ኬንያውያን ተከልለው የአገሪቱን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አደጋ ላይ ጥለዋል” ብለዋል።

“ኬንያ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ በዴሞክራሲ ሥርዓቷ፣ በሕግ የበላይነት እና ሕገ-መንግሥታዊ ተቋማቷ ላይ ጥቃት ደርሷል” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ የዚህ ዓይነቱ ክስተት “በብሔራዊ ደኅንነታችን ላይ ለሚደርሱ ከባድ አደጋዎች ምላሽ የምንሰጥበትን ሁኔታ የቀየረ ነው” ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ሩቶ “የትኛውንም ዋጋ ቢያስከፍል” መሰል አመጽ ዳግም እንዳይፈጠር የተቻለንን ፀጥታ አስከባሪ አሰማርተናል ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ ይህን ይበሉ እንጂ ኬንያውያኑ ነገ ሐሙስ ሰኔ 20/2016 ዓ.ም. ሌላ የተቃውሞ ሰልፍ ከማድረግ ወደኋላ እንደማይሉ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሐሳባቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

ማክሰኞ በአገሪቱ ፓርላማ የጸደቀው አዲሱ የቀረጥ ሕግ ኑሮ ያስወድድብናል ሲሉ የቆዩት ኬንያውያን ወጣቶች በኢንተርኔት አማካይነት ተሰባስበው ከአገሪቱ ፓርላማ ፊት ለፊት የተቃውሞ ድምጻቸውን ሲያስሙ ቆይተዋል።

መንግሥት በበኩለ ታክስ በመጨመር ተጨማሪ ብድር ከሌሎች ምንጮች መውሰድ ሳያስፈልገው ለአስፈላጊ የመንግሥት ወጪዎች እና አገልግሎቶች ገቢ ለማግኘት ዓላማ አድርጎ መሆኑን ገልጿል።

ዊልያም ሩቶ ሥልጣን ከተቆጣጠሩ ጀምሮ በርካታ አዳዲስ እና በሕዝቡ ተቀባይነት ያላገኙ ግብሮችን አስተዋውቀዋል።

በዚህም በኬንያውያን ዘንድ ‘ዘኪዮስ’ የሚል ስያሜን አግኝተዋል። በክርስትና አማኞች ዘንድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካለ ዘኪዮስ ከሚባል ቀራጭ ጋር በማመሳሰል ነው።

ፕሬዝዳንቱ ግን አገሪቱን ካለችበት የ80 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ለማውጣት እና ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር አዳዲስ ግብሮችን ተግባራዊ ማድረግ የግድ ነው ይላሉ።

ማክሰኞ ዕለት የተከሰተውን እና በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰውን ተቃውሞ ተከትሎ ኬንያውያን፣ የተለያዩ ተቋማት እና አገራት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ከዊሊያም ሩቶ በፊት ለሁለት የሥልጣን ዘመን ኬንያን የመሩት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ መረጋጋት እና ሥነ ሥርዓት በአገሪቱ እንዲሰፍን ጥሪ አቅርበዋል።

“ሕዝብን ማድመጥ ምርጫ ሳይሆን በሕገ መንግሥታችን መርሆች የተደነገገው ግዴታ ነው” ያሉት የቀድሞ ፕሬዝዳንት መንግሥት የሕዝቡን ያድምጥ ሲሉ አሳስበዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ፖሊስ በተቃዋሚዎች ላይ ከልክ ያለፈ ኃይል እንዳይጠቀም እንዲሁም ተቃዋሚዎች በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን እንዲያሰሙ ጠይቀዋል።

መቀመጫቸውን በኬንያ ያደረጉ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች እና ከፍተኛ ኮሚሽነሮች ትናንት ማክሰኞ “በኬንያ የተመለከትነው ያልተጠበቀ እና አስደንጋጭ ክስተት ነው” ብለዋል።

የብሪታኒያ፣ ካናዳ፣ ዴንማርክ፣ ጀርመን፣ አሜሪካ እና ኔዘርላንድስ ዲፕሎማቶች ተቃዋሚዎችን ለመቆጣጠር የተወሰደው እርምጃ አስደንጋጭ ነው ብለዋል።

“በተለይ ከኬንያ ፓርላማ ውጪ የተመለከትነው ትዕይንት አስደንግጦናል” ካሉ በኋላ፤ “ሁሉም አካላት የሕግ የበላይነትን የማክበር እና የማስክበር ኃላፊነት አለባቸው” ብለዋል።